ሲዳማ በቀን 30ሺህ ሊትር ወተት ሊያመርት ነው፤ ኦሮሚያ ተጨማሪ 70 ግድብ ሊገነባ ነው

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው ስምንተኛ 8ኛ መደበኛ ስብሰባው በቀን ሰላሳ ሺህ ሊትር ወተት ለማምረት የሚስችለውን ተቋም ባጭር ጊዜ ገንብቶ ስራ እንደሚያስጀምር ገለጸ። የኦሮሚያ ክልል አሁን በመጠናቀ ላይ ካሉት 73 ግድቦች በተጨማሪ 70 አዳዲስ የመስኖ ግድቦችን ሊገነባ ነው።

በመደበኛ ስብሰባው የወተት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የክልሉን ህዝብ የዘርፉ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና በቂ ወተት ለማቅረብ ዘመናዊ የወተት እንስሳት እርባታ ክላስተሮች እንዲቋቋሙ የሚያስችል እስትራቴጂ ማጽደቁን የክልሉ መረጃ ያመልክታል።

የወተት ላሞች መንደር በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከሀይቅ ማዶ በሚገኝ አከባቢ 40 ሄክታር መሬት ላይ እንዲገነባ የመስተዳድር ምክር ቤቱ ወስኗል።በዚህ ክላስተር ዘመናዊ የእርባታ መንደር የሚገነባ ሲሆን 2ሺ የወተት ላሞች ወደ ማዕከሉ ገብተው በሁለት ዓመት ውስጥ ወተት ወደ ከተማ ማዕከላት ለገበያ በተመጣጣን ዋጋ እንደሚቀርብ ተመልክቷል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በቀን 30ሺ ሌትር ወተት ማቅረብ የሚችል ሲሆን ከ7ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድልም ይፈጥራል።

በተመሳሳይ የልማት ዜና በ”ፊና ኦሮሚያ” ፕሮጀክት ተጨማሪ 70 የመስኖ ግድቦች ለመገንባት መታቀዱ ተገልጿል። በፊና ኦሮሚያ ፕሮጀክት እየተጠናቀቁ ካሉ 73 የመስኖ ግድቦች በተጨማሪ 70 የመስኖ ግድቦች በዚሁ ዓመት ለመጀመር መታቀዱን የኦሮሚያ መስኖና አርብቶ አደር ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኢንጂነር አለሙ ረጋሳ ናቸው ያስታወቁት።

በክልሉ እየተገነቡ ካሉ 73 ግድቦች መካከል 14ቱ በቦረና ዞን በሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ተገንብተው በመጠናቀቅ ላይ እንዳሉ ገልጸው፤ ከእነዚህም ውስጥ የተጠናቀቁ መኖራቸውንም አስታውቀዋል። አነስተኛ ግድቦቹ እየተገነቡ ያሉት ውሃ አጠር በሆኑ ቦታዎች እንደሆነም ኢንጂነሩ ለኢፕድ አመልክተዋል።

እርሳቸው እንዳሉትም፤ በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለው የእርሻ ሥራ ነው፤ ይህን ለማሳደግ ደግሞ ውሃ ወሳኝ ነው። በተለይ ውሃ አጠር በሆኑ አርብቶ አደር አካባቢዎች ግድቡ ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ በቀጣይም ችግሩን ለመቅረፍ ተጨማሪ ግድቦች ለመገንባት መታቀዱንና ድርቅን በመስኖ እርሻ የመቋቋም ስራ ትኩረት እንደሚሰጠው አመልክተዋል።

See also  ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊላክ የነበረ የጦር መሳሪያ ተያዘ

Leave a Reply