የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የግሎባል ሴኩሪቲ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኖ ተመረጠ

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የግሎባል ሴኩሪቲ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኖ ተመርጧል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቻይና ናንጂንግ ከተማ ሚያዚያ 3 እና 4 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው የዓለም አቀፍ የህዝብ ደህንነት ትብብር ፎረም ላይ ነው የግሎባል ሴኩሪቲ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኖ የተመረጠው፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል÷ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት የተመራው ልዑካን ቡድን በቻይና ናንጂንግና በቤጂንግ ከተማ ሲደርስ ደማቅ ፖሊሳዊ አቀባበል ተደርጎለታል።

በዓለም አቀፍ የህዝብ ደህንነት ትብብር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ፎረም ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ÷ የቴክኖሎጂ እድገት የዓለም አቀፋዊ ትስስር ከመፍጠሩም ባሻገር መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች አሉት ብለዋል፡፡

የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከል የሚቻለው በጋራ በመስራት ሲሆን÷ ኢትዮጵያ በአፍሪካ፣ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የህዝቦችን ደህንነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።

ፎረሙ የዓለም አቀፍ ግጭቶችንና ዋና መንስኤዎችን ለማስወገድ፣ የዓለም አቀፍ ደህንነት አስተዳደርን ለማሻሻል እና የፀጥታ ማስከበር የጋራ ጥረቶችን ለማበረታታት እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ ከቫለንሲ ኡርኪዛ የኢንተርፖል ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የብራዚልየፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር እና የዓለም አቀፍ የሕግ ትብብር ኃላፊ ጋር ባደረጉት የጎንዮሽ ውይይት አደገኛ ዕፅ ዝውውርን ለመከላከል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ሚያዝያ 5 ቀን 2015 ዓ.ም በቤጂንግ ተገኝተው ከአቻቸው ከቻይና መንግስት ምክር ቤት አባል እና የህዝብ ደህንነት ሚኒስትር ዋንግ ዢአሆንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የኢትዮጵያን እና የቻይናን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመዋጋት እና የፀጥታ አካላትን የህግ ማስከበር አቅምን በመገንባት ረገድ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ አብሮ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የቻይና ፖሊስ አዛዥና የህዝብ ደህንነት ሚኒስትር ዋንግ ዢአሆንግ በበኩላቸው÷ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የወዳጅነት ትብብር ለማጠናከር ትልቅ ትኩረት እንደምትሰጥ አንስተዋል፡፡

See also  ከዜጎቻቸው ለአስር በመቶ ያህሉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት የሰጡ የአፍሪካ አገራት 15 ናቸው

የሁለቱን ሀገራት የህግ ማስከበርና የፀጥታ አጋርነት ለማጠናከር እንዲሁም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት እንደምትፈልግ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስን በሰው ኃይል የአቅም ግንባታ፣ ለቴክኖሎጂ እና ለፖሊስ ሥራ የሚያገለግሉ የተለያዩ ትጥቆችን በከፍተኛ ደረጃ ለማገዝም ቃል መግባታቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሁለትዮሽ የህግ አስከባሪ ማዕከል እንዲገነባ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች ተስማምተው ለዚህም ጥናትና አስፈላጊው ዝግጅት ለማድረግ የጋራ ኮሚቴ እንዲደራጅ እንዲሁም የሁለቱ አቻ የፖሊስ ተቋማት የጋራ መግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡

OBN

Leave a Reply