እንትን ምስጥን እበላለሁ ብሎ ሲነሳ …

መሰረቱ ኤርትራ ላይ የሆነና ራሱን Center for research and documentation ማእከል ምርምርን ስነዳን ግዱሳት ሃገራዉያን ሲል የሚጠራ አካል ” ቀናት ያለፈበት ሥጋ ከመሽተት አይድንም” ሲል በትግርኛ ባሰራጨው ጽሁፍ “እንጠንቀቅ” ሲል በአሽሙር ስጋቱን ገልጿል። ለጽሁፉ ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን ለግንዛቤ ያህል ጸሃፊው በሚቀጥለው ጥናታቸው አክለው እንዲያዩት አንዳንድ አሳብ ለማካፈል ነው። ከዛም ራሳቸውን በነቀዝ መስለው ምስጥን ሊስለቅጡ የተመኙትን ምኞት እንዲመረመሩ ለማሳሰብም ነው።

ምኞቴ – ኢሳያስ በመጨረሻው ዘመናቸው ላይ ናቸው። ዕድሜ ሰጥቷቸዋል። በክብር ቀሪውን እድሜያቸውን እርቅና ሰላም አውርደው፣ በሌሎች አገሮች በተለይም ኢትዮጵያ ላይ የሚጎነጉኑትን አቁመው ቢያልፉ ምኞቴ ነው። ጦርነት ቀርቶ ተራ መቀያየም ለኤርትራም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንዳችም አይፈይድም። የኤርትራና የትግራይ ጎረቤት ህዝብም የጸብ ታሪኩን በእርቅ ደምድሞ በመልካም ጉርብትና እንዲኖሩ ነው። አለያ ግን ከላይ በርዕስ እንድተባለው ነው። ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር መመለሷ የማይቀር ነውና እሱንም አስቦ በጋር ጥቅም ሰላም አውርዶ መኖር ይበጃል። ምክርም ምኞትም ነው። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ምስጥ መንግስት ነው ያለው። ምስጥ መንግስት ደግሞ 120 ሚሊዮን ህዝብ ይዞ በነቀዝ አይበላም። በታሪክም ነቀዝ ምስጥን በልቶ አያውቅም። ነቀዝና ምስጥ ከጽሃፊው አሳብና ገለጻ ይተወሰዱ የእብጠት እሳቤዎች ናቸው

ኢሳያስ አፉወርቂ ይህ ነው የሚባል ፖሊሲ ባይኖራቸውም ብዙ ጊዜ አሳባቸውንና የሚያራምዱትን ጉዳይ በተዘዋዋሪ ማስተላለፍ የተካኑበት ስልት ነው። ከዚ አንጻር ጽሁፉ አሽሙርና ጥሬ እይታ ቢሆንም የሻዕቢያ አቋም ስለመሆኑ ምድር ላይም ያሉ ጉዳዩች ይመስክራሉ።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን ግርታና የልዩ ሃይል መስከምን አስምልክቶ የተፈጠረውን ክፍተት ሻዕቢያ እየነዳው እንደሆነ በግልጽ የሚያሳየው ይህ ጽሁፍ ከአሽሙር በላይ ያሳበቀው ጉዳይ ይጎላል። ጉዳዩም ኢሳያስ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መንግስት መፍራታቸውን የሚያጋልጥ ነው። “ቀናት ያለፈበት ሥጋ ከመሽተት አይድንም” ሲሉ ጸሃፊው ኢትዮጵያን ከመሽተት ጋር አያይዘው ሲያቀርቡ ያለ ምርጫ፣ ያለ ህገመንግስት፣ ያለ ተቃዋሚና ነጻ ፕሬስ፣ በከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት የገለማውን፣ አምራች ሃይሎችን ገፍቶ አገሪቱን ባዶ ያስቀረውን፣ አሮጊትና አዛውንቶች ሳይቀሩ የስደት ካምፕ ተመጽዋች ያደረገውን፣ በየ እስር ቤቱ ነጽሃንን አጉሮ የቆረጠመና እየቆረጠመ ያለውን፣ የሃይማኖትና እምነት ነጻነትን አፍኖ የያዘውን የኢሳያስን መንግስት መልካም መዓዛ በንፅር አላሳየም። በርካታ ቤተሰቦቹ፣ ዘመዶቹ፣ ወገኖቹና መንደረተኞቹ እንዳሻቸው ነግደው፣ ሰርተውና ተዝናንተው ሳይሸማቀቁ የሚኖሩባትን ኢትዮጵያ በሸተተ ስጋ የመስለው የ”ጥናት ማዕከል” ኢትዮጵያንና ኤርትራን እንደ አገር ለማወዳደር የሚከረና የቀድሞ የድንጋይ ዘመን ላይ የተቸከለ አጥጪ ሆኖብኛል። ችግሩ ግን እሱ ላይ ሳይሆን የእኛዎቹ ወዶ ገቦች ጋር ስለሆነ ልለፈው።

በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የሚሆነውን ሁሉ የሚመራውና ስምሪቱን የሚቆጣጠረው ማን ነው? ይህን ጥያቄ መርምሮ አቋም መያዝ ለድጋፍም ለተቃውሞውም ምክንያታዊ ያደረጋል። ልብ እንበል በኢትዮጵያ የሚመረቱትን አመጾችና በመናበብ የሚያሰራጩትን ማን ነው የሚደጉማቸው? እንዴትስ ነው ከአገራቸው ይልቅ ለሌሎች ምቾት ባሪያ ለመሆን የመረጡት? ሚዲያ፣ የሚዲያ ስራ፣ የሚዲያ መርህ እንዲህ በአፍጢሙ ተተክሎ አገሪቱ ላይ የጥፋት ዲዲቲ የሚረጨው ምን አይነት “አንድ ኢትዮጵያ” እንድትገነባ ተፈልጎ ይሆን? …. የሚሉት ጥያቄዎች መልስ እያገኙ ነው።

ትህነግ የአገር መከላከያን በክህደት ሲያርድ ድጋፍ የሰጠው ሻእቢያ በወጉ ተመስግኗል። ተወድሷል። መንግስትም “ውለታ እንረሳም” ኢትዮጵያን ታኮ ማንም ኤርትራን እንዲነካ እንደማይፈቅድ በይፋ አስታውቋል። ጽሁፉ የክረምት ቀለብ የሆነውን ጎመን ” ጊዜ ባሳለፈ ተመጻደቁበት” ሲል ከምስጋና ስትዘረፍ ዝም ከማለት በላይ ኢትዮጵያ ምን እንድታደርግ እንደተፈለገ ግልጽ አላደረገም። ቡና ኤክስፖርት ለማድረግ ታስቦ ከሆነ በቅርቡ የቅባት ዕህል ዝርፊያው እንደሚቆም ከመጠቆም ውጭ የምለው የለም።

See also  ሕልም ሳይኖራቸው ፍቺ የሚጠይቁ ወበከንቱዎች

ጽሁፉ ተጀምሮ እስኪያልቅ በትግራይ ሰላም መስፈኑ ያሰጋው፣ ትግራይን ልክ የኢትዮጵያ አካል አድርጎ ማየት ያልፈለገ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጋር አንዳችም ውል እንዳይኖረው የሚመኝ፣ እንደ አቂሚቲ ጨላማ ውስጥ ያለ የትልቅነት አባዜ የወለደው ወፈፌነት ነው። ህዝብን ስለማከብር ወርጄ ብዙ አልልም ግን በደፈናው “አንመጣጠንም”፣ በብዙ መልኩ መለያየታችንን በቅርቡ አዲስ አበባ ደርሰው የተመለሱትን አዛውንት ካቢኔዎችህን ጠይቅ። አናሎግ ዝመን ላይ ተቀርቅሮ መዘላበድ ትህነግን እንዳደርገው ከመሆን ውጭ ሌላ እድል አያመጣም።

