ምክራችን አንድ ነው!

የአማራ ብሄረተኞች አልሰማ አሉን እንጂ ምክራችን አንድ ነው። ለአንድ አምስት አመት ድምጻችሁን አጥፉ ፣ ክልሉን የሞቀ የኢኮኖሚ እንቅቃሴ ማዕከል አድርጉት። ባህርዳርን የምስራቅ አፍሪካ pharmaceutical ማዕከል ፣ ደብረብርሃንን የጨሰ የኢንዱስትሪ ከተማ ፣ ጎንደርን የባህልና ቱርዝም መናኸሪያ ደሴና ኮምቦልቻን ባለ 5G የቴክኖሎጂ ማዕከሎች አድርጓቸው። ከማህበራዊ ሚዲያ ዕብደት ውጡ ፣ ያኔ እንወደዋለን የምትሉት ህዝብ ቀና ብሎ ይሄዳል ከኢትዮጵያም ባለፈ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማህበረ ኢኮኖሚ ይኖራችኃል። ክላሽ ያነገበ ልዩ ሀይል ቢበዛ ከጦርነት ያላቀ ፋይዳ የለውም

Opinon by Samson Michailovich

፩. የልዩ ሀይሎች ሪፎርምን በተመለከተ

የልዩ ሀይል ምስረታን ኢህገመንግስታዊነት ፣ የግጭት እሳት ለኳሽነትንና ሀገር አውዳሚነትን ከማንም ቀድሞ ሲሞግት የነበረው ቀድሞ የአንድነት ሀይል ( ነፍሱን ይማረውና) ስንል እንጠራው የነበረው ፖለቲካዊ ስብስብ ነው። ይሄን መታገያ አጃንዳ ፣ የፖሊሲ አቋም መንግስት ሲቀበለውና ተግባራዊ ሲያደርገው ” እምቢዮ ” ይሉት ኩርፊያ ምን የሚሉት የልጆች ጨዋታ ነው ? ይሄ አስቂኝ ሁነት የኢህአፓ ወጣቶች የ ‘ መሬት ላራሹ ‘ ጥያቄን በመሪነት ለአመታት አንስተው ሲታገሉ ቆይተው ደርግ የመሬት አዋጅን ሲያወጣ ኩርፊያ ውስጥ ከገቡበት ሁናቴ ጋር ይመሳሰልብኛል።

የክልል ልዩ ሀይሎችን በሪፍሮም የማፍረሱ ሂደት እንከን ካለበት እነዚያን ጉድለቶች አንስቶ መሞገት ትክክል ነው። ከዚያ ባለፈ ለአመታት ስታነሳው የነበረን የፖሊሲ ጉዳይ ሌላ የፖሊቲካ ቡድን ወይም ገዥው ፓርቲ ስለተቀበለው አቋምህን ቀልብሰህ ተቃውሞ ውስጥ መግባት አስቂኝ የፖለቲካ ጨዋታ ነው።

፪ . የልዩ ሀይል ሪፎርም ከአማራ ክልል ውጪ ሌላ ስፍራ አልተጀመረም የሚለው መከራከሪያ

እኔ እስከማውቀው የልዩ ሀይል ሪፎርም የመጀመሪያው አፈጻጸም ደረጃ ላይ ነው ያለው። በየክልሉ ለሚገኙ የልዩ ሀይል አባላት የሪፎርሙ አላማ ተግልጾላቸዋል ፣ ከባባድ ትጥቆች ቆጠራና መሰብሰብ ተጀምሯል አባላቱም ፎርም መሙላት ጀምረዋል። ይሄ ተግባር አማራ ክልል ውስጥ ብቻ ነው እየተካሄደ ያለው የሚል አካል መረጃ አቅርቦ መሟገት ብቻ ነው ያለበት። ምክትል ኢታማዦር ሹሙ እንዳሉት ግን መንግስት ” አንዱን ክልል በሀይል አሳብጦ ሌላውን አኮስሶ የመምራት ፍላጎት የለውም ” ።

See also  የወያኔ አጀንዳ አሻሻጭ የመንፈስ ልጆች ዘመቻ..

