የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባሏ ሊመሰገኑ ነው

የመጀመሪያዋ ሴት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የነበሩት ወይዘሮ ማርታ ገብረጻድቅ ዛሬ፣ ሚያዝያ 2 2015 አ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አዳራሽ እውቅና ያገኛሉ፡፡

ወይዘሮ ማርታ በአሁኑ ሰአት የ90 አመት እናት ናቸው፡፡

ዛሬ ከቀኑ 8:00 ሰአት ጀምሮ የወይዘሮ ማርታ የቅርብ ወዳጆች እና ምሁራን በሚታደሙበት የምስጋና መርሀ-ግብር ይደረግላቸዋል፡፡

ወይዘሮ ማርታ ገብረጻድቅ በግላቸው ወደ ሃገረ- አሜሪካ ሄደው በአዳምስ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ የያዙና በ1951አ.ም የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን በመቀላቀል ለ9 አመት ያገለገሉ ናቸው፡፡

በወቅቱ ጠ/ሚኒስትር የነበሩት ጸሐፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በሰጡት ጥቆማ መሰረት፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነዋል።

ለወይዘሮ ማርታ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ኃላፊነቱ እጅግ ከባድ ቢሆንም የበርካታ ዓመታት ልምድ ካላቸው ሰዎች ጋር አብረው መስራታቸው ደግሞ መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡

የደርግ መንግስት ሲመጣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልነታቸውን በመልቀቅ ለስደት ተዳረጉ፡፡

አሜሪካ ገብተው ብዙም ሳይቆዩ ከባለቤታቸው ከአቶ ደመቀ ተክለወልድና ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በአፍሪካ ሃገራት ያሉ ስደተኞችን በመደገፍ ላይ ያተኮረውን ፕሮጀክት ሜርሲን ጀመሩ።

በፕሮጀክት ሜርሲ ለስደተኞች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ከማቅረብ ባለፈም ወደ ተለያዩ ሃገራት እንዲሻገሩ የማመቻቸት ስራን ይሰሩ ነበር። በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ማላዊ፣ ጊኒ፣ ጂቡቲና አይቮሪኮስት የነበሩ ስደተኞች ተጠቃሚ ሆነዋል።

የፕሮጀክቱን አቅጣጫ በማስፋትም በኢትዮጵያ የማህበረሰብ ልማት ስራ ላይ ተሰማርተዋል። በዋናነት በቡታጅራ የተንቦ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታል፣የጤና ሳይንስ ኮሌጅና የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት ከፍተው ስራ አስጀምረዋል።

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን

See also  ጌራሲሞቭ የፑቲን ቀኝ እጅና የጦርነት ዶክትሪን ባለቤት

Leave a Reply