“… ለሚመለከታቸሁ አካላት ሁሉ  ከግጭት መለስ ያሉ ሰላማዊ መንገዶችን እንድታስቀድሙ ጥሪ እናቀርባለን” ኢዜማ

"በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ሰላምና መረጋጋት እንደሌለና ዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንዳልቻሉ መንግሥታዊ ሥራዎች ማከናወን አስቸጋሪ ሆኖ ኅብረተሰቡ ስጋት ውስጥ እንደወደቀ በአካባቢው ከሚገኙ ከተለያዩ ምንጮች መረጃዎች ደርሰውናል።

እንደሚታወቀው ክልሉ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ገፈት ቀማሽ ነበር። ይህን ተከትሎም በድህረ ጦርነት ወቅት መሠራት ያለባቸው አያሌ ተግባራት ካለመከናወናቸው ጋር ተያይዞ የጦርነቱ ጠባሳ አሁንም የሚታይ ነው። ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላም ቢሆን በትግራይ እና በአማራ ክልል አካባቢ ላይ ያሉ የቅራኔ ቦታዎች “ምን አይነት መፍትሔ ያገኛሉ?” የሚለው ሐሳብ በክልሉ ላይ ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሮ የተለያዩ መላ ምቶች እየተሰጡ ጉዳዩን እያጦዙት እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው።

ይህ ውጥረት ባለበት ሁኔታ እንደ መልካም እርምጃ ሊወሰድና ድጋፍ ሊቸረው የሚገባውን የክልሎች ልዩ ኃይል ወደ ፌደራል ፀጥታ መዋቅር ውስጥ የመካተት ሂደት የተከናወነበት ደካማ መንገድ የፈጠረው ውዥንብር ኅብረተሰቡን ከፍተኛ ስጋትና ጥርጣሬ ውስጥ ጨምሮታል። ይባስ ብሎም በክልሉ ውስጥ በፋኖ አደረጃጀት ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እና በአማራ ብሔርተኝነት ፖለቲካ ውስጥ እጃቸውን የሚያስገቡ ኃይሎች ያገኙትን ቀዳዳ ተጠቅመው ያስተጋቡት አደገኛ ትርክት የሰው ሕይወት እስከ መቅጠፍ አድርሷል። በእነዚህ “ካልደፈረሰ አይጠራም” ባይ ኃይሎች አማካኝነትም ለሀገራቸው እና ሕዝባቸው መስዋዕትነት የከፈሉ እውነተኛ ፋኖዎች በጅምላ በፅንፈኝነት እንዲታዩ ተደርጓል። ትላንት ሀገር በጭንቅ ውስጥ ስታልፍ አብረው አጥንታቸውን ከከሰከሱ፣ ደማቸውን ካፈሰሱ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋርም ግጭቶች እንዲፈጥሩ ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ።

በአማራ ክልል ፖለቲካ ውስጥ እጃቸውን ሰድደው እንዳሻቸው የሚፈነጩ፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ በመንግስት ውስጥና ከመንግስት ውጪ ያሉ ጽንፈኛ ዘውጌ ብሔርተኛ ኃይሎች በሚያቀነቅኑት ፅንፍ የወጣ ትርክት እና እንቅስቃሴ ንፁሃን ዜጎች መከራቸውን ሊበሉ አይገባም። በክልሉ ሰላም ለማስከበር እየተንቀሳቀሰ ያለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሕዝቡ አለኝታና መከታው ሆኖ መስዋዕትነት እንደከፈለ ለማህበረሰቡ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ጽንፈኛ ዘውጌ ብሔርተኝነት አንዱ መገለጫው ብሔራዊ እሴት ያላቸው ተቋማትን በዘውግ መነፅር እያዩ ማጥላላትና ከህዝብ ጋር ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን ህዝቡ ልብ ሊል ይገባል።

See also  የኦሮሚያና የአማራ ክልል አመራሮች በዝግ እየመከሩ ነው፤ "ሁሉንም እዛው ጨርሱ ከውይይት ጀርባ ቤፊስ ቡክ አሽሙር አታራግቡ "

ከሁሉም በላይ መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት በመረዳት ጉዳዮቹን በትዕግስት እና በሆደ ሰፊነት በማስተናገድ፣ ህግና ሥርዓት እንዲከበር በመስራት ተጨማሪ የሰው ሕይወትም ሆነ የንብረት ውድመት ተከስቶ አላስፈላጊ ትርምስ እንዳይኖር የሚቻለውን ጥንቃቄ በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አንጠይቃለን።

ከጠብመንጃ አፈ ሙዝና በጉልበት የሚመጣ መፍትሔ እንደሌለ በመረዳት ሁሉም ወገኖቻችን  በሰላማዊ መንገድ  መነጋገርና መመካከር ባህል በማድረግ ችግሮችን መፍታት ይኖርብናል። መንግሥት ከህወሓት እና እራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ብሎ ከሚጠራው ኃይል ጋር የተፈጠሩ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት የሄደበትን የውይይት መንገድ ሁሌም ቅድሚያ ቢሰጠው መልካም መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን።

ይህ ማለት ግን ወንጀለኞች ያሻቸውን ሕገ ወጥ ተግባር እየፈጸሙና የሰው ሕይወት እየቀጠፉ በሰላም ስም እንዲከለሉ ሊፈቀድ ይገባል ማለት አይደለም፡፡ በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጸሙ ተራ ወንጀሎች፣ ግድያዎች እና ዝርፊያዎች ሕጋዊ በሆነ መንገድ ፍርድ የሚገባቸው እንደሆነ በፅኑ እናምናለን።

በጋዜጠኝነት፣ በአክቲቪስትነት እና በፖለቲከኛነት በንቃት የምትሳተፉ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ያላችሁ አካላት ሁሉ ሕዝብን ለበለጠ አደጋ ከሚያጋልጡ ተግባራትና ቅስቀሳዎች በመቆጠብ አዎንታዊ ሚና እንድትወጡ እየጠየቅን፤ ለሚመለከታቸሁ አካላት ሁሉ  ከግጭት መለስ ያሉ ሰላማዊ መንገዶችን ሁሉ እንድታስቀድሙ ጥሪ እናቀርባለን።”
ኢዜማ

Leave a Reply