“የመንግስትና ኦነግ ድርድር በሰላም የድል ዜና ለሕዝብ ይፋ ይሆናል”

ብዙም ለሚዲያ ፍጆታ የሚሆን መረጃ የማይወጣበት የመንግስትና የኦነግ የሰላም ድርድር በሰላም የድል ዜና ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ተሰማ። በተለይ ለኢትዮ 12 መረጃ የሰጡ የጉዳይ ቅርብ ሰዎች እንዳሉት የሰላም ንግግሩ ከሚጠበቀው በላይ በመልካም ሁኔታ እየሄደ ነው። ተደራዳሪዎቹ አቅማቸውን፣ የአካባቢውንና የዓለምን አሁንዊ ምልከታ በማገናዘብ መላዘብ ማሳየታቸው ንግግሩን ቀና ስሜት አላብሶታል።

መንግስት ከትህነግ ጋር ያደረገውን ውጊያ በድል የሚቋጭበት ደረጃ ከደረሰ በሁዋላ የሰላም አማራጭ ስምምነት መካሄዱ፣ ከስምምነቱም በሁዋላ እንቅፋት ጉዳይ አለማጋጠሙ ጠብ መንጃ ላነሱ ሁሉ መነቃቃት መፍጠሩን በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የፖለቲካ፣ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዴኦዬ መናገራቸውን ቪኦኤ አመልክቷል።

ኅብረቱ በአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ፣ ዛሬ በበይነ መረብ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል፣ በታንዛኒያ ይደረጋል የተባለው ድርድር ተጀምሮ እንደኾነና ሒደቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ ለተጠየቁት ቀጥተኛ ምላሽ እንዳልሰጡም ተመክቷል።

በታንዛንያ የዛንዚባር ደሴት እየተካሄደ ስላለው ንግግር ዝርዝሩን መናገር እንደማይፈልጉ የገለጹልን እንዳሉት የኦነግና የመንግስት ድርድር ምን አልባትም ትጥቅ አንስተው ለመታገል ጫካ የሚገቡ ድርጅቶች ማክተሚያ ስለሚሆን ስጋት የፈጠረባቸው የሩቅና የቅርብ ጠላቶች ድርድሩን ልዩ መልክ እያስያዙት እንደሆነ ጠቁመዋል።

“እመኑ” ሲሉ እንዳስታወቁት ምንም ምንም ይበል የሰላም ዜና ከዛንዚባር ይሰማል። ቀደም ሲል የመነጋግወሪያ አጀንዳዎችን ከማበጀት አኳያ ብዙ ስራ መሰራቱ ለንግግሩ መቀላጠፍ እገዛ ማድረጉንም ገልጸው ” አጀንዳ ቀረሳ ላይ እዚህ ግባ የሚባል ጊዜ የፈጀ ንትርክ አልነበረም” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል በኩል መንግስት የሚስማማበትን ውሳኔ ለመቀበል ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛነቱ ስላለ የሰላም አማራጭ ንግግሩ በውጤት እንዲጠናቀቅ እድል የሚሰጥ እንደሆነ፣ ምድር ላይ ያለው ሁኔታም መንግስት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የበላይነት የያዘበትና ጎረቤት አገራትም ከመንግስት ጋር የሚቆሙበት አግባብ እየጎላ መሄድ፣ ከዚህም በላይ አሜሪካና አውሮፓ ህዝብረት መንግስትን በይፋ መደገፍ የጀመሩበት ወቅት መሆኑ ሌላው መገጣጠም እንደሆነ እነዚሁ ወገኖሽ አመልክተዋል።

See also  የሸኔን የጥፋት ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በዋነነት ” አሁን ላይ የኦሮሞ ህዝብ ሊሎች ላይ ተኩሶ የሚያስፈጽመው አጀንዳ የሌለ በመሆኑ የሰላም ወይይቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ፖለቲካ ድርድር እንደቀየረው ተረድተናል” ብለዋል።

