ፍራንኮ ቫሉታ ቢፈቀድም የዋጋ ንረቱን አልቀነሰም፤ ለምን?

በፍራንኮ ቫሉታ ዋና የሚባሉ የምግብ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ቢፈቀድም የዋጋ ንረቱን እንድተሰቀለ ነው። ባለሙያዎች የሚሉትና የሚሰጡት ዓለም ዓቀፍ ዕውነታን የተንተራሰ ምክንያት እንዳለ ሆኖ ሌብነቱም ትልቅ አስተዋጾ እንዳለው ይሰማል። ሌብነቱ ከምንዛሬ አጠባ ጀምሮ ትርፍ ማጋበስ፣ እንዲሁም ሆን ተብሎ ህዝብ ምሬት ውስጥ እንዲገባና እንዲያምጽ የማስገደጃ መሳሪያ እየተደረገ መሆኑንን የሚገልጹ አሉ።

በሁሉም መስክ ሴራ የሚንጣት ኢትዮጵያ አሁን ላይ ካሉት ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች ጋር ተዳምሮ ፣ ከውጭ የሚገባውን ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ ምርትን ሳይቀር መደበቅ፣ ማጭበርበር እንዲሁም በህገወጥ ወደ ጎረቤት አገር ማስረግ፣ ኮንትሮባንድ ላይ ማተኮር ለኑሮ ውድነቱ ቅድሚያ የሚይዙ እውነታዎች ናቸው።

የነዳጅ ድጎማ ላይ ሳይቀር በርብርብ ሲካሄድ የነበረውን ዝርፊያ ለማስቆም መንግስት የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ሲዘረጋ የተሰማው ጩኸትና ጩኸቱ እንዲስተጋባ የተደረገበት አውድ አንድ ማሳያ ነው። ይህንኑ ጩኸት እየተቀባበሉ ያሰራጩት ሚዲያዎች ዝርፊያውን እንዳላየ ከማለፍ ውጭ” ህዝብ ተሰቃየ” በሚል ድጎማው ህዝብን እንዲጠቅም አለመስራታቸው ሴራው ምን ያህል የተደራጀ እንደሆነ ያሳያል ሲሉ ሰሞኑንን አስተያየት የሰጡ አሉ።

ይህን እንደምሳሌ የሚያነሱ ከሙያዊ ትንተናው በሌላ ጎኑ ህዝብ ለራሱ ህልውና ሲል በችጋር ሊጨርሱት የተነሱ ስግብግቦች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ምክክሮች ተጠይቋል። ለአሁን አዲስ ዘመን ይህን ብሏል ከታች ያንብቡ።

መንግሥት በምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ላይ እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ለማርገብ የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን እየወሰደ ነው። በተለይም ከውጭ የሚገቡ እንደ ፓስታ፤ ማካሮኒ፤ ዱቄትና የሕፃናት ምግቦች፣ የምግብ ዘይትና የመሳሰሉት ምርቶች ላይ የነበረውን ታክስ በማንሳት ከታክስ ነፃ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በፍራንኮ ቫሉታ በኩል መፍቀዱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የእነዚህ ምግቦች ዋጋ አሁን ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ለኅብረተሰቡ ፈታኝ ሆነው እየተስተዋሉ ነው። ይህ ለምን ሆነ፤ እያጋጠመ ያለውን የዋጋ ንረት ለመግታት የመፍትሔ እርምጃዎች  እንደሚያስፈልጉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሀሳባቸውን ያጋራሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ መንግሥት በፍራንኮ ቫሉታ አማካኝነት እንደ ፓስታ፤ ማካሮኒ፣ ዱቄት፤ የሕፃናት ምግብና መሰል የፍጆታ ምርቶች ከታክስ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል። አብዛኛዎቹ ምርቶች ከውጭ የሚገቡ እንደ መሆናቸው መጠን ከታክስ ነፃ ሆነው እንዲገቡ በፍራንኮ ቫሉታ በኩል ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል። ነገር ግን በነፃ እንዲገቡ ቢደረጉም ዋጋቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ ምርቶቹ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት በውጭ ምንዛሬ አማካኝነት ከመሆኑ አንጻር የአገር ውስጥ የዋጋ ግሽበት ብቻ ሳይሆን የምርቶቹን ዋጋ መናር የሚጎዳው ከውጭ የመጣ የዋጋ ግሽበት( imported inflation) የሚባል በመሆኑ በምርቶቹ ዋጋ ላይ ጫና አሳድሯል ይላሉ።

