የዓለም ወታደራዊ ወጪ ከ2 ነጥብ 24 ትሪሊዮን ዶላር በለጠ

ይህም የምንጊዜውም ከፍተኛ ወጪ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ የወሰደችው ወታደራዊ እርምጃ በመላው አውሮፓ ወታደራዊ ወጪን እንዲጨምር አድርጓል ነው የተባለው፡፡

የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት (SIPRI) ዓለም ዐቀፋዊ ወታደራዊ ወጪን አስመልክቶ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ ለስምንት ተከታታይ ዓመታት የዓለም ወታደራዊ ወጪ ጭማሪ አሳይቷል ብሏል።

13 በመቶ ጭማሪ የተመዘገበውም በአውሮፓ ሲሆን ባለፉት 30 ዓመታት ከተመዘገበው ከፍተኛው እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

ለወታዳራዊ ወጪው ጭማሪ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ጋር የተገናኘ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ሌሎች ሀገራትም ለሩሲያ ስጋቶች ምላሽ ለመስጠት ወታደራዊ ወጪን ከፍ ማድረጋቸውም በምክንያትነት ተነስቷል።

የተቋሙ ወታደራዊ ወጪ እና የጦር መሳሪያዎች ምርት ፕሮግራም ከፍተኛ ተመራማሪ ናን ቲያን “በቅርብ ዓመታት ውስጥ ያለው የዓለም አቀፍ ወታደራዊ ወጪ ቀጣይነት ያለው ጭማሪ ማሳየቱ ይበልጥ አስተማማኝ ባልሆነ ዓለም ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳይ ምልክት ነው ብለዋል።

“አገራት እየተባባሰ ላለው የፀጥታ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት ከሰላም ይልቅ ወታደራዊ እርምጃን እያጠናከሩ ነው፤ ይህም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊሻሻል እንደማይችል እገምታለሁ ሲል አመልክተዋል፡፡

ሩሲያ ክሬሚያን ከቀላቀለችበት ከ2014 ጀምሮ ብዙ አገራት ወታደራዊ ወጪያቸውን ከእጥፍ በላይ አሳድገዋል።

በ2022 በዩክሬን ወታደራዊ ወጪ ከስድስት እጥፍ በላይ ወደ 44 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል፡፡

በ2022 የሩሲያ ወታደራዊ ወጪ በግምት 9.2 በመቶ ያደገ ሲሆን ይህ በገንዘብ ሲሰላ ወደ 86.4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይደርሳል።

አሜሪካም በ2022 እስከ 877 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓ ተመላክቷል፡፡ በዚህም ከዓለም አቀፍ ወታደራዊ ወጪ 39 በመቶው የዓለም ትልቁን ወታደራዊ ወጪ የምትመድብ ሀገር አድርጓታል።

ጭማሪው በአብዛኛው የተንቀሳቀሰው “ለዩክሬን በተሰጠው ታይቶ በማይታወቅ ወታደራዊ የገንዘብ ዕርዳታ” ነውም ተብሏል።

ቻይና እ.ኤ.አ. በ2022 292 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ በመመደብ ከዓለም ሁለተኛዋ ትልቅ ወታደራዊ ወጪ ያወጣች ሀገር ሆና ቆይታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጃፓን እ.ኤ.አ. በ2022 ለውትድርና 46 ቢሊዮን ዶላር ያወጣች ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ5.9 በመቶ እድገት አሳይቷል። SIPRI ከ1960 ጀምሮ ከፍተኛው የጃፓን ወታደራዊ ወጪ መሆኑን በሪፖርቱ አመላክቷል።

See also  ኢትዮጵያ በግዛቷ የሚያልፉ ሳተላይቶችን መረጃ መቀበል የሚያስችል ቴክኖሎጂ መግጠሟን ገለጸች

ጃፓን እና ቻይና 575 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ወጪን በመመደብ በእስያ ካሉ ሀገራት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ SIPRI ሪፖርት በክልሉ ያለው ወታደራዊ ወጪ ከ1989 ጀምሮ እየጨመረ መጥቷል።

ቤጂንግ የግዛቷ አካል እንደሆነች በምታስባት ታይዋን ደሴት ላይ በምስራቅ እስያ ውጥረት ነግሷል።

ጃፓን እና ቻይና ከታይዋን በስተሰሜን ምስራቅ በምትገኘው በሴንካኩ ወይም በዲያዮዩ ደሴቶች ላይ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።

ይህም ዓለም አስተማማኝ ባልሆነ የደህንነት ችግር መተብተቧን የሚያመላክት ነው ተብሏል።

በትዕግስት ዘላለም ዋልታ ኢንፎርሜሽን

Leave a Reply