Site icon ETHIOREVIEW

በህገ-ወጥ መንገድ በከፍተኛ ደረጃ የተከማቸ የጨው ምርት ተያዘ

የዋጋ ንረትን ለማባባስ በህገ-ወጥ መንገድ በከፍተኛ ደረጃ የተከማቸ የጨው ምርት መያዙን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አሰታወቀ።

በጉዳዩ የተጠረጠረው አቶ ታደለ አበባው ደስታ የተባለ ግለሰብ ሆን ብሎ በጨው ምርት ገበያ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት በህገ-ወጥ መንገድ በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ቃሊቲ ገብርኤል አካባቢ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ኃይሌ ጋርመንት እና በሸገር ከተማ ገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በሚገኙ ትላልቅ መጋዘኖች ከህዝብ የተሰጠውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ጋር ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የጨው ምርት ክምችት ተይዟል፡፡

በጥቆማው መሠረት በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸው የጨው ምርት የዋጋ ንረት ለማስከተል ሆን ተብሎ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ፣ በአጠቃላይ ከፍተኛ ታክስ ማጭበርበር ጋር የተገናኙ በርካታ መረጃዎች የቀረቡ ስለሆነ፣ የጨው ምርቱና ክምችቱ ለተጠቃሚው ጤና ተስማሚ ባልሆነ መልኩ ስለመዘጋጀቱ የተገኘው መረጃ የሚያስረዳ ስለሆነ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው አንዳንድ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በጥቅም ትስስር የተገናኙ በመሆኑን የቀረበው መረጃ የሚያመላክት በመሆኑ በተወሰደው ህጋዊ እርምጃ የተጠቀሰው ከፍተኛ ህገ-ወጥ የጨው ክምችት ሊያዝ የቻለ ሲሆን ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች ላይም ጠንካራ ምርመራ የቀጠለ መሆኑን የምርመራ ቡድኑ ገልፃል፡፡

ህብረተሰቡ ለሰጠው ጥቆማ እና ላደረገው ትብብር የምርመራ ቡድኑ ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረበ በቀጣይም የሚደርስበትን የምርመራ ውጤት ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጾ ኅብረተሰቡ የተለመደውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version