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ እንዲህ እንዳሁኑ ተንፍሶ በቸርኬው ሳይሄድ የችግሮች ሁሉ ጠማቂና የሴራዎች ሁሉ መጠንሰሻ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ጎን ለጎን አንዳችም ጥርጥር የሌለው ጉዳይ ቢኖር ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ በሻዕቢያ አመራሩን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያን የሚያደማ ሃይል ማሰልጠን፣ ማብቃትና አግቶ መደረደሪያ ማድረጉን ለአንዳችም ቀን አቁመው አያውቁም። ሚሌኒየም አዳራሽ ” ኢሱ” እየተባሉ ሲወደሱ እንኳን ኤርትራ ውስጥ ኢትዮጵያን ሲፈለግ ቀውስ ላይ የሚጥል ሃይል ያሰለጥኑ ነበር። ይህ ሚስጢር ሳይሆን ገሃድ ነው። ለሰላም ሲባል እንጂ ኢሳያስ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ልጆች ላይ ያደረጉት፣ ያስደረጉት እንዲሁ በቀላሉ አይዘነጋም። እድሜ ለበለዓሉ ግርማ ሻቢያና ጉም አንድ መሆናቸውን አስተምሮን አልፏል።


ህወሓት፤ የኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ ጠላት!

በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ብሮንዊን ብሩቶን ይህ ለብዙዎች ደብዝዞ የሚታያቸውን ጉዳይ ግሩም ትንታኔ በመስጠት Ethiopia and Eritrea Have a Common Enemy በሚል ርዕስ ተሟጋች መጣጥፍ አቅርበዋል። ይህ ማስረጃዎችን በመደርደርና በማጣቀስ በቀረበ ጽሁፍ ላይ ጸሃፊዋ አስረግጠው የሚያቀርቡት ሙግት ህወሃት የኢትዮጵያና የኤርትራ የጋራ ስጋት መሆኑን ነው። ስጋት የሚሆነበትን ምክንያት በመዘርዘር የቀረበውን ይህንን መነበብ የሚገባውን ትንታኔ ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ ወደ አማርኛ መልሶ እንደሚከተለው አቅርቦታል። ትርጉሙ ቀጥተኛና ተዛማጅ የትርጉም ስልትን የተከተለ መሆኑ እንዲታወቅልን እንፈልጋለን


ብራውኒ ብሩቶ እንዳሉት ኤርትራና ኢትዮጵያ የጋራ ጠላት ስለነበራቸው ነው ለውጡን ተከትሎ ኢሳያስ ተንደርድረው አዲስ አበባ የገቡት። እቅፍና አበባ፣ አድናቆት የነጎደላቸውም ለዚሁ ነው። ፈቃድ ያገኙት ትህነግ ባዶ ቤት አድርጎን በክህደት መንፈስ ሲመራን ስለነበር ነው። ለነገሩ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ሊሎችም የፖለቲካ ተኩላዎች ተግተልትለው ገብተው መከራ ሆነውብን ነበር!! … ተንደርድረው ወደ ጦርነቱ ሲሰምጡም አርንጓዴ የበራላቸው በዚህ ስሜት ነው። ለሳቸውም ቀን ተገጣጠመና ትህነግን ወገሩት። እንዳሻቸው ጋለቡበት። ስጋት መሆኑ ቀርቶ ዋጋ ቢስ እንደሆነ ቢገልጹም በስተመጨረሻ አኮረፉ። የጸሃፊው ፍላጎትም ይህንኑ ማለት ነው። እዚህ ላይ ግልጽ ለማድረግ በመከባበር ካልተኖረ የትግራይ ህዝብ ከወገኖቹ ጋር ሆኖ ኢሳያስን ለምጉመጥመጥ አንድ ሳምንት በቂው ነው። ግን አይመከርም።

ትህነግ የሚባለው ሴረኛ ድርጅት እንዲህ ሊወላልቅ እርቅ አሻፈረኝ ብሎ በተነከረበት ጦርነት ትግራይን እንደ ክልል፣ የትግራይ ህዝብን እንደ ህዝብ ማቅ ውስጥ ከቶ፣ በመቶ ሺህ ታዳጊ አስበልቶ በእምብርክክ እርቅ ተቀብሏል። ኢሳያስ በዚህ ደረጃም ቢሆን ዕርቅ ሊደረግ እንደማይገባ አዛኝ፣ ከኢትዮጵያዊ በላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው ሰፋፊ ቃለ ምልልስ አቀረቡ። ስም መዘርዘር ባያስፈልግም የሳቸውን ቃለ ቡራኬና መመሪያ ለመቀበል አስመራ የተመላለሱና የሚመላለሱ ደገፏቸው። ልክ እንደ አንድ መልካም ስብዕና እንዳለው ታላቅ መሪ ኢትዮጵያ እንድተሰማቸው በስምና በአድራሻ የሚታወቁት ሁሉ ጮሁ። ቃላቸውን እየተረጎሙ ህዝብ ላይ ጭነው ከኢትዮጵያ መሪዎች በላይ እሳቸው እንዲወደሱ ሰበኩ።