፫. የአማራ ልዩ ሀይል የህወሃት ታጣቂ ጦሩን ሳያወርድ ትጥቅ አይፈታም የሚለው መከራከሪያ።
ይሄ መከራከሪያ ከሁሉም ጭብጦች ውሀ የማያነሳው ነው። ሲጀመር የህወሃት ወረራ የተመከተው ይበልጡኑ በሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ነው። የአማራ ልዩ ሀይል ለብቻው ህወሃትን ማደብየት የሚችል ቢሆን ኖሮ የህወሃት ታጣቂ ደብረብርሃን ድረስ ሊደርስ ባልቻለ ነበር። እንዲህ አይነቱ ፍሬ አልባ መከራከሪያ ከኦሮሚያ ፣ ደቡብ ፣ ሶማሌ ወዘተ ወደ ክልሉ ዘምተው የነበሩትን ልዩ ሀይሎች መስዋዕትነትም ይክዳል። እውነቱን ለሚያውቁ በጦርነቱ ወቅት የአማራ ሆስፒታሎች ከሁሉም ክልሎች በመጡ የጦር ሰራዊት ቁስለኞች እንደተሞሉ አብጥረው ያውቀታል። ፋኖና የአማራ ልዩ ሀይል አማራን ከህወሃት ወረራ ታደጉ የሚለው ተረክ ባዶ የፌቡ ጨዋታ ነው።

ከዚህ ባለፈ እጅግ አስቂኙ ነገር መከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ያሉት ከአማራ ብሄር የሚዉለዱ ጄነራሎችና ባለሌላ ማዕረግ የሰራዊቱ አባላት በወነግ አገልጋይነት መፈረጃቸውና የልዩ ሀይል አባላት የክልሉ ታማኝ ጠባቂ ሆነው መታሰባቸው ነው።

የአማራ ክልል ከህወሃትም ይሁን ሌሎች የብሄር ስብስቦች ጥቃት ከለላ የሚሻ ከሆነ ሀላፊነት መውሰድ ያለበት የፌዴራል መንግስቱ ፣ መከላከያ ሰራዊቱ ነው። ልዩ ሀይል ያድነኛል የሚል መከራከሪያ ለሌላ ዙር የብሄር ሀይሎች ጡንቻ መፈርጠምና መፈታተሽ ከመዘጋጀት ያለፈ ፋይዳ የለውም።

፬. እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ መከራከሪያዎች :

በዚህ ሰሞን ከአማራ ብሄረተኞችም ሆነ ጭምብላም የአንድነት ሰባኪዎች የምንሰማቸው በርካታ እርስ በራስ የሚጣረሱ መከራከሩያዎች አሉ። ከእነዚህ አንዱ ለ 35 ዙር ሰለጠነ የሚሉት የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ሰራዊት ብዛት ነው። ችግሩ ይሄን ብለው ጥቂት ሳይቆዩ የኦሮሚያን ልዩ ሀይልም አፍርሶ የፌዴራል ሰራዉቱን አቅም የሚገነባውን ፖሊሲ ሲቃወሙ ይታያል። ሁለት ወዶ !

አንዳንዶች ደግሞ ፌዴራል መንግስቱ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ አማሮች ጥበቃ ሊያደርግላቸው አልቻለም ሲሉ ይከሳሉ። ይህ እውነት ነው። ነገር ግን የፌዴራል መንግስቱ ለዜጎቹ በቂ ጠበቃ ማድረግ የሚችለው ጡንቻው ሲበረታ ፣የመቆጣጠር አቅሙ ሲጠንክር መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ታዲያ የክልል ልዩ ሀይሎችን አፍርሶ የፌዴራል ሰራዊቱን አቅም የሚያሳድገው ሪፎርም ለምን ተቃውሞ ተነሳበት ?

See also  ከሰላም ስምምነቱ በኋላ.. የትህነግ የፊት ደጀኖች ምን እያሉን ነው?!

