“ዛሬ እኛ ነን ነገ ደግሞ እናንተ ትሆናላችሁ” ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሤ

ዓለም አስደማሚውን የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ ድል እና ተዓምራዊ ክስተት ካጣጣመ አራት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ተሸናፊዎቹ ሰላቶዎች ያልጠበቁት ምትሃታዊ ሽንፈት የእግር እሳት ሆኖባቸው ለሌላ እልቂት እና ጦርነት ቂም ቋጥረው በደል ጠንስሰው ቀን እየጠበቁ ነው፡፡ ፋሽስት ጣሊያን አርባ ዘመኗን ሁሉ ለዳግም ወረራ ስትዘጋጅ ኢትዮጵያ ግን የተለየ ዝግጅትም፤ የተሻሻለ አቅርቦትም አላደረገችም ነበር፡፡

ከዓድዋ ድል ማግስት ጀምሮ በኢትዮጵያ በኩል የተለየ የሚባል ክስተት ካለ ሊጠቀስ የሚችለው የነገስታቱ ለውጥ ብቻ ነበር፡፡ የዓድዋ ድል ጉልላት የነበሩትን ንጉሰ ነገስቷን የተፈጥሮ ሕግ በሆነው ሞት ያጣችው ኢትዮጵያ ከልጅ ኢያሱ እና ከንግስተ ነገስት ዘውዲቱ ተሸጋግራ በጊዜው ተራማጅ ከሚባሉት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መዳፍ ላይ ወድቃለች፡፡ ንጉሰ ነገስቱም ዘውድ ከጫኑ ማግስት ጀምሮ በሀገሪቱ ሥር የሠደደውን ዘውዳዊ ሥርዓት የጎሪጥ እየገረመሙ፤ ተራማጅ ሀገር እና ሥርዓት ለማንበር ምቹ አጋጣሚ ያማትራሉ፡፡

ከሁለተኛው ዙር የጣሊያን ወረራ አምስት ዓመታት ቀደም ብሎ በበርካታ ውጣ ውረድ መካከል አልፈው ንጉሰ ነገስት ተብለው የተቀቡት ጃንሆይ ይህችን ጥንታዊት፣ ቀዳማዊት እና ታሪካዊት ሀገር የመምራት አጋጣሚው ጫንቃቸው ላይ አርፏል፡፡ የመጨረሻው ሰለሞናዊ ንጉስ ታሪክ የሰጣቸውን መልካም እድል ማባከን አልፈለጉም፡፡

ጃንሆይም ከቀደምት አባቶቻቸው የመሪነት ጥበብን፤ ከዓልም አቀፉ የፖለቲካ አሰላለፍ እውቀትን አጣምረው ነጻዋን አፍሪካዊት ሀገር በባህላዊም በዘመናዊም መንገድ ማስተዳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ የንጉሰ ነገስቱን ግለ ታሪክ የጻፈው ሃጋይ ኤርሊክ “ጃንሆይ በወቅቱ ወግ አጥባቂውን ነባር ሥርዓት በተራማጁ ለውጥ ፈላጊ ተተኪ ወጣት ቀስ በቀስ ለመለወጥ ብርቱ ሥራ ላይ ነበሩ” ይሉናል፡፡

ለንጉሰ ነገስቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከንግስናቸው ማግስት ጀምረው የነበሩት አምስት ዓመታት እጅግ መልካም የሚባሉ ሆነውላቸው ነበር፡፡ አልጋቸው እረግቶ እና አጀባቸው በዝቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ቦታ እንደ አዲስ መገንባት የሚችሉበትን ነጻነት እና ኃይል አገኙ፡፡

ንጉሰ ነገስቱ በእነዚህ ዓመታት የሀገራቸውን እና የራሳቸውን እጣ ፋንታ የሚወስኑት እራሳቸው ብቻ ነበሩ፡፡ ገና አልጋ ወራሽ እያሉ በርካታ የምዕራቡ ዓለም ሀገራትን የመጉብኘት እድል እና አጋጣሚ ያገኙት ንጉሰ ነገስቱ የገበዩትን እውቀት እና የሸመቱትን ተሞክሮ ተጠቅመው ኢትዮጵያን ከራሳቸው ጋር እንድትመሳሰል አድርገው ለመሥራት ደፋ ቀና እያሉ ነበር፡፡

