የ13 ዓመቱ ታዳጊ 66 ተማሪዎችን የያዘ አውቶብስ ሊገጥመው ከነበረ ከባድ አደጋ ታደገ

የ13 ዓመቱ አሜሪካዊ ታዳጊ በወሰደው ፈጣን እርምጃ ራሱን እና 66 የትምህርት ቤት ጓደኞቹን የከፋ ሊሆን ከሚችል አደጋ አተረፈ።

አጋጣሚው የተከሰተው በአሜሪካዋ ሚችጋን ግዛት ዋረን ከተማ ውስጥ የሚገኘው ካርተር ሚድል ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አሳፍሮ የሚጓዝን የትምህርት ቤት አውቶብስን ስታሸከረክር የነበረችው ሹፌር በድንገት ራሷን በሳተችበት ጊዜ ነበር ተማሪዎቹ ለአደጋ የተጋለጡት።

በዚህ ጊዜ ከሹፌሯ አምስት ወንበሮች በኋላ ተቀምጦ የነበረው የ13 ዓመቱ ታዳጊ ዲለን ሪቭስ ከተቀመጠበት በመነሣት የአውቶብሱን መሪ ራሷን ከሳተችው አሽከርካሪ ተረክቦ ምንም አደጋ ሳያጋጥም እንዲቆም ለማድረግ ችሏል።

በአንድ ቪዲዮ ላይ የተማሪዎቹ አውቶብስ ሹፌር ለአለቆቿ ጤንነት እየተሰማት እንዳልሆነ መልዕክት ስትልክ ታይታለች።

ዲለን ሪቭስ ራሱን እና ጓደኞቹን ከከፋ አደጋ ከታደገ በኋላ በሚኖርበት ከተማ የጀግና አድናቆት እየቀረበለት ይገኛል።

የዋረን ከተማ ምክር ቤት አባል ጆናታን ላፈርቲ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ “በፈጸምከው ጀግንነት የተሞላበት ተግባር ኮርተናል!” በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ዲለን ስለፈጸመው አስደናቂ ተግባር ለመንገር ፖሊስ ለወላጆቹ በደወለበት ጊዜ፣ አባቱ ስቲቭ ሪቭስ ቀድመው የጠየቁት “ደግሞ ምን አጥፍቶ ይሆን?” የሚል ነበር።

የደወለው ፖሊስም “ምንም አላጠፋም፣ ልጅዎ ጀግና ነው” በማለት ያደረገውን በመጥቀስ አድናቆታቸውን እንደገለጹላቸው የአካባቢው መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

የታዳጊው ዲላን ሪቭስ ወላጆች ልጃቸው በፈጸመው ተግባር ኩራት የተሰማቸው ሲሆን፣ የልጃቸው ስምም በሚኖሩበት ከተማ መነጋገሪያ ሆኗል።

ETV

See also  ጥቂት አጭር መረጃዎች - የእስራኤልና የሃማስ ጦርነት

Leave a Reply