See also  ሻዕቢያና ትህነግ - ሰሞኑን ይህ ሆነ

ትህነግ ሳይደቅ ሃብት ያከማቸውን ሃብት እየረጨ በየክልሉ ነጻ አውጪ ሲያደራጅ፣ በሚዲያ ማዕበል አየሩን አጥኖ በፕሮፓጋንዳ ሲያጦዘን፣ ማጅራታቸን ከሚሸከመው በላይ ችግር ጠንቶብን ስለነበር ዝም አልን እንጂ ሻዕቢያ ጦርነቱን አስታኮ ከባድ መሳሪያ ዘርፏል። ከትግራይ ቢሆንም የኢትዮጵያዊያንን ሃብት አግዟል። ቀምቷል። ያላደርገው የለም። ከሁሉም በላይ ኦነግን በትግራይ በእግር፣ በአየር ደግሞ በሱዳን ሲያጓጉዝ በምትኩ ፈንዲሻ በትኖ አዲስ ምልምሎችን አስገብቷል። አሁንም እያስገባ እንደሆነ እየተገለጸ ነው። ኤርትራ ድረስ እየሄዱ ቡራኬና ጻድቅ የሚወስዱ የኢትዮጵያ “ልጆች” አሉ። ስም መዘርዘሩ አሁን ላይ ስለማይመረጥ በደፈናው እገልጸዋለሁ እንጂ ነገሩ ግልጽ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው።

ሻዕቢያ ትህነግን አሰልጥኖ፣ አስታጥቆና አብቅቶ ኢትዮጵያ ላይ ከጫነበት ጊዜ አንስቶ ይህ ጽሁፍ እስከታተመበት ቀንና ሰዓት ድረስ ሻዕቢያ ኢትዮጵያን የሚያውክ ሃይል ማደራጀቱን አላቆመም። ጦርነቱን ተገን አድርጎም በሚያሰማራቸው አማካይነት ንግድ ውስጥ ገብቷል። በዚሁ የኮንትሮባንድ ንግድ ያበዱ ህዝብ እንዲናከስ አጀንዳ እያመረቱ በቅባት እህል ንግድ ዶላር እየተራጩ ነው። በቅርቡ መንግስት ይፋ ያደርገዋል ተብሎ የሚጠበቅ ከፍተኛ የህገወጥ ንግድና የውጭ ምንዛሬ አጣቢዎች ሰንሰለት ተይዟል። ይህን ልተወውና ወደ ዋናው ጉዳይ ለመለስ።

ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሰው ልጅ፣ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ቁሳዊ ኪሳራ ያስከተለ፣ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ምስኪን ዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆነው ጦርነት መቆሙና በስላም መጠናቀቁ ለም ፕሬዚዳንት ኢሳያስን አናደደ? በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር መካከል የመከላከያ ሰራዊት ከሰፈረ ኢሳያስ ትህነግ እንዴት ስጋታቸው ሊሆን ይችላል? ስለምንስ ኢሳያስ ይህን ቀላል ሂሳብ እያወቁ ” እኔ አላማረኝም” የሚለውን ዘፈን መረጡ? “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉን “ጋዜጠኞች” እንዴትና በምን ስሌት ከአገራቸው ሰላም በላይ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ስጋት ጭንቀታቸው ሆነ? ጭንቀት ብቻ አይደለም እንዴት በዚህ ደረጃ ማሰቢያቸው ላላ?

