“በነዉጥና በኃይል የበለፀገ ሀገር የለም”

ኢትዮጵያ የብዝሃ አመለካከት፣ የብዝሃ ማንነትና የሌሎችም ዝንቅ መገለጫዎች አምባ ናት። ኢትየጵያ ቀለመ ብዙ ህብራዊ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት ወዘተ ያሉባት ሀገር ናት ።

ኢትዮጽያ መገንባት የጀመረችዉ የዴሞክራሲ ባህልም ኢትዮጵያን የሚመስል ፣ በሀሳብ ብዝሃነት፣ በመግባባትና በመተባበር ላይ የተመሠረተ ሁሉንም ኢትዮጽያዊያን የሚያስተናግድ የዴሞክራሲ ዓይነት ነዉ።

ለዚህ ዓይነቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ተመራጩ አቅጣጫ ደግሞ የመሀለኛዉን የፖለቲካ መንገድ መከተል ነዉ። የመሀለኛዉ የፖለቲካ መንገድ የሀሳብ ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ፣ ትብብርና ፉክክር ሚዛናቸዉን ጠብቀዉ እንዲጓዙ የሚያደርግ ነዉ። የመሀከለኛዉ የፖለቲካ መንገድ በሚዛናዊ የሀሳብ ቅኝት የሚዳኝ ነዉ።

አግላይነትና ጠቅላይነት በአስተሳሰብም ይሁን በተግባር ሚዛናቸዉን ጠብቀው እንዲራመዱ የቅኝት ልጓም ሆኖ የሚያገለግል ነዉ የመሀከለኛዉ የፖለቲካ አቅጣጫ ።
በተቃራኒዉ የፅንፈኝነት አስተሳሰብና ተግባር ‘ እኔንና የኔ ብቻ ‘ ከሚል ጠቅላይ እና አግላይ እሳቤ የሚነሳ ነዉ። አንድ ጫፍ ላይ ቆሞ የአንድ ቡድንን ወይም የአንድ አካልን ፍላጎት ለማስጠበቅ የሚሻዉ የፅንፈኝነት አባዜ መነሻው ምንም ይሁን ምን ለብዝሃ ሀሳብ፣ ለብዝሃ አመላካከትና ፍላጎት ፣ ለብዝሃ ማንነት ተገዢ ባለመሆኑ ከዴሞክራሲያዊ ዉይይትና ንግግር ይልቅ አቋራጭ መንገዶችን ይመርጣል ።

ህብረተሰቡን ለማደናገር ኮርኳሪ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።ተስፋ ሲቆርጥም ወደ ኃይል እርምጃ፣ ብጥብጥና ሁከት ይሸጋገራል ።

ፅንፈኛ ሲያሻዉ ሃይማኖትን ወይም ብሔርን ከፈለገም መንደርና ጎሳን ነጥሎ በማራገብ ሰሚ ጆሮና ልብ እንዲሁም ደጋፊ ሀይል ለማሰባሰብ ይጣጣራል።

ለማጠቃለል ያህል ፣ አሁን በምንገኝበት ዘመን ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር መሆኗን ተረድቶ ሚዛናዊ ፖለቲካን ማራመድ ተገቢ ይሆናል ። ኢትዮጵያ ከ1 መቶ ሃያ በላይ ሚሊዮን ህዝብ ያላት የሀገር ናት፣ ከዚህ ህዝብ መካከል ደግሞ አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸዉና የችግሮች ሰለባና ተጠቂ እንዳይሆኑ መጠንቀቅና ማስተዋል ያሻል።

ኢትዮጵያ ከሰባ በላይ ብሔርና ብሔረሰቦች ያሉባት ሀገር በመሆኗ የሚያግባባ የፖለቲካ መንገድን መምረጥ፣ የሀሳብና የፍላጎት ብዝሃነትን አክብሮ በመደጋገፍ መንፈስ መኖር ከሀላፊነት ስሜት የሚመነጭ አማራጭን የመከተል ጉዳይ ነዉ።

ኢትዮጵያ በለዉጥ ሽግግር ላይ ናትና ለዉጡን ከማደናቀፍ መታቀብ መልካም ነዉ።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ የብዝሃ ሀሳብ፣ የብዝሃ አመለካከት ፣ የብዝሃ ማንነት ሀገር መሆኗን ማመንና ማስናገድ መፃኢ የጋራ ዕጣ ፈንታችን ያመረ እንዲሆን ያስችላልና ከስሜትና ጠርዝ ከረገጠ አዝማሚያ መታቀብ የተሻለ ይሆናል።

See also  የሐምሌ 5/2008 ዓ.ም ማስታወሻ!

በለዉጥ ሀሳብ ታግዞ እንጂ በነዉጥና በኃይል የበለፀገ ሀገር የለምና በበለፀገ ሀሳብ ለመዳኘት እድል እንስጥ።

propserity

Leave a Reply