የጥላቻ ንግግሮች ባለሀገሮችን ሀገር አልባ …

“ጥላቻ ሀገር ታደማለች፣ ወዳጆችን ታጋድላለች”

የበረታች ጥላቻ ሀገር አድምታለች፣ በመከራ ችንካር ወጥራ አሰቃይታለች፣ ወገንን ከወገኑ ደም አፋስሳለች፣ አጥንት አስከስክሳለች፣ አንገት አስቀልታለች፡፡ የከረረች ጥላቻ ባለሀገሮችን ሀገር አልባ አድርጋለች፣ የከረረች ጥላቻ ንጹሐንን አሰቃይታለች፣ በመከራ ቆፈን ውስጥ ይኖሩ ዘንድ ፈርዳለች፡፡

ብዙዎች በጥላቻ ጎራ ለይተው ተዋግተዋል፣ ደም ተቃብተዋል፡፡ የማይረሳ ጥቁር ታሪክ ጽፈዋል፡፡ ጥላቻ ሰላም የሆነችን ሀገር በጠብ ትንጣለች፣ በሚዋደዱት መካከል ገብታ ታቃቅራለች፡፡ ክፉ ልቦች ክፉ ነገርን ያስባሉ፣ ክፉ አንደበቶች ክፉ ነገርን ይናገራሉ፣ ክፉ እጆች ክፉ ነገርን ያደርጋሉ፣ በግፍ ንጹሐንን ያስለቅሳሉ፣ እንባ ያፈስሳሉ፣ ክፉ እግሮች ወደ ክፋት ይጓዛሉ፡፡

መልካም ልቦች መልካም ነገርን ያስባሉ፣ መልካም አንደበቶች መልካም ነገርን ይናገራሉ፣ መልካም እጆች መልካም ነገርን ያደርጋሉ፣ መልካም ልቦች ያዘነችን ልብ ያጽናናሉ፣ የምትፈስስን እንባ ያብሳሉ፣ በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና፡፡ መልካም ሰው ከመልካም ልቡ መዝገብ መልካም ነገር ይናገራል፣ ክፉ ሰው ከክፉ ልቡ መዝገብ ክፉ ነገር ይናገራል፡፡

መልካም አንደበቶች የተጣሉትን ያስታርቃሉ፣ የተለያዩትን ያገናኛሉ፣ የተራራቁትን ያቀራርባሉ፣ ቂምና በቀል የቋጠሩትን ያሽራሉ፣ መልካም አንደበቶች ሰላምን ይፈጥራሉ፡፡ ክፉ አንደበቶች የተገናኙትን ያራርቃሉ፣ በሰላም የሚኖሩትን ያጋጫሉ፣ በንጹሕ ልብ ላይ ቂምና በቀል ይቋጥራሉ፡፡

“ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሳ ትጸድቃለህና፣ በቃልህም የተነሳ ትኮነናለህ” እንደተባለ የጥላቻ ንግግሮች በበርካታ ሀገራት የከፉ ዋጋዎችን አስከፍለዋል፡፡ በዚህ ዘመን ታላቅ የታሪክ መዝገብ በሚገለጥባት ኢትዮጵያም የጥላቻ ንግግሮች ዋጋ አስከፍለዋል፤ እያስከፈሉም ነው፡፡ ታዲያ መልካም አንደበቶች ከዳር ዳር የሚሰሙበት ጊዜያት ተናፍቀዋል፡፡

በባሕርዳር ዪኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ስነ ተግባቦት መምህር አደም ጫኔ (ዶ.ር) ስለ ጥላቻ ንግግር እንዲህ ብለዋል የጥላቻ ንግግር የቡድን ማንነትን መሠረት በማድረግ ሰዎችን የሚያቆሽሽ ነው፣ በብሔራቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በባሕላቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው እና ሌሎችን መሠረት በማድረግ ሰዎችን ማንቋሸሽ፣ የሰዎችን ክብር ዝቅ ማድረግ የጥላቻ ንግግር ነው ይላሉ፡፡

