Site icon ETHIOREVIEW

የሙስና ወንጀል ክስ አቋርጣለሁ ያለው በሌብነት ክስ ተመሰረተበት

በፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል በሌብነት በሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተበት።

በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እየታየ በእስር ላይ ያለውን ተከሳሽ ክሱ እንዲቋረጥና ከእስር እንዲፈታ አደርጋለሁ በማለት 2 ሚሊዮን ብር ጠይቆ ከዚህ ውስጥ 310 ሺ ብር በተቀበለው ተከሳሽ ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተበት

በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት እየታየ በእስር ላይ ያለውን ተከሳሽ ክሱ እንዲቋረጥና ከእስር እንዲፈታ አደርጋለሁ በማለት 2 ሚሊዮን ብር በመጠየቅ ከዚህ ውስጥ በቅድሚያ 310 ሺ ብር በተቀበለው ተከሳሽ ላይ በፈፀመው በግል ተሰሚነት መነገድ የሙስና ወንጀል እና ህገ-ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ ተመሰረተበት፡፡

ሳሙኤል ታደሰ የተባለው ተከሳሽ በ1ኛ ክሱ ላይ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 29(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ፤ በ2ኛ ክሱ ላይ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁ. 780/2005 አንቀፅ 29 (1)(ሀ) ላይ የተደገገውን በመተላለፍ ሁለት ክስ ቀርቦበታል፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ በ1ኛ ክሱ ላይ በአንድ የመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ብቻ ሊሰጥ የሚችለውን ልዩ መብት ወይም ጥቅም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ፀረ-ሙስና ወንጀል ችሎት እየታየ በእስር ላይ ያለውን አለማየሁ ሶሬ የተባለን ተከሳሽ ከእስር ለማስፈታት ቀኑ በውል ባልታወቀ የካቲት ወር 2015 ዓ.ም አራዳ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ፒያሳ ጎንደር ሆቴል ውስጥ 1ኛ እና 2ኛ የዓቃቤ ህግ ምስክሮችን ካገኛቸው በኋላ እኔ ሁሉንም አቃቤ ህጎችንና ሃላፊዎችን ስለማውቅ እነሱን አናግሬ የተከሳሽ ክስ እንዲቋረጥና ከእስር እንዲፈታ አደርጋለሁ በማለት እና ይህንን ተሰሚነቱን ለማሳየት በማሰብ 1ኛ ምስክርን በፍትህ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ቢሮ ድረስ ወስዷል፤

በዚሁ የካቲት ወር 2015 ዓ.ም ቦሌ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 1ኛ ምስክርን በማግኘት ለጉዳዩ ማስፈፀሚያ 2 ሚሊዮን ብር እንደሚከፍሉት በመንገር ከዚህ ገንዘብ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን ከዐቃቤ ህግ ቢሮ ለማውጣት በቅድሚያ 350 ሺ ብር ክፈል በማለት ከጠየቀው በኋላ፤ በ1ኛ ምስክር ስም በተከፈተ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር በተለያዩ 3 ቀናት 180 ሺ ብር በባንክ እዲተላለፍለት አስድርጓል።

በመቀጠልም ተሰሚነቱን የበለጠ ለማሳየት በማሰብ 1ኛ ምስክርን ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ድረስ በመውሰድና ሰነዶችን ወደ ዐቃቤ ህግ ቢሮ አስገብቻለሁ ጉዳዩ ለውሳኔ እንዲቀርብ ተጨማሪ 150 ሺ ብር ያስፈልጋል በማለት ከዚሁ ምስክር ጋር በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው ደሳለኝ ሆቴል ገንዘቡን ይዞ እንዲመጣ ተቀጣጥረው ከተገናኙ በኋላ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ80 ሺ ብር ቼክ እና 50 ሺ ብር ጥሬ ገንዘብ ከተቀበለ በኋላ ሊያመልጥ ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል።

በአጠቃላይ ተከሳሽ እንዳለው ያስመሰለውን ተሰሚነት በመጠቀም በአንድ የመንግስት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ሰራተኛ ብቻ ሊሰጥ የሚችለውን ልዩ መብት ወይም ጥቅም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ጠቅላላ 310 ሺ ብር የተቀበለ በመሆኑ በፈፀመው በግል ተሰሚነት መነገድ የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡

በ2ኛ ክሱ ላይ ተከሳሽ ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባዉ የንብረቱን ህገ- ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን ወይም ከወንጀል ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ከላይ በ1ኛ ክስ በተጠቀሰው መልኩ ከጠየቀው ገንዘብ ውስጥ ከ1ኛ ምስክር ገቢ የተደረገለትን ገንዘብ ህገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ እና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ገንዘቡን በሌላ ግለሰብ የባንክ ሂሳብ ያስተላለፈ በመሆኑ፤ በአጠቃላይ ተከሳሽ ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የንብረቱን ህገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን ወይም ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ በፈፀመው ህገ-ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

ጉዳዩን ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ተከሳሽ በተገኘበት ክሱ በችሎት የተነበበለት ሲሆን በዋስትና ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሚያዚያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል።

Exit mobile version