የአገሪቱ ችግሮች ምንጭ የሆነው ህገመንግስት መፍትሄ ሊሰጠው ነው

የአገሪቱ ችግሮች ምንጭ የሆነው ህገመንግስት መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ድኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን ማስረጃና ጥናት አጣቀሰው አስታወቁ። በጉዳዩ ላይ ሶስት የልዩነት ዕይታዎች ቢኖሩም አብዛኛው ሕዝብ ፍላጎቱ ግን የህገ መንግስት መሻሻል አስፈላጊነት ላይ ያመዘነ ነው። አሚኮ ከታች ያለውን ዜና አስነብቧል።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለውጥ ያስፈልገው ይሆን? ከኾነስ የትኞቹ ድንጋጌዎች በሚል የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት ጥናት አካሒዷል። በዚህ የጥናት ውጤት ይፋ ማድረጊያ እና መወያያ መድረክ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ዘሃራ ሁመድን ጨምሮ የፖሊሲ ባለሙያዎች፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት ኀላፊዎች፣ ሚኒስቴር ዴኤታዎች እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

በፕሮግራሙ የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ሕገ መንግሥቱ ከተረቀቀበት ጊዜ አንስቶ የክርክር ምንጭ መኾኑን ጠቅሰዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ ችግሮች፣ መፈናቀሎች እና ብሔር ተኮር ግጭቶች ሕገ መንግሥቱ መሰረታዊ ድጋፍ ይሰጣል የሚሉ ሃሳቦች ይደመጣሉ፡፡ በሌላ በኩል የማንነት መሰረት ነው የሚሉም አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ጥናት መሥራት አስፈልጓል ብለዋል። ሕገ መንግሥቱ የሊህቃኑ ብቻ ሳይኾን የሕዝብም በመኾኑ ሁሉንም ያማከለ ሀሳብ ይዞ መጓዝ ይገባል ነው ያሉት።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መስፍን (ዶ.ር) ሁሉም የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች በተለያየ መንገድ የሚሻሻሉበትን ሁኔታ አስቀምጠዋል። በመደበኛም ይሁን በኢመደበኛ መንገድ ሕገ መንግሥቱ እንደሚሻሻልም አስገንዝበዋል።

በምሳሌት ያነሱት 391 አንቀጽን የያዘው የሕንድ ሕገ መንግሥት 105 ጊዜ ተሻሽሏል ነው ያሉት። በመኾኑም ሕገ መንግሥቱ ሙሉ ሊኾን እንደማይችል የሌሎችን ሀገራትን ሕገ መንግሥት በመጥቀስ አንስተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ምንም እንኳን ሕገመንግሥቱ አልተሻሻለም ይባል እንጂ የተለያዩ አንቀጾቹ በአዋጅ እና በትርጉም እንዲሁም በሌላ መንገድ ተሻሽለዋል ብለዋል። የፌዴሬሽን ምክርቤት ለእነዚህ ሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች ዕውቅና ያልነፈገ በመኾኑ እንዲሻሻል እንደፈቀደ ይቆጠራል ነው ያሉት። በምሳሌነትም የፌዴራሉ አባል ክልሎችን የሚደነግገው አንቀጽ 47 ስለመሻሻሉ ጠቅሰዋል። በተመሳሳይ የፌዴራል እና የክልል የጋራ ገቢዎች የሚወስነው አንቀጽ 58 እንዲሁም መሬት ማሥተዳደርን በተመለከተ የሚደነግገው አንቀጽ 89 እና ሌሎች አንቀጾች መሻሻላቸውን አንስተዋል።

See also  መላላክ በየደረጃው አምልኮ ነው - ተላላኪዎች ሁሉ ሰጋጆች ናቸው

ሕገ መንግሥትን በተመለከተ በሀገር ደረጃ 3 ምልከታዎች አሉ ያሉት ዶክተር ስዩም አንደኛው ሕገ መንግሥቱ ረብ የለውም የሚል ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ በፍፁም መነካት የለበትም የሚል ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ሁሉንም ባካተተ መልኩ ይሻሻል የሚል እንደሚገኝበት ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው ጠቃሚው ሀሳብ ሁሉንም ባካተተ መልኩ ይሻሻል የሚለው እንደኾነ አስገንዝበዋል።

ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል እጅግ አስፈላጊ እንደኾነ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው ሕገ መንግሥቱ የማይሻሻል ከኾነ ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ በኃይል የመቀየር እንቅስቃሴ እና ፍላጎት ሊያሳዩ እንደሚችሉ አስረድተዋል። በሀገሪቱ ያሉ የግጭት እና የአለመግባባት ጉዳዮችን በቀላሉ ለመፍታትም እንዲያስችል ሁሉንም ያማከለ ሀሳብ ይዞ ቢሻሻል መልካም እንደኾነም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን

Leave a Reply