በዚህ ሁሉ መካከል ግን በዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች አናት ላይ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥታ አሳፋሪ ሽንፈትን የተጋተችው ጣሊያን ለዳግም ወረራ ዝግጅት ማድረጓን በሰሚ ሰሚ ከንጉሰ ነገስቱ እና መኳንንቶቻቸው ጆሮ ደርሷል፡፡ ከመጀመሪያው ወረራ ሽንፈቷ ብዙ የተማረችው ጣሊያን በምሥራቅ አፍሪካ የተንሰራፋ የቅኝ ግዛት ይዞታ እንዲኖራት ብትፈልግም በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል ኤርትራን ብቻ ይዛ በሠላም መቀጠል እንደማትችል ግን አውቃዋለች፡፡ ለዚህም ሲባል በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ እና ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ልዩ ተልዕኮ በልዩ ዝግጅት ቋፍ ላይ ደርሷል፡፡

ማርሻል ኢሚሎ ደቦኖ የጣሊያን ቅኝ ግዛት ሀገሮች ኮሚሽነር ሆኖ ተሹሟል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል በኮሚሽነሩ የሚመራ እና ከሊቢያ፣ ከሶማሊያ እና ከኤርትራ የተውጣጣ 400 ሺህ ወታደር ተዘጋጅቷል፡፡ ከ1920ዎቹ ጀምሮ ብርቱ ቅድመ ዝግጅት ላይ የነበረችው ጣሊያን ይህንን ዘመቻ በማያዳግም ሁኔታ ለመፈጸም ከ300 በላይ የጦር አውሮፕላኖች ለግዳጅ ዝግጁ አድርጋለች፡፡ በሌላ በኩል በማርሻል ሮዶልፍ ግራዚያኒ የሚመራ ኃይል መነሻውን በደቡብ በኩል አድርጎ በ100 አውሮፕላኖች እየታገዘ ወደ መሃል ኢትዮጵያ እንዲንቀሳቀስ ግዳጅ ተሰጥቶታል፡፡ በጣሊያን በኩል ይህ ሁሉ የሚሆነው የሊግ ኦፍ ኔሽንን ተፅዕኖ ለመቋቋም አዲስ አበባን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር የሚል ዓላማ አንግባ ነበር፡፡

See also  የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን መግደላቸውን ሪፖርት ጠቆመ

ከጣሊያን ዘውዳዊ መንግሥት የጦር ኃይል ተቀንሶ ተጨማሪ እና ተጠባባቂ 650 ሺህ ሠራዊት ኤርትራ ገብቷል፡፡ በከፍተኛ ሥንቅ እና ትጥቅ ተጠናክሮ የገባው ይኽ ጦር አይቀሬውን የወረራ ድል በብቃት ይፈጽማል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡ ማርሻል ሮዶልፍ ግራዚያኒም ለሮማዊያን ሁሉ “ኢትዮጵያን ከነሰዎቿ ወይም ያለሰዎቿ ተረክቤ አስረክባችኋለሁ” ሲል በጀብደኝነት ቃል ገብቷል፡፡ የጦርነቱን ጣፋጭ የድል ብሥራት ዜና እየተከታተሉ ለዓለም ሕዝብ ጆሮ ቀለብ ለማድረስ እና የዓድዋ ጦርነት የተሸናፊነትን ትርክት ለማረም 200 ያህል ጋዜጠኞች አብረው ተሰማርተዋል፡፡

እጅግ የላቀ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ዝግጅት ያደረገውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል የሚመክተው ኋላ ቀር የጦር መሣሪያ የታጠቀውና ዘመናዊ የውትድርና ሥልጠና ያላገኘው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ሠራዊት ነበር፡፡ አይቀሬው የጦርነት ነጋሪት በፍሽስት ጣሊያን እየተጎሰመ ተጀምሯል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ከሽሬ እስከ እንዳባጉና፣ ከተምቤን እስከ ዓቢይ ዓዲ፣ ከእምባ አርአዶም እስከ አምባ አላጌ የሞት ሽረት ውጊያዎች ተካሄዱ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በተደረጉት ጦርነቶች ቁጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሀገር ወዳድ ቢያልፍም በተለይም በሽሬ በተደረገው ጦርነት 300 ያክል መትረጌሶች፣ ታንኮችና ሌሎችም ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ተማረኩ፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ግንባር በማርሻል ግራዚያኒ የሚመራውን የጦር ኃይል የነራስ ደስታ፣ ደጃዝማች ነሲቡ እና የራስ መኮንን የጦር ኃይል በኦጋዴን በተደረገው ጦርነት ገጥሞታል፡፡ በቦነያ ነቀምት ደጃዝማች ሃብተ ማርያም እና በሲዳማ ራስ ደስታ ዳምጠው አይቀሬውን ጦርነት ተጋፍጠዋል፡፡ በዚህ ሁሉ መካከል በሰሜኑ ክፍል በወርሃ መጋቢት 1928 ዓ.ም ማይጨው ላይ በተደረገው ጦርነት በንጉሠ ነገሥቱ የሚመራና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት ቢሰለፍም ኢትዮጵያዊያኑ ድል ሆኑ፡፡

