በአማራ ክልል “በተደራጀ የሽብር ተግባርና ባለስልጣናት ግድያ” ተሳትፈዋል በተባሉ ላይ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ

ፍርድ ቤቱ ዳዊት በጋሻውና ቴድሮስ አስፋው የሽብር ወንጀል ተሳትፎ አላቸው ተብሎ በቀረበባቸው የጥርጣሬ መነሻ ላይ ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ፈቀደ።

አዲስ አበባ ሚያዝያ 20/2015(ኢዜአ)፦ፍርድ ቤቱ ዳዊት በጋሻውና ቴድሮስ አስፋው የሽብር ወንጀል ተሳትፎ አላቸው ተብሎ በቀረበባቸው የጥርጣሬ መነሻ ላይ ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ተፈቀደ።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1 ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ተጠርጣሪዎቹ በሽብር ወንጀል ተሳትፎ አላቸው ሲል ፖሊስ ያቀረበውን የጥርጣሬ መነሻ ተመልክቶ ነው ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ የፈቀደው።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩት ከሙያ ተግባራቸው ጋር ሳይሆን አመፅ በማስነሳት እና በአማራ ክልል አመራሮች ላይ ጥቃት ለማድረስ ከተደራጀው የሽብር ቡድን ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ ስላላቸው ነው በማለት ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።

በተለይም የፌዴራል ስርዓትን ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ አግባብ በኃይል እርምጃ ለመቀየር በማሰብ፣ በተደራጀ የሚዲያ ክንፍ በመሳተፍ በአማራ ክልል አመራሮች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም የሎጀስቲክና የፋይናንስ ገቢ የማሰባሰብ ተግባር ላይ ተሳትፎ አላቸው ሲል ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።

ተጠርጣሪ ዳዊት በጋሻውን በሚመለከት በሌላ መዝገብ በምርመራ ላይ ከሚገኙት ከዶ/ር ወንደሰን አሰፋ ጋር የሽብር የተግባር ግንኙነት እንዳለቸው የሚያሳይ የፎረንሲክ ማስረጃ ማግኘቱን ጠቅሶ መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ” ገልጿል።

በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ ”ተጠርጣሪዎቹ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ስራዎችን በተቀናጀ መንገድ ሲሰሩ እንደነበር እና አንዱ ህዝብ አፈናቃይና ተጠቃሚ አንዱን ህዝብ ደግሞ ተጓጂ አድርገው በማንፀባረቅ በህዝቦች መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር አስቀድመው እቅስቃሴ ማድረጋቸውን የሚያመላክቱ የመነሻ ማስረጃዎችን ማግኘቱን አብራርቷል።

በዚህ መልኩ ተጠርጣሪዎቹ ባደረጉት የተደራጀ የሽብር ወንጀል ተግባር ተሳትፎ የሰው ህይወት መጥፋቱን ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንም መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል።

በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ሀገርን ማፍረስ ስውር ሴራዎች ያሉበት የሽብር የወንጀል ውስጥ በመሳተፍ በአመራሮች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ከተዋቀሩ 3 ክንፎች መካከል የሚዲያ ክንፍ አንዱ መሆኑን የጠቀሰው ፖሊስ በዚህ በሚዲያ ክንፍ ውስጥ ሙያን ሽፋን በማድረግ በሽብር ተግባር የተሳትፎ እንቅስቃሴያቸውን የሚያሳይ ማስረጃ መሰብሰቡን ጠቅሶ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።።

See also  የሐረሪ የምርጫ ሂደት በተመለከተ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ

በዚህ መልኩ የተጀመሩ የምርመራ ስራዎችን በሰውና በሰነድ አደራጅቶ ለማቅረብ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል። የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው ተጠርጣሪዎቹ ሊጠየቁ የሚገባው በመገናኛ ብዙሀን አዋጅ እንጂ በሽብር ወንጀል አዋጁ ሊሆን አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል። የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ የተጠረጠሩት ከሚዲያ የሙያ ተግባራቸው ጋር ሳይሆን አመፅ በማስነሳት እና በአማራ ክልል አመራሮች ላይ ጥቃት ለማድረስ ከተደራጀው የሽብር ቡድን ጋር በቀጥታ ባላቸው ተሳትፎ ነው ሲል መልስ ሰጥቷል።

በተጨማሪም የሰው ህይወት የጠፋበት የሽብር ወንጀል ተግባር የተሳተፉ በመሆኑ ሊጠየቁ የሚገባው የሽብር ወንጀልን ለመከላከል በወጣው በሽብር አዋጅ 1176/2012 አንቀጽ 39 ነው ሲል ተከራክሯል።

አጠቃላይ ክርክሩን የተመለከቱት ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ዳኛው ተጠርጣሪዎቹ ከተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል አንጻር የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ለመመልከት ፍርድ ቤቱ ስልጣን እንዳለው አብራርተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የሰው ህይወት በጠፋበት በሽብር ወንጀል መጠርጠራቸውን በራሱ የዋስትና መብት የሚያሰጥ አደለም በማለት ለጊዜው የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርገዋል።

ከወንጀሉ ወሰስብስብነት አንጻር ተጨማሪ የምርመራ ስራ ማከናወን አስፈላጊነትን በማመን ለፖሊስ የ14 ቀን የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

Leave a Reply