ጎበዜ ሲሳይ ከጅቡቲ ተላልፎ መሰጠቱን የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረሃይል አስታወቀ

በአማራ ክልል ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ከፅንፈኛ ሀይሎች ጋር ተባብሮ በመስራት የሽብር ተግባር ፈፅሟል በሚል ሲፈለግ የነበረው ጎበዜ ሲሳይ የተባለው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረሃይል አስታወቀ።

ግለሰቡ አምልጦ ጅቡቲ ከገባ በኋላ ወደሌላ አገር ሊሻገር ሲል ከዓለም አቀፉ ፖሊስ እና ከጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር እንዲውልና ተላልፎ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ተደርጎ ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረሃይል ገልጿል።

በአማራ ክልል ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ክልላዊ ስልጣንን በኃይል ለመያዝ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በህቡዕ ተደራጅተውና ተቀናጅተው በሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ሚያዚያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

በዚህ መሰረትም ፦

1. ሀብታሙ አያሌው፣

2. ምንአላቸው ስማቸው

3. ብሩክ ይባስ እና

4. እየሩሳሌም ተ/ፃዲቅ

5. ዘመድኩን በቀለ

6. ልደቱ አያሌው

7. መሳይ መኮንን

8. ጎበዜ ሲሳይ

9. ምህረት ወዳጆ (ምሬ ወዳጆ)

10. በለጠ ጋሻው እና

11. ሙሉጌታ አንበርብር የተባሉት ተጠርጣሪዎች በፈፀሙት የሽብር ተግባር እንደሚፈለጉና ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንደሚቀርቡ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሀይል ማሳወቁ ይታወሳል።

ከነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከልም ጎበዜ ሲሳይ ዘገየ የተባለው ግለሰብ፣ በአማራ ክልል ቆቦ አካባቢ የጽንፈኛ ታጣቂ ሀይሎችን በማደራጀት፣ በቅርቡም በጽንፈኞች ግድያ የተፈጸመበትን የአቶ ግርማ የሺጥላን ግድያ በማስተባበር ሚና እንደነበረው፣ በመከላከያና በህዝቡ ላይ ጽንፈኞች ጥቃት እንዲያደርሱ በማደራጀትና ቃል አቀባይ ሆኖ በማስተባበር የሽብር ተግባር ውስጥ በመሳተፍ ተጠርጣሪ በመሆን ሲፈለግ ቆይቷል።

ግለሰቡ አማራ ክልልን በማሸበርና ስልጣንን በሀይል በመቀማት በቀጣይም የፌዴራል መንግስትን ለማፍረስ ሲንቀሳቀስ ከነበረ ጽንፈኛ አካል ጋር በመተባበር ሲሰራ እንደነበር በመጠርጠሩ፣ ግለሰቡን ጨምሮ ሌሎች በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የጋራ ግብረ ሀይሉ ከኢንተርፖል ጋር ባለ ስምምነት መሰረት ሲሰራ መቆየቱን ገልፆ ነበር።

See also  በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ ግዙፏ "ዓባይ ፪" መርከብ አቀባበል ተደረገላት

በዚሁ መሰረትም አስፈላጊውን ፎርማሊቲና አግባብ ያላቸው መረጃዎችን በማደራጀት ጎበዜ ሲሳይ የተባለው ግለሰብ አምልጦ ጅቡቲ ከገባ በኋላ ወደሌላ አገር ሊሻገር ሲል ከዓለም አቀፉ ፖሊስ እና ከጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር እንዲውልና ተላልፎ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ተደርጎ ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ገብቷል።

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሀይል አሁንም ኢትዮጵያ ባላት ስምምነት መሰረት ሌሎች ያልተያዙ የሽብር ቡድኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰራ መሆኑን ለኢዜአ ገልጿል።

Leave a Reply