See also  አብይ "አልቋል ... እጅ ስጡ"አሉ

የምርቶቹ በሚፈለገው መጠን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና ዋጋቸው እንዳይቀንስ ያደረገው አንዱ ምክንያት ከምንዛሪ ጋር የተያያዘ ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ የማካሮኒ፣ ፓስታና ዱቄት ምርቶች በብዛትና በስፋት በግብዓትነት የሚጠቀሙት ስንዴን ነው። ስንዴን በብዛት የሚያመርቱት አገሮች በተለምዶ የዳቦ ቅርጫት የሚባሉት ሩሲያና ዩክሬን ናቸው፤ ነገር ግን አገራቱ በጦርነት ውስጥ ያሉ በመሆናቸው የግብዓት እጥረት ተፈጥሯል። የግብዓት አቅርቦት እጥረት ደግሞ አንዱ ለዋጋ ንረት ምክንያት ይሆናል። ይህም የምርቶቹ ዋጋ በሚፈለገው ልክ እንዳይቀንስና እንዳይረጋጋ አድርጎታል ነው ያሉት።

በሌላ በኩልም ምርቶቹ አገር ውስጥ እየገቡ ቢሆንም አገር ውስጥ ያለው የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ምርቶቹን በማቅረብ ሂደት ውስጥ ዋጋቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። የጉልበት ዋጋ (labor coast) ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣበት ሂደት አለ። ይህም ያላደጉ አገሮችን ብዙ ጊዜ ዋጋቸው የሚተመነው በጉልበት ነው። በአሁኑ ወቅት ላይ ቁርስ፣ ምሳና እራት፣ እየጨመረ ከመሄዱ አንጻር የጉልበት ዋጋ መጨመሩ ዋጋቸው በተፈለገው መንገድ እንዳይሆን አድርጓል። ከትራንስፖርት ጋር የተያያዘው ዋጋ የጨመረበት ሁኔታ ስላለ ለምርቶቹ የዋጋ መናር አሉታዊ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው በምክንያትነት ያነሳሉ።

ዶክተር ዳዊት እንደሚሉት፤ የገበያ ዋጋ የሚባሉት በአገር ውስጥም ተጨባጭ በሆነ መንገድ ጭማሬ ከማሳየት አንጻር በፊት ከነበረበት ሁኔታ ዋጋው ያልቀነሰበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው። ነገር ግን በፍራንኮ ቫሉታ አማካኝነት ከታክስ ነፃ ባይገቡ ኖሮ ዋጋው ምን ያህል ይንር ነበር ብሎ ማሰብም ተገቢ ነው። ፍራንኮ ቫሉታ ባይፈቀድ የምርቶቹ ዋጋ አሁን ካለው በላይ ከ25 እስከ 50 በመቶ ጭማሪ እንደሚያሳይ መገመት ይቻላል።

ከዚህ አኳያ በተወሰነ መልኩም የዋጋ ማረጋጋት አስተዋጽኦ እንዳለው መገመት ያስችላል። ለምሳሌ ከጎረቤት ስንዴን በስፋት ወደ ውጭ ገበያ ከሚያቀርቡ እንደ ግብጽና ሱዳን የመሳሰሉ አገራት ጋር ሲነጻጸር የስንዴ ዋጋ ሲታይ  በእነዚህ አገራት ላይ ዜጎቻቸው መግዛት የማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። በኢትዮጵያ የተፈቀደው ፍራንኮ ቫሉታም በተወሰነ መልኩም ቢሆን የምርቶቹ ዋጋ ከዚያም በላይ የናረ እንዳይሆን እገዛ እንዳለው ገልጸዋል።

