Site icon ETHIOREVIEW

ጄነራል አበባው – የመንደር ጄነራል አይደለሁም … የአጥንት ፖለቲካ እንዲቀር ጥሪ አቀረቡ

የክልል ልዩ ኃይልን መልሰን እናደራጀው እንጂ እንበትነው አላልንም

ጄነራል አበባው ታደሰ

“ሲጀመር” አሉ ጂነራል አበባው፣ ሲጀምር አበባው ናቸው። ሲቀጥል ኢትዮጵያዊ ናቸው። ሲደመር ደግሞ የኢትዮጵያ ጀነራል ናቸው። ይህን ብለው ነው በአጥንታቸው መነሻ እንዲያስቡ ጫና ለማድረግ ወይም የዘር ቅርቃር ውስጥ እንዲገቡ ለሚደረገው ስም ማጥፋት ምላሽ የሰጡት።

የአገር መከላከያ ምክትል ኤታማዦር ሹም አበባ ታደሰ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ድፍን የመከላከያ ሰራዊት መኮንኖች ኢትዮጵያዊ እንጂ ወደ ክልል የሚሳቡ አይደሉም። የሚያስተዳድሩት ከአራቱም አቅጣጫ የመጣ የኢትዮጵያን ልጆች እንደሆነ አመልክተው ” የአንዱ መሆን አልችልም። የተገነባሁበት መንገድም ይህ አይደለም” ብለዋል።

ጀነራሉ ይህን ያሉት በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሲሰጡ ነው። “እባካችሁ ወንድሞቼ” ሲሉ የአጥንት ፖለቲካን ከማራመድ ራቁ ሲሉ ተማጽነዋል። ለማስፈራራት ሳይሆን ኢትዮጵያ የገነባቸው ሃይል ትልቅ በመሆኑ በዘር ካባ ተደራጅቶ መንገድ በመዝጋት የሚሆን ነገር እንደሌለም አስታውቀዋል።

“እንኳን ሕዝብ እኛ አስራ ስድስት ፋቲክ (የወታደር ልብስ) መለየት አልቻልንም” ያሉት ጄነራል አበባው፣ ሁሉም እኩል በመሆኑ አንዱን ትጥቅ አስፈትቶና አዳክሞ አንዱን ወገን የማሳበጥ አሰራር ፈጽሞውኑ እንደማይታሰብ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አንደኛ፣ ሁለተኛ የሚባል ህዝብ እንደሌለ አመልክተው ሁሉም እኩል እንደሆኑ በግልጽ ተናግረዋል። አያዘውም የክልል ልዩ ሃይላትን መልሶ የማደራጀት ስራ በጥናት፣ በውይይት፣ ሁሉም አካል የተስማማበት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያግድ ሃይል እንደሌለ ገልጸዋል። ይህን ሲሉ በመገረም ጥያቄ አንስተዋል። ማን ትጥቅ ፍቱ እንዳለ፣ ማን ይህን አሳብ ከየት እንዳመጣው፣ ለምን ዓላማ በዚህ መልኩ እንዲጋጋል እንደተፈለገ የጠቆሙት ጄነራሉ ” ትጥቅ የሚፈታ የለም። እንዲያውም ዘመናዊ መሳሪያ ይታጠቃል” ብለዋል።

“ፖለቲከኞቹ በተጣሉ ቁጥር በየክልሉ ከታጠቀ ሃይል ጋር ውጊያ ሰለቸን” ሲሉ የተድመጡት የመከላከያ ምክትል ኤታማሾር ሹም ” ፖለቲከኞች እኛ በናንተ ስራ ጣልቃ እንደማንገባ ሁሉ እናንተም በእኛ ስራ ጣልቃ አትግቡ። ህዝብ ሲመርጣችሁ ያደርሳችኋል” ሲሉ ህግ ተከትለው እንዲሄዱ መክረዋል። ጠቅይቀዋል።

ህዝብ ከክልል ክልል እንደፈለገ መጓጓዝ፣ ከመንደር መንደር እንዳሻው መንቀሳቀስ እንዳልቻለ አንስተው አሁን በሚደረገው አዲስ አደራረጃጀት ይህን ችግር ለመቅረፍ በስፋት ዝግጅት መደረጉን በማንሳት ውሳኔው የህዝብን ጥያቄ ለመተግባር እንደሆነ አመልክተዋል።

ስም ሳይጠሩ ፖለቲከኞች ከአጥንት ቆተራና የዘር ፖለቲካ ራሳቸውን እንዲያቅቡ ሲያስታውቁ በዘር ካባ እየተከናነቡ ችግር የሚፈትሩትን ወገኖች ዘልፈዋል። አካሄዱ ጥቅም እንደማያስገኝ ከትህነግ እንዲማሩም አሳስበዋል።

