ETHIOREVIEW

በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ

የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በጋምቤላ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 45 የውጭ ሀገር ዜጎች እና ሦስት ኢትዮጵያውያንን ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የፀና የጉዞ ሰነድ፣ የመግቢያ ቪዛ እንዲሁም የመኖሪያ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገ-ወጥ የወርቅና የተለያዩ ማዕድናት ፍለጋ እንዲሁም የማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ 47 የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ዘጠኝ ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት እንዲሁም ሰባት ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችን ከእነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ገልጿል፡፡

ሀገራችን ከማዕድን ዘርፉ ተጠቃሚ እንዳትሆን በሕገ-ወጥ መንገድ ማዕድናትን በማውጣት በኮንትሮባንድ ከሀገር እንደሚያወጡ ደርሸበታለሁ ያለው የጋራ ግብረ-ኃይሉ በህገ-ወጥ መንገድ በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ተባባሪ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችና ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት ላይ እያደረገ ያለው ጠንካራ ክትትል በጋምቤላ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በሌሎች ክልሎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በሀገራችን የማዕድን ሃብት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል በመፈፀም የተጠርጣሩ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች እና ኃላፊነታቸው የተወሰነ የግል ማኅበራት ከነ-ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት በአካባቢው ኅብረተሰብ ጥቆማ መሠረት በተካሄደው ጠንካራ ክትትልና ኦፕሬሽን በመሆኑ ኅብረተሰቡ ላደረገው ቀና ትብብር የጋራ ግብረ-ኃይሉ ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረበ በየትኛውም አካባቢ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸሙ መሰል የወንጀል ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግና ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version