ኢሳያስ አፉወርቂ ኢትዮጵያን ማፈራረስ፣ ወይም እንዳትረጋጋ አጀንዳ መስጠት አጀንዳቸው እንደሆነ ገና በእንጭጩ ወቅት መናገራቸውን እድሜ ለዩቲዩብ ለታሪክ አስቀምጦታል። በተግባርም ነጻ አውጪ ሲያደራጁ መኖራቸው ገሃድ ስለሆነ ክርክር የለውም። ይህ የሚያስማማ ከሆነ የቀደመውን ብንተወውም አሁን ላይ ከላይ በመግቢያዬ እንዳልኩት ማን ነው የሚያተራምሰን? ማን ነው አጀንዳ የሚቀርጽልን? ይህንኑ አጀንዳ የሚያከፋፍሉንስ ምን ያጨሱ ወገኖች ናቸው? እንዲህ አቅል አሳጥቶ የደሃን ልጅ ለማስበላት የደም ደወል የሚነቀንቁ ወገኖቻችን ጤነኞች ናቸው? ቢያንስ “ጦርነት አብቅቷል መሳሪያ አውርዱ” ከተባለ በሁዋላ ኤርትራ በረሃ የተረሸኑ ወገኖቻችን ደም አይጮህም? 120 ሚሊዮን ህዝብ ላይ በደባ የቆለፉና ባህር አልባ ላደረጉ መሪ ይህን ያህል ጭራ መቁላትስ ይገባል?

አሁን ላይ ላለፉት አራት ዓመታት የተረጩት አበሳዎች እየተሰበሰቡ ነው። ትህነግ በ”በቃኝ” ለሰላም እጁን ሲሰጥ ፍልፍሎቹም ከየክልሉ ወደ ሰላም እያመሩ ነው። ኦነግም ሰላም እንደሚሻል በገሃድ አስታውቆ ንግግር ላይ ነው። ይህ እረፍት የሚሰጥ ዜና ትህነግ እስኪያቅለሸልሸው ድረስ ተቀጥቅጦ ልክ ሲገባ የተገኘ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ከሚታዩ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች አንጻር ጠልቀን እንድንመረምር የሚገፉ ጉዳዮች አሉ።

See also  24 ሠዓታት በወታደር ህይወት - ምስክርነት ክፍል ሶስት - "የፍልሚያ ቀናት ተናፈቀ"

ከህግ ማስከበሩ ዘመቻ ጎን ለጎን አስደማሚ በሚባል ደረጃ ኢትዮጵያ የአየር፣ የባህርና የምድር ሃይሏን ገንብታለች። እነ ሻለቃ ዳዊት ቀደም ሲል በሴራ የሚከሽፍ መፍንቅለ መንግስት አዘጋጅተው የአገሪቱን ጦር መሪ አልባ እንዳደረጉት አይነት ጨዋታ እንደማይታሰብ የበርካቶች ዕምነት ነው። ይልቁኑም በተቃራኒው ልክ ትህነግ እስኪያጥወለውለው እንድተቀጠቀጠ ሁሉ በሌሎች ማናቸውን ዓይነት ኢትዮጵያ ላይ ሴራ የሚጎነጉኑ በተመሳሳይ ሊቀምሱ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። ውጊያ ባይመረጥም፣ በአፍ ሌላ በግብር ሌላ እየሆኑ በደርግ ዘመን እንደተደረገው አይነት ጨዋታ ዛሬ ላይ ተራ ሞኝነት እንደሆነ አሰላለፉን የሚያውቁ እየመሰከሩ ነው።

ኢሳያስና መለስ የተጣሉት በኢኮኖሚ ጉዳይና ኢሳያስ ኢትዮጵያ ላይ የበላይ ልሁን ከሚል መነሻው የማይታወቅ ዕብለት ሳቢያ ነው። ትህነግ አቅሙን ስቶ ዕብለት ውስጥ ገብቶ እንድተከሰከሰው ሁሉ ዛሬም ኢሳያስ የትህነግን ታሪክ ከመድገም ሌላ አማራጭ ሊኖራቸው አይችልምና መከራን ራሳቸው ላይ ባይደግሱ ይመረጣል።