ሰዎችን ዝቅ ማድረግና ማንቋሸሽ ደግሞ ማኅበራዊ መስተጋብርን ይንዳል፣ አብሮነት እና አንድነትን ያናጋል፡፡ ብዝኃ ሃይማኖት እና ባሕል ባለበት ሀገር ላይ የቡድን ማንነቶችን ማንቋሸሽ ተቻችሎ እንዳይኖር ያደርጋልም ነው ያሉኝ፡፡ በሀገር ላይ መናጋትን ይፈጥራል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳና እንዱ ሌላውን እንዲጠራጠር የሚያደርጉ የጥላቻ ንግግሮች መኖራቸውንም ነግረውኛል፡፡ እንደ ምሁሩ ገለጻ የጥላቻ ንግግሮች ማኀበራዊ አለመረጋጋትን እና ፖለቲካዊ ስብራትን ይፈጥራሉ፡፡

See also  ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የ31 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

የጥላቻ ንግግር አንዱን በአንዱ ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጥር ከማድረግ ከፍ ባለ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ግጭት ይፈጥራል፤ ግጭቱ እየሰፋ ሲሄድ ደግሞ ወደ ዘር ማጥፋት ይሸጋገራል ነው የሚሉት፡፡ በታሪክ ውስጥ እጅግ አሰቃቂ የሆኑ የዘር ማጥፋቶች ላይ ጥላቻ ንግግር አቀጣጣይ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ የዘር ማጥፋት ከመፈጠሩ አስቀድሞ የጥላቻ ንግግሮች አንደኛው በአንደኛው ላይ እንዲነሳና አንደኛው ሌላኛውን እንዲጠራጠር ያደርግ ነበር፡፡

የጥላቻ ንግግር የሰው ልጅ ምክንያታዊ አስተሳሰብ እንዳይኖረው፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ ጨካኝ የሆነ እርምጃ እንዲወስድ እንደሚያደርግም አንስተዋል፡፡

አንደኛው ብሔር በነበረው የፖለቲካ ሥርዓት በዘሬ፣ በሃይማኖቴ ተጠቅቻለሁ ብሎ ሲያስብ፣ በቡድን ማንነቶች መካከል መወነጃጀል ሲኖር፣ የተዛባ የታሪክ አረዳድ እና አተራረክ፣ የማኅበራዊ ፍትሕ መዛባት፣ ጦርነት፣ ሥር የሰደደ ድኅነትና የሥራ ዕድል አለመኖርም ለጥላቻ ንግግር መነሻዎች እንደሚሆኑ ነው የነገሩኝ፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ መረዳት እንደሚያሻ የተናገሩት ዶክተር አደም በኢትዮጵያ ውስጥ ጫፍ የረገጠ የብሔር ፖለቲካ አለ፤ ጫፍ የረገጠውን የፖለቲካ አካሄድ ማረቅና ወደ አማካኝ ማምጣት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ፖለቲካው ጫፍ የረገጠ በመሆኑ የጥላቻ ንግግሮች ከዚህ እየተነሱ እንደሚሰራጩም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካን ማስተካከል እንደሚገባትም አመላክተዋል፡፡

ሀገራት ከብሔር ፖለቲካ አጥፊነት ትምህርት ወስደው ማስተካከያ እንዲያደርጉ ያነሱት ዶክተሩ በኢትዮጵያ ውስጥም በአንድ ጊዜ ባይሆን እንኳን ቀስ በቀስ የብሔር ፖለቲካ መክሰም አለበት ነው ያሉት፡፡ ጋና ውስጥ በብሔር መደራጀት እንደማይቻል እና ሩዋንዳ ውስጥ ብሔርህ ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ክልክል መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል፡፡ ሩዋንዳውያን ከውድቀታቸው መማራቸውንም ገልጸዋል፡፡