See also  ሩሲያና ኢትዮጵያ በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

በፍራንኮ ቫሉታ ከታክስ ነፃ በሆነ መልኩ መግባታቸው መልካም ነገር ነው የሚሉት ሌላኛው የፋይናንስና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ኃይለመስቀል ጓዙ፤ ነጋዴው ማህበረሰብ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚገዛው በጥቁር ገበያ በሚያገኘው ምንዛሬ ነው። ይህም ማለት በባንክ ያለው የአንድ ዶላር ምንዛሬ 54 ቢሆንም እነሱ አንድን ዶላር ከመቶ ብር በላይ ገዝተው ዕቃዎችን የሚያስገቡ ነጋዴዎች ይኖራሉ። ይህም ለእነዚህ ምርቶች ዋጋ መናር አንዱ ምክንያት ነው። በሌላ በኩልም ዕቃዎቹ የሚጓጓዙበት ዋጋ መጨመሩም ሌላኛው ለዋጋቸው መናር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ኃይለመስቀል፤ የምርቶቹ ከታክስ ነፃ መደረግ በተወሰነ መልኩ የዋጋ ንረቱን መቀነስ ቢያስችልም ሙሉ በሙሉ ግን ዋጋውን መቀነስ አይችልም። ምክንያቱም ምርቶቹን ከታክስ ነፃ በሆነ መንገድ እንዲያስገባ የተፈቀደለት አካል ምርቶቹን ለማስገባት ምንዛሬ በጥቁር ገበያ ሊገዛ ይችላል። የጥቁር ገበያ ዋጋን አስቦ የሚደረግ ግብይት ሊኖር ስለሚችል የምርቶቹ ዋጋ የሚጨምርበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። በፍራንኮ ቫሉታ አማካኝነተ ከታክስ ነፃ ሆነው ገቡ ማለት ገበያውን አረጋጋ ማለት አይደለም ይላሉ።

የምርቶቹን ዋጋ በሚገባ ለማረጋጋት የአቅራቢውና የፈላጊው መጠን መመጣጠን መቻል አለበት ያሉት አቶ ኃይለመስቀል፤ ይህ ካልሆነ ግን በራሱ ጊዜ የገበያ ዋጋውን እንዲንር ያደርገዋል። በተጨማሪም በዓለም ላይ ያለው የገበያ ሁኔታ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል። መንግሥት በዋጋው ላይ ጣልቃ መግባት የሚችልበት አግባብ ካለ ምርቶቹ የሚገቡበትና የሚሸጡበት ዋጋ መታወቅ አለበት ብለዋል።

በምርቶቹ ዋጋ ንረት ላይ ዋና መፍትሔው ከውጭ የሚገቡ የምግብ ሸቀጦችን በአገር ውስጥ ማምረት መቻል ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ዩክሬንና ሩሲያ ላይ ያለው መሬት ኢትዮጵያ ውስጥ አለ። እናም መካናይዝድ የሆነ የእርሻ ልማት መሥራት ያስፈልጋል። የተትረፈረፈ ምርትን ማምረት መቻል ዋናው የዋጋ ንረቱ መፍትሔ ነው። ይህ ሲሆን ዶላር በጥቁር ገበያ ገዝቶ ከውጭ የማስገባቱ ሁኔታ ይቀራል።

አገር ውስጥ ምርትን መተካት ከተቻለ የውጭ ምንዛሬ እንደ ችግር አይነሳም፤ የአገር ውስጥ ገበያን በሚገባ ማረጋጋት ያስችላል። ታዲያ ይህ እንዲሆንና ምርትን ለማምረት ወሳኙ የሰላምና ደህንነቱ የተረጋገጠ አገር መገንባት ያስፈልጋል። የሰላም ዕጦት ገበያው እንዳይረጋጋ ያደርገዋል ።

See also  በሰሜን ወሎ ትህነግ በተቆጣጠራቸው ቦታዎች የሚበላ የለም፤ ዜጎች ህይወታቸው እያለፈ ነው

እንደ አገር የተረጋጋ ሰላም ወሳኝ ነው። የሰላም እጦት ለዋጋ መናር ትልቅ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር የተረጋጋ ሰላም እንዲኖር በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየታየ ባለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሳቢያ እንደ ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ ስንዴ፣ ፓስታና ማካሮኒና የመሳሰሉ መሠረታዊ ምርቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም. መፈቀዱ ይታወሳል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2015 

Leave a Reply