የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀደሞ ፕሬዚዳንት ጨምሮ 15 ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀደሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታን (ዶ/ር) ጨምሮ 15 ተከሳሾች ላይ ከ195 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ፡፡

ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ያለመከሰስ መብታቸው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተነሳው በቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀደሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ታምሩ ኦኖሌ፣ የአስተዳደር እና የተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ሮባ ደንቢ (ዶ/ር) ፣ የቢዝነስና ተቋማዊ ልማት ም/ፕሬዚዳንት አብርሐም ባያብል (ኢ/ር)፣ የግዢ ዳይሬክተር ሊበይ ገልገሎ፣ የግዢ ዳይሬክተር ቦሩ ህርቦዬ፣ የዩኒቨርስቲው መምህርና የቢኤች ዩ አማካሪ ለታ ድሪባን ጨምሮ ጠቅላላ ስራ ተቋራጮችና የቢዳሩ ኮንስትራክሽን ስራ አስኪያጆች ይገኙበታል።

በተከሳሾቹ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዓቃቤ ሕግ አራት ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክሶችን መስርቷል።

በዚህም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር ያሉት ተከሳሾች የዩኒቨርሲቲው አመራርና የማኔጅመንት አባል በመሆን ሲሰሩ የመንግስት ግዢ አዋጅን በመተላለፍ በ2012 ዓ.ም በያዙት ቃለ ጉባኤ መሰረት ሕግን ባልተከተለ መልኩ ያለአግባብ ቢኤች ዩ ለተባለ አማካሪ ግዢው በቀጥታ እንዲፈጸም በማኔጅመንት ውሳኔ ማስተላለፋቸው ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ዩኒቨርሺቲው ውል ሲዋዋል ዩኒቨርሲቲውን በመወከል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት 1ኛ ተከሳሽ ውል ሰጪ ሆነው 7ኛ ተከሳሽ ውሉን በመፈረም በ5ኛ ተከሳሽ ትዛዝ መሰረት በአንደኛ ተከሳሽ ስም ለተመዘገበው አማካሪ ድርጅት ያለአግባብ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጉን ዓቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

በሌላ በኩል የዩኒቨርሲቲውን የመተዳዳሪያ እና የግዢ አዋጁ በመተላለፍ የ14 ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎችን ግዢ በመፈጸምና 116 ሚሊየን 389 ሺህ 964 ብር ማሽነሪዎችን በስጦታ ያገኙ በማስመሰል ያለአግባብ 12ኛ፣ 13ኛ እና 14ኛ ተከሳሾች በተሽከርካሪ ግዢ ጥቅም ማግኘታቸው ተመላክቷል።

ተከሳሾቹ ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በቀጥታ ግዢ እንዲፈጸም ውሳኔ በማስተላለፍ ከሌሎች ተከሳሾችና ከስራ ተቋራጮች ያለአግባብ ካለ ግልፅ ጨረታ ግዢ በመፈጸም በመንግስት ላይ 195 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል ዓቃቤ ሕግ በዋና እናበልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

See also  የፍትህ ያለህ የሚሉት የ87 ዓመት አረጋዊቷ እሮሮ

በዚህ መልኩ የተመሰረተባቸው የክስ ዝርዝርም በችሎት ለተከሳሾቹ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡

ተከሳሾቹ ከጠበቃቸው ጋር ተማክረው የፊታችን ግንቦት 7 ቀን 2015 ዓ.ም ፍድር ቤት ቀርበው ክሱን በንባብ ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

Leave a Reply