ሸኔም ሆነ ማናቸውም ተቃዋሚዎች መሳሪያ ፈትተው ወደ ንግግር እንዲመጡ ያሳሰቡት ጄነራል አበባው ” የሰላሙ ጥሪ የማይገባቸውና መሳሪያ የማያወርዱ ከሆነ ሁሉንም በቅርብ እንተርጋቸዋለን” ብለዋል። መከላከያ ማናቸውንም ግዳጅ ለመወጣት በቂ ድርጅትና ቁመና እንዳለው በማመልከት ከህጋዊ ጎዳና መዛነፍ ካሁን በሁዋላ እንደማይቻል ለሁሉም አካላት በአጭር ጊዜ ምላሽ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በዘር ካባ ተሸፍነው የሚሰርቁ፣ የሚተኩሱ፣ የሚያውኩና የሚያሳድሙ ከውስጥም ከውጭም መኖራቸውን አስታውሰው ስለማይጠቅማቸው እንዲተውት መክረዋል። በምርጫ ካልሆነ መንገድ በመዝጋትም ሆነ በሌላ ህገወጥ ተግባር ስልታንን መመኘት እንዲያቆም ህዝብ እንዲመክርና እንዲገጽም ጥሪ አቅርበዋል። የደም መፋሰስ ታሪክ እንዲያበቃ ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት አንድ የጸጥታ ሃይል እንዲኖር ህዝብ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ” ባሪያህ የሆነውን መከላከያ አግዝ” ሲሉ የወትሮውን ድጋፉን እንዳያቋርጥ ብለዋል።

ጄነራል አበባው የክልል ልዩ ኃይልን መልሶ የማደራጀት ተግባር አሁን የተጀመረ ተግባር አይደለም፤ ለረጅም ጊዜም ጥናት የተደረገበት ነው” ብለዋል፡፡

ጥናቱ የክልሎች ልዩ ሃይሎች ጥንካሬ ምንድነው ብሎ የተመለከተ ሲሆን፥ የክልሎች ልዩ ሃይሎች ክልላቸውን መጠበቃቸው፣ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ህይወታቸውን አሳልፈው መስጠታቸውና መሞታቸው፤ እንዲሁም መቁሰላቸውን በጥንካሬ ተመልክቷል ነው ያሉት።

ነገር ግን የልዩ ኃይል አወቃቀሩ ጉድለት እንደነበረው እና ህጋዊም እንዳልነበረም አመልክተዋል።

ከሀገሪቱ ህገመንግስት አንፃር ሲታይ አወቃቀራቸው ህጋዊ አይደለም፤ ህገመንግስቱም እውቅና አይሰጣቸውም ሲሉ ጄነራል አበባው አስረድተዋል።

ይህ ልዩ ሃይል አገነባቡ ብሄር ተኮር መሆኑን በማንሳትም፥ ይህም የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽር መሆኑ ጉድለቱ ነው ብለዋል።

የሀገሪቱን የፖለቲካ መፍቻ መንገድ አበላሽቷል ያሉት ጄነራል አበባው፥ “በምን አበላሸ ለሚለው በእኛ ህገ መንግስት ፖለቲካ እና ጉልበት አብሮ አይሄድም፤ ለዚህም ፖለቲከኛው በሃሳብ ማሸነፍ ሲያቅተው ሌላ በትር አለው ማለት ነው፤ የታጠቀውን ልዩ ሃይል ያነሳል” ሲሉ ነው ያስረዱት።

“ሌላው ልዩ ኃይል ያለበት እጥረት ለሀገር የሚሞተውን ሃይል መገዳደር መቻሉ ነው፤ ተገዳዳሪ ሃይል ተፈጠረ” በማለት ለዚህም እንደምሳሌ ለሁለት ዓመት የቆየውን የትግራይ ጦርነት አንስተዋል፡፡

በጥናቱ ይህ የክልሎች ልዩ ሃይል ትክክል አይደለም ከተባለ አራት አመት እንደሆነው ነው ያመለከቱት።

“በዚህም ይህንን ሃይል መልሰን እናደራጀው የሚል ውሳኔ ነው እንጂ የተወሰነው ይበተን፤ ትጥቁን እናስፈታው አልተባለም” ብለዋል።

የሚደራጅበትም መንገድ መከላከያ መግባት ያለበት ወደ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ የሚገባው ወደ ፌደራል እንዲገባ እና መደበኛ ፖሊስ መሆን የሚፈልገውም መደበኛ ፖሊስ እንዲሆን ነው የተቀመጠው ሲሉ አብራርተዋል።

ይህም ክብሩን፣ ሞራሉን እና ጥቅሙን በማይነካ መልኩ እንደሚፈፀም የተያዘው መርሃ ግብር ማስቀመጡን ጠቁመዋል።

“ይህም ምንም ክፋት የለውም፤ ህግ የማስያዝ ነው፤ ጊዜ የሰጠነውም ሌላ ችግር ስለነበረ ነው” ብለዋል፡፡

ሁሉም ክልሎችን ባሳተፈ መልኩ ጥናቱ ላይ ለረጅም ጊዜ ምክክር ተደርጎ የተወሰነ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ይህንን ጥናት ሊያስፈፅም የሚችል ብሄራዊ ኮሚቴ መቋቋም አለበት ተብሎ መቋቋሙን በማከልም ይህም የተደረገው አፈፃፀም ላይ ጉድለት እንዳይኖር በማሰብ መሆኑን ገልፀዋል።

ሙሉ ቃላቸውን ያድምጡ።

Exit mobile version