ቪኦኤ የሚከተለውን ዘግቧል።

 “የፕሪቶሪያው ስምምነት ተኣምራዊ ስምምነት እየተባለ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ላለፉት ስድስት ወራት ምንም ዐይነት ጥይት አልተተኮሰም፡፡ በመኾኑም ስምምነቱ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ትልቅ መነሣሣት ይኾናል ብዬ አምናለኹ፤” ሲሉም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል በታንዛኒያ ይደረጋል የተባለው የሰላም ድርድር፣ ትላንት ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚጀመር፣ ሁለቱም አካላት ያረጋገጡ ቢኾንም፣ ድርድሩ በርግጥም ስለመጀመር አለመጀመሩ እስከ አሁን በይፋ የታወቀ ነገር የለም፡፡
በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የፖለቲካ፣ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዴኦዬ፣ ኅብረቱ በአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ፣ ዛሬ በበይነ መረብ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል፣ በታንዛኒያ ይደረጋል የተባለው ድርድር ተጀምሮ እንደኾነና ሒደቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ኾኖም ኮሚሽነሩ፣ ለጥያቄው በሰጡት አስተያየት፣ ችግሩን በሰላም ድርድር ለመፍታት የተጀመረው ጥረት የሚደነቅ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ “ግባችን እ.አ.አ. በ2030 የመሣሪያ ድምፆችን ኹሉ ዝም ማሰኘትና ኹሉም ግጭቶች እንዲቆሙ ማድረግ ነው፤” ያሉት ኮሚሽነሩ፣ “ስለዚኽ በኢትዮጵያም ይኹን በሌላ ማንኛውም የኅብረቱ አባል ሀገር፣ ለሕዝቦቻችን ጥቅም ሲባል፣ እንዲሁም ዐቅማችንን ሁሉ የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን በማድረግ ተግባር ላይ ማዋል ይቻል ዘንድ፣ ግጭቶችን ለመፍታት የሚወሰዱ ርምጃዎች የሚደነቁ ናቸው፤” ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው አፍሪካ ተምሳሌት እንደኾነ የጠቀሱት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት፣ በሀገሪቱ ለሚንቀሳቀሱ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች መነሣሣትን እንደሚፈጥር ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ “የፕሪቶሪያው ስምምነት ተኣምራዊ ስምምነት እየተባለ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ላለፉት ስድስት ወራት ምንም ዐይነት ጥይት አልተተኮሰም፡፡ በመኾኑም ስምምነቱ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ትልቅ መነሣሣት ይኾናል ብዬ አምናለኹ፤” ሲሉም ተናግረዋል።

See also  አብን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደመረጠ ተደርጎ የሚሰራጭ መረጃ ሐሰት መኾኑን ገለጸ

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቃል አቀባይ ኑር መሐሙድ ሼኽ ደግሞ፣ በጽሑፍ በሰጡን አጭር ምላሽ፣ “እኛ የምናውቀው ንግግሩን የመጀመሩ ሒደት የላቀ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ንግግሮቹ በታንዛኒያ እንደሚደረጉ ነው፤” ብለዋል፡፡ “ሒደቱ በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የሚመራ ነው፤” ሲሉ በጽሑፋቸው ገልጸዋል።
የኢጋድ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ ስለ ኹኔታው “ጥሩ ግንዛቤ” እንዳላቸውና “በፓርቲዎቹ ከተፈለጉ ድጋፍ ለማድረግ” እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ በታንዛኒያ እንደሚነጋገሩ ከመታወቁ ባለፈ፣ ተደራዳሪ ወገኖች በማን እንደሚወከሉ፣ ስለ አደራዳሪዎች ማንነት፣ እንዲሁም ስለ ድርድሩ ሒደት፣ መንግሥት እና ታጣቂው ቡድኑም ኾኑ የታንዛንያ ባለሥልጣናት፣ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ መቆጠባቸውን ሮይተርስ አመልክቷል።
የአሜሪካ ድምፅ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል፣ አስተያየት ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
በአሶሺየትድ ፕሬስ የተጠቀሱት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ግን፣ “ለዋናው ድርድር መንገድ የሚጠርግ” ያሉት “የመጀመሪያ ውይይት መጀመሩን” ጠቅሰዋል፡፡ “የአሁኑ ንግግር ትኩረት፥ መተማመንን መፍጠር እና አቋሞችን ግልጽ ማድረግ ነው፤” ማለታቸውን፣ እንዲሁም ኖርዌይ እና ኬንያ፣ በዚኽ ሳምንት የሚደረገውን ንግግርም እንደሚያሸማግሉ መግለጻቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ በዘገባው ጠቅሷል፡፡
በታንዛኒያዋ የዛንዚባር ደሴት በሚካሔደው ድርድር የኢትዮጵያን መንግሥት በመወከል ከሚሳተፉት መካከል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴንና የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ እንደሚገኙበት፣ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሁለት ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ተወካዮችን ማንነት በተመለከተ ግን፣ እስከ አሁን በዘገባዎች አልተጠቀሰም፡፡

Leave a Reply