“ለሰላም ስምምነቱ መጽናት በቁርጠኝነት እንሰራለን”

በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት በማጠናከር ለሰላም ስምምነቱ መጽናት በቁርጠኝነት እንሰራለን-የአፋርና አማራ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች

ኦቢኤን ሚያዝያ 16/2015 – በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት በማጠናከር ለሰላም ስምምነቱ መጽናት በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ የአፋርና አማራ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች ገለጹ፡፡

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሂደቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና በሚል መሪ ሃሳብ የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር በፊንፊኔ ተከናውኗል።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለስምምነቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት በቀጣይ የሰላም ስምምነቱን በህዝብ ለህዝብ ትስስር ማጽናት እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመራና የሁሉንም ክልሎች ርዕሳነ- መስተዳደሮች ያካተተ ቡድን በተያዘው ሳምንት ወደ መቀሌ እንደሚያቀና ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለና የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ በቀጣይ የሰላም ስምምነቱን ይበልጥ ለማጽናት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ነው የገለጹት፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጦርነቱ ኢትዮጵያን በብዙ ዋጋ እንዳስከፈላት ነው ያብራሩት፡፡

ልዩነቶችን በግጭትና ጦርነት ለመፍታት የሚደረጉ ሙከራዎች ውጤታቸው የጋራ ጥፋት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የሰላም ስምምነቱ እንዲጸና ሁሉም ዜጋ በባለቤትነት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የሚያስፈልገው በኢትዮጵያዊ አንድነት ስር የዜጎችን ወንድማማችነት ትስስር ማጠናከር ነው ብለዋል፡፡

የአማራና የትግራይ ህዝብ ለዘመናት አብሮ የኖረ፤ በባህል እንዲሁም በኢኮኖሚ የተሳሳረ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተር ይልቃል፤ በቀጣይ ይህንን አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

የሚያጋጥሙ ልዩነቶችንም በውይይትና በመነጋጋር ብቻ ለመፍታት እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለው አብሮነት ጠንካራ ነው፤ ይህን ማስቀጠል ደግሞ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡

ሰላም ኢትዮጵያውያንን በማስተሳሰር የተሻለ ነገን በጋራ እንዲገነቡ የሚያስችል ቁልፍ መሳሪያ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የሰላም ስምምነቱ ይዞት የመጣውን ብሩህ ተስፋ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት አለብን ነው ያሉት፡፡

See also  በሕገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከ12 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተያዘ

ሁሉም ዜጋ ጦርነቱ በኢትዮጵያ ላይ ካስከተለብን ጉዳት በሚገባ በመማር “ጦርነት ይብቃ” ማለት እንዳለበትም ርዕሳነ መስተዳደሮቹ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ በጦርነቱ የባከኑ ጊዜያትን በልማት ለማካካስ በጋራ መነሳት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነት በማጠናከር ለሰላም ስምምነቱ መጽናት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ርዕሳነ መስተዳደሮቹ መረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Leave a Reply