ለማጠቃለል :
የአማራ ህዝብ ጥቅም በተደራጀ ልዩ ሀይል አይጠበቅም። ያ ቢሆን ኖሮ ታንክና ሮኬት የታጠቀው የትግራይ ልዩ ሀይል የትግራይ ህዝብን ጥቅም ባስጠበቀ ነበር። ብሄሮችም እንበል የፖለቲካ ማህበረሰቦች ጥቅማቸው የሚጠበቀው በስለጠነ የፖለቲካ ድርድር ፣ ሙግት እና ሁሉን በእኩልነት በሚመለከቱ ህጋዊ ቀመሮች ነው።

የብሄር ፖለቲከኞች ህዝብን ሞቢላይዝ ያደርግልናል ብለው ካሰቡ እምቦጭንም ይሁን የኮየ ፈጬ ህንጻዎች የፖለቲካ አጀንዳ ከማድረግ አይመለሱም። የአንድነት ሀይል ነኝ ፣ ኢትዮጵያውያንን በዕኩልነት ለማየት እሞክራለሁ የሚል ግለሰብ ይሁን ስብስብ ግን የፖሊሲ ጉዳዮችን ከጊዜያዊ ሆይ ሆይታና ህዝባዊ ቅቡልነት አርቆ ሊመለከት ይገባል። የክልል ልዩ ሀይሎች ይፍረሱ የሚለው አጀንዳ ይቀነቀን የነበረው አቢይ አህመድ የሚባል ሰው ከማወቃችን ብዙ መንፈቆች በፊት ነው። ይህንን መርህ ዛሬ አቢይ ቢገዛው የለም አልጣመኝም ብሎ ጀርባ መስጠት የህጻናት ጫወታ ነው።

ብሄር ዘለል የፖለቲካ ህሳቤ ውስጥ ላለ ስብስብ የአማራም የትግራይንም ህዝብ በእኩል አይን ሊመለከት ይገባል። የትግራይን ህዝብ ስንል ክልሉ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችንም ይጨምራል። የአማራ ክልል ልዩ ሀይል እድሜ ልኩን ህዝቡን ከወረራ ጠባቂ አድርጎ ማሰብ ስህተት የሚሆነው እዚህ ላይ ነው። የአማራና ትግራይ ፖለቲከኞች ልዩነቶቻቸውን ከነፍጥና ልዩ ሀይል ባለፈ በውይይት መፍታት ይቻላሉ። ቢያንስ ቢያንስ በብሄር ፖለቲካ የማናምነው ወገኖች civil dialogue ብቸኛ የፖለቲካው ክፍተቶች መሙያና ማስተካከያ መንገድ እንዲሆን መሟገት አለብን።

ብዙው አስመሳይ አማራ አፍቃሪ ልዩ ሀይሉ ይፍረስ ስትለው ጸረ አማራ የሚል ታፔላ ሊለጥፍልህ ይፈልጋል። በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ወጣቱን መሳሪያ አንጋች ማድረግ የሚሻ ሰው ቆምኩለት ለሚለው ህዝብ ድንቁርናን ከማምጣት ያለፈ ፋይዳ የለውም። የአማራ ብሄረተኞች አልሰማ አሉን እንጂ ምክራችን አንድ ነው። ለአንድ አምስት አመት ድምጻችሁን አጥፉ ፣ ክልሉን የሞቀ የኢኮኖሚ እንቅቃሴ ማዕከል አድርጉት። ባህርዳርን የምስራቅ አፍሪካ pharmaceutical ማዕከል ፣ ደብረብርሃንን የጨሰ የኢንዱስትሪ ከተማ ፣ ጎንደርን የባህልና ቱርዝም መናኸሪያ ደሴና ኮምቦልቻን ባለ 5G የቴክኖሎጂ ማዕከሎች አድርጓቸው። ከማህበራዊ ሚዲያ ዕብደት ውጡ ፣ ያኔ እንወደዋለን የምትሉት ህዝብ ቀና ብሎ ይሄዳል ከኢትዮጵያም ባለፈ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማህበረ ኢኮኖሚ ይኖራችኃል። ክላሽ ያነገበ ልዩ ሀይል ቢበዛ ከጦርነት ያላቀ ፋይዳ የለውም።

See also  እንግዲህ ገጥመናል ...

Leave a Reply