ሰሞኑንን “እንዘጋጅ” የሚሉ ድምጾች ከወደ ሻዕቢያ ወዳጆች እየተሰራጨ ነው። የኔትወርክ አባል የሆኑት ደግሞ እየተረጎሙ እያሰራጩ ነው። በአማራ ክልል የተፈጠረውን ክፍተት የመጠቀም አቋም እንዳለም እየነገሩን ነው። አማራ ከአገሩ ይልቅ ለኢሳይስ ስጋት ማብረጃ እንዲሆን የሚሰብኩ እንደሚሉት ሳይሆን፣ የሻዕቢያ አለቅላቂ የሆኑት እነ ሻለቃ ዳዊት እንደሚቀደዱት ሳይሆን መሬት ላይ ያለው ሃቅ ሌላ ነው።

ሻዕቢያ በተደጋጋሚ መስመር እየሳተ ነው። በሃይማኖት ስም ነውጥ ለማስነሳት ሲሰራ ነበረበት፣ የዓለም አብያተክርስቲያናት ማህበር ጣልቃ እንዲገባ ግብጽ ድረስ ሄዶ አሲሯል። በአማራ በኩል ህግ ከሚፈቅደው ውጪ በህቡዕ ከተደራጁ አካላት ጋር ገጥሟል። አስልጥኖም ጦርነት እንዲለኮስና እርስ በርስ እንድንጋደል ነዳጅ እየረጨ እንደሆነ መረጃው አለኝ። እኔ ብቻ ሳልሆን በርካቶች ያውቁታል። ይህ አካሄድ የትግራይ ጦርነት እየተካሄደ ሳለ ቢሆን ኖሮ አደጋ ነበረው። አሁን ግን አያዋጣምና ለሰላማዊ ዜጎች የቀእደመው ዓይነት ፈተና ከማሳቀፉ ውጭ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። ወደፊት ማስረጃ ጠቅሼ የምመለስበት ጉዳይ ይሆናል።

የተዘጋው ድንበር ሲከፈት ያየነው የህዝብ አንድነትና ፍቅር እንዲጎለብት በቀናነት መስራቱ ያዋጣል። ምንም ያማያውቁ ምስኪኖችን መርዳትና ማሻሻል ባይቻል እንኳን ሰላማቸውን፣ ባሻቸው ቦታ ከመረጡት ጎረቤቶቻቸው ጋር አቭሮ መኖርን መንፈግ እንደ ቀድሞው በዝምታ የሚታለፍ አይሆንም። የኢትዮጵያን የኤርትራ ህዝብ በፍቅር የሚዋደድ፣ አብሮ የኖረ፣ ሴራ የነጠለው ግን ያልተለያየ ህዝብ ነውና ለሌላ መከራ እንዳይደረግ ጥንቃቄ እንዲወሰድ ለማሳሰብ ይህን ጽፌያለሁ።

ኢትዮጵያን በብስባሽ መስሎ ራስን በመስታዋት ፊቷን ስታይ አንበሳ እንደመሰለችው ድመት መገመት በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውጤቱ ሌላ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ነቀዝ ምስጥን አይበላውም። ነቀዝ ምስጥን እበላለሁ ብሎ ሲነሳ ያኔ ነቅዟል። ከመንቀዝ ቀደም ሲል እንደተጀመረው ግንኙነትን አድሶ፣ መልካም ወዳጅነትን አበልጽጎ አሰብን እስከመሻረክ የሚደርስ ትሥሥር መፍጠር ይሻላል። የማይቀርም ነውና!! ከዚያም በላይ ምርጥ የኤርትራን ልሂቃን ወደ መሪነት አምጥቶ በክብር ማለፍ ደግ ነው። አዲስ ሃይል በአዲስ እሳቤ የሴራ ሽመናውን አምክኖ ተያይዞ መሻገር የሚችል ይሆናልና!!

ሰለሞን ጎርፍነህ – ደቡብ አፍሪካ

ዝግጅት ክፍሉ – ጽሁፉብ የጸሃፊውን አስተሳብ ብቻ የሚወክል ነው። የተለየ አስተያየት በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ ለሚያቀርቡ መድረኩ ክፈት ነው

Leave a Reply