የጥላቻ ንግግሮችን መቆጣጠር የሚያስችሉ የሕግ ማስከበሪያ ማዕቀፎች ሊኖሩ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚዲያ አጠቃቀም ላይ ክፍተቶች በመኖራቸው የጥላቻ ንግግሮች እንዲበራከቱ እንዳደረጉም ገልጸዋል፡፡ የሚዲያ አጠቃቀም ላይ ስልጠናዎች መስጠትና ግንዛቤ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት፡፡

ተቀባይነት ያላቸው ግለሰቦች ለሚናገሯቸው ንግግሮች ጥንቃቄ ማድረግ እና ንግግሮቻቸው ሊያመጡት የሚችለውን ቀውስ እየተረዱ መናገር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ የሚዲያ አማራጭ ስለተገኘ ብቻ ዝም ብሎ መናገር አይገባም፤ ዛሬ የሚደረግ ንግግር ነገ ምን ሊያመጣ እንደሚችል አስቀድሞ ማሰብ ይገባል፡፡

See also  ለግብጽና ሱዳን ሴራ - ሰርጎ ገቦችን መቆጣጠር የሚያስችል መረብ!

የጥላቻ ንግግር ዲሞክራሲን እንደሚበላም ዶክተር አደም ተናግረዋል፡፡ ሚዲያ ለአንድ ሀገር የሚሰጠውን አወንታዊ አስተዋጽዖ ማግኘት ከተፈለገ ሰከን ወደ አለ ውይይት መግባት ይገባል ነው ያሉት፡፡ የጥላቻ ንግግርን በሚያሰራጩ ሰዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉም ግልጸዋል፡፡

የጥላቻ ንግግር እንደ ሰው ሳይሆን ከሰውነት አሳንሶ ያጠፋሃል፣ ሩዋንዳዎች የክብር ሞት አልሞቱም፣ ጠመንጃና ጥይት እንዳይጨርሱ ተብለው በቆንጨራ ተገድለዋል፣ እንዳይቀበሩ ተብለው ወንዝ ላይ እንዲወረወሩ ሆነዋል፤ የጥላቻ ንግግር ከሰውነት አውርዶ እንስሳዊ ባሕሪን ያስፋፋል፣ የተጠላው አካል ከሰው ተራ ውጭ ተደርጎ ይታሰባል፣ ክብር የሌለው ሞት እንዲሞት ያደርጋል፤ ሩዋንዳውያን ከጥፋታቸው ተምረው፣ አዲስ ሀገር ለመገንባት በጥረት ላይ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ውደቀቶች መማር ይገባቸዋል፣ የተጓዝናቸው የጥፋት መንገዶች ብዙዎች ናቸው፣ ይበቃሉ፣ ከዚህ በላይ እንዳንሄድ ከሌሎች መማር እንችላለን ነው ያሉን ዶክተር አደም፡፡ የጋራና የሚያሳፍሩ ታሪኮች እንዳይኖሩ ከጥፋቶች መማር እንደሚገባም ነግረውኛል፡፡ ከመፈራረጅ፣ ከመፈናቀል፣ ከመገዳደል ታሪክ መማርና ከስህተት መንገዶች መመለስ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሀገር ናት፤ ሁሉም ሃይማኖት ጥላቻን ይጸየፋል፣ ሃይማኖቶች ፍቅርን፣ መተዛዘንን አብሮነትን ይሰብካሉ፣ መቼ ነው ይሄን የምንኖረው? ሃይማኖተኛ መሆን ዝም ብሎ የሃይማኖት ተቋም መገንባትና መፎካከር አይደለም፣ ሃይማኖተኛ ማለት አስተምህሮቱን የሚኖር ነው፤ የሃይማኖት ተቋማት ብርቱ የሆነ ሥራ መሥራት አለባቸውም ብለውኛል፡፡

“በአፍ ይጠፋሉ፣ በአፍም ይድናሉ” እንዲሉ አበው ለንግግሮቻችን ሚዛን እንስጣቸው፣ መከራ እንዳያመጡ፣ ግጭት እንዳይጠምቁ እንጠንቀቅላቸው፡፡

በታርቆ ክንዴ (አሚኮ)

Leave a Reply