በሁሉም አቅጣጫ በለስ የቀናቸው ጣሊያናዊያኑ የሀገሪቱን ርእሰ መዲና አዲስ አበባ ተቆጣጠሩ፡፡ ማርሻል ባዶሊዮ ሚያዝያ 27/1928 ዓ.ም አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አስወርዶ፤ ቀይ ነጭ እና አረንጓዴውን ባንዲራ በአዲስ አበባ ሰማይ ስር አውለበለበው፡፡ “ይኽን ቆሞ ከማየት ሞት በስንት እጁ ይጥማል” ያሉት አርበኞችም ውሎ እና አዳራቸውን በዱር በገደሉ አድርገው እምቢ ለነጻነቴ አሉ፡፡

ኢትዮጵያ በንጉሠ ነገሥቷ አማካንነት የዓለማቀፉን ማሕበረሰብ ድጋፍ ብትጠይቅም የዓለም መንግሥታት ጆሮ ነፈጓት፡፡ ጭራሽ በጣሊያን ላይ አስተላልፈውት የነበረውን ማዕቀብ ነሐሴ/1928 ዓ.ም ላይ አነሱት፡፡ ታኅሳስ/1929 ዓ.ም ላይ ደግሞ ጃፓን የጣሊያንን ቅኝ ገዥነት እውቅና ሰጠችው፡፡ ፈረንሣይ እና እንግሊዝም ከቅኝ ገዥዋ ጣሊያን ጎን በመቆም የድጋፍ ድምጻቸውን አሰሙ፡፡ በርካቶቹ ኃያላን ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ ፊታቸውን አዞሩ፡፡ ጣሊያንም ከየአቅጣጫው የሚጎርፍላት ድጋፍ የልብ ልብ ሰጥቷት የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ እስከመጠቀም ድረስ የግፍ ዶፍ አዘነበች፡፡

ከሜክሲኮ እስከ ቻይና፣ ከኒውዚላንድ እስከ ሶቪየት ኅብረት፣ ከስፔይን ሪፐብሊክ እስከ አሜሪካ ወራሪው የጣሊያን መንግሥት በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ ተቃወሙ፡፡ ነገር ግን እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ድረስ እነዚህ ሀገራት ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ሆነ ለኢትዮጵያ ያመጡት ተፅዕኖ፤ የፈጠሩት ለውጥ አልነበረም፡፡ የዘገየው ዲፕሎማሲ በንጉሰ ነገስቱ እና ልዑካቸው በመላ አውሮፓ እየተዘዋወረ “ፍትህ ወዴት አለሽ” ቢልም ኃያላኑ የጣሊያንን ክፉ ላንሰማ “የዝሆን ጆሮ ይስጠን” አሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን “እንኳን ሰዎቹ ምድሪቱ እንኳን ለወራሪዎች እሾክ ትሁን” ተብሏልና የሞት ሽረት ትግሉ በአሃድም በህቡዕም አልተቋረጠም፡፡

See also  የሱዳን ጦር ሠራዊት የራሱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሾም ምዕራባዊያን አገራት አስጠነቀቁ

በዓለም መንግሥታት ማሕበር ፊት ጀኔቭ አደባባይ ላይ ቆመው “ዛሬ እኛ ነን ነገ ደግሞ እናንተ ትሆናላችሁ” ያሉት ንጉሰ ነገስቱ ትዕምቢታቸው እውን ሆኖ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡ ጦርነቱ የዓለም ሀገራት በተለይም በጅኦ-ፖለቲካል አጠራራቸው ምዕራባዊያኑ ሀገራት ጎራ ለይተው ተሰለፉበት፡፡ ፋሽስት ጣሊያን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጀርመን ናዚ ደጋፊ ሆና ብቅ አለች፡፡ ይኽ አቋሟ ደግሞ በተለይም እንግሊዝ ጥርስ እንድትነክስባት አደረጋት፡፡ ኃያላን አንሰማም ያሉትን የፍትህ ድምጽ የኃያላን አምላክ ሰምቶ እንደ ባቢሎናዊያን እርስ በእርስ አናከሳቸው፡፡

ሲለመኑ እምቢ ያሉት እንግሊዞች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጣሊያን ከናዚዎች ጎን መሰለፏን ተከትሎ ለኢትዮጵያ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ወሰኑ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ከስደት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መንገድ ጠራጊ የፍትህ መልዕክተኛ ለመሆን ወሰኑ፡፡

በጀኔራል ካኒንግሂም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከኬኒያ ተነስቶ ከደቡብ አቅጣጫ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ገሰገሰ፡፡ በጄኔራል ፕላት የሚመራው ጦር ደግሞ ከሱዳን ተነስቶ ወደ አስመራ፤ ከአስመራ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ተንቀሳቀሰ፡፡ ጌዲዮን የሚል ስያሜ የተቸረው ጦር በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አርበኞች እና በእንግሊዝ አማካሪዎች ተዋቅሮ ከሱዳን ተነስቶ በኦሜድላ አልፎ በጎጃም በኩል ወደ መሃል ሀገር ገሰገሰ፡፡

በዚህ ሁሉ መካከል ግን እምቢ ለሀገሬ ያሉት አርበኞች አጣብቂኝ ውስጥ የወደቀውን የፋሽስት ጦር ቁም ስቅሉን ያሳዩታል፡፡ በቡድን ወጥቶ በተናጠል የሚመለሰው የጣሊያን ጦር በኢትዮጵያዊያኑ አርበኞች አይገመቴ የጦር ታክቲክ እየከፈለው ባለው የሕይዎት ዋጋ ተሰላችቷል፡፡ ዘመቻው ከተጀመረ ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ የፋሽስት ጦር አዲስ አበባን ለቆ ፈረጠጠ፡፡ መጋቢት 28/1933 ዓ.ም የጄኔራል ካኒንግሃም ጦር አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ፡፡

ኢትዮጵያ በርእሰ መዲናዋ አዲስ አበባ ሰማይ ስር የማይመስላትን እና የማያምርባትን ባንዲራ ባውለበለበች ልክ በአምስተኛው ዓመት ሚያዝያ 27/1933 ዓ.ም አዲስ ታሪክ ተመዘገበ፡፡ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ላይ ከታላቁ በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት አደባባይ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማ መልሰው አውለበለቡት፡፡ መድፍ ደጋግሞ እያጓራ፣ የክብር ዘብ ተሰልፎ፣ አርበኞች በፍጹም ብሔራዊ ኩራት ቆፍጠን እንዳሉ ንጉሰ ነገስቱ እንዲህ አሉ

“ይህ የምትሰሙት ድምጽ የእኔ የንጉሳችሁ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድምጽ ነው፡፡ ይኽ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ከከባድ የመከራ ቀንበር እና ከዘላለም ባርነት ነጻ የወጡበት ቀን ነው፡፡ እኛም አምስት ዓመታትን ሙሉ ተለይተነው ከነበረው፤ ከምንወደው እና ከምንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላቀል የበቃንበት ቀን ነው፡፡ ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ በየዓመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ ልጆች የድል በዓል ሆኖ ይከበራል” ሲሉ የአርበኞች ቀንን በአርበኞች መካከል ቆመው አወጁ፡፡

ኢትዮጵያም ከነሰዎቿም ሆነ ያለሰዎቿ ለባዕድ ሳትረካከብ ዳግም በንጉሰ ነገስቷ መዳፍ ውስጥ አረፈች፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ኃያላን ጆሮ የነፈጉት የፍትህ ጥያቄዋ በልጆቿ እና ጎራ ባመሰቃቀላቸው ወዳጆቿ ከምንም በላይ ደግሞ በታመነችው የፍትህ አምላክ ዳግም ነጻ ወጣች፡፡ ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ ስትረማመድ አልጋ ባልጋ ሳይሆን እሾክ እና ቀጋ እየፈተኗት እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው፡፡

See also  ሸኔ እየተበታተነ ንጽሃንን በድጋሚ መጨፍጨፉን መንግስት ይፋ አደረገ

የመረጃ ምንጮቻችን፡- “አጼ ኃይለ ሥላሴ አነሳሳቸው እና ውድቀታቸው” ሃጋይ ኤርሊክ፤ “የዓድዋ ጦርነት እና የዓለም ቅኝ ግዛት አሰላለፍ” በኤርሚያስ ጉልላት እና “የኢትዮጵያ ታሪክ” ሪቻርድ ፓንክረስት

በታዘብ አራጋው / አሚኮ

Leave a Reply