የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎችና የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች የአቋም መግለጫ

“ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 10-12/2015 ዓ.ም በአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች እና የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ሲመክር የቆየው ኮንፍረንስ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

ኮንፈረንሱ ለፓርቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመገንባት የተዘጋጀ መድረክ መሆኑ ይታወሳል።

በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም ፋራህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዳይሬክተር ጀኔራል ተመስገን ጥሩነህ ተገኝተዋል።

የኮንፈረንሱ የአቋም መግለጫ ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል፦

ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን!!!

የአማራ ክልል የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ከግንቦት 10 እስከ 12 /2015 ዓ.ም ድረስ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በባሕር ዳር ከተማ “ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ቃል ክልላዊ ኮንፍረንስ በማካሄድ በክልሉ እየተፈጠሩ ያሉ ፖለቲካዊ፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በጥልቀት ገምግመናል፡፡

የለውጡ ምዕራፍ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በሀገራችና በክልላችን አይነተ ብዙ ውጤታማ ድሎችን ያስተናገድን መኾኑ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ ለአብትም ከነዚህ ለውጦች መካከል የዴሞክራሲ ምህዳር የማስፋት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ ሰላማዊ ትግል የማምጣት፣ ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ ፕሮጀክቶችን የማስጀመርና የመጨረስ ፤ አዳዲስ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን የመከወን፣ የአግላይነትና የጠቅላይነት የፖለቲካ ባህልን የቀየረ የፓርቲ አደረጃጀት መፈጠሩ፣ የአማራ ሕዝብ የወሰንና የማንነት ጥቄዎች ከ30 ዓት በኋላ በሕጋዊ መንገድ ምላሽ የሚያገኙበት እድል መፈጠሩ፣ የተቋማት ሪፎርም መካሄዱ … ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሁኖም ግን እነዚህን ድሎች ስናስመዘገብ የሄድንበት መንገድ አልጋ በአልጋ አለመሆኑን የሚያስረዱ ያደሩና አሁናዊ ፈታናዎች ጋር በመጋፈጥ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በመጣንበት የለውጥ ጎዳና መፈናቀልና ሞት፣ ጽንፈኝነትና ሥርዓት አልበኝነት፣ አውዳሚ የሆኑ የትግል ስልቶችን በመከተል መሪ አልባ ክልል ለመፍጠር የሚደረግ አጥፊ እንቅስቃሴ እንዲሁም መንግሥትን ከሕዝብ የሚነጥል የጠላት አጀንዳ በመስጠት ሕዝባችን ሁለንተናዊ የተጠቂነት ስነ ልቡና ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ሌት ተቀን ያለእረፍት እየተሠራብን መሆኑን መላው ሕዝባችን ሊረዳው ይገባል፡፡

በመሆኑም ስኬቶቻችንን የበለጠ በማጽናት አሁናዊ ችግሮቹን ደግሞ ደረጃ በደረጃ እየፈቱ ለመሄድ ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት የምንቆምበትና የትግል መስመራችንን የምናፀናበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡

በመሆኑም የገጠሙንን ችግሮች ከመሰረታቸው ለመፍታት የሚያስችሉ የአስተሳሰብና የተግባር መፍትሔዎችን ማጎልበት የምንችልበትን ስልቶች የጋራ አድርገናል፡፡ ስለሆነም በውይይቱ የተደረሰባቸው ማደማደሚያዎች እደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

ውድ የድርጅታችን አመራሮች፤ አባላት፤ ደጋፊዎቻችን እና መላው የክልላችን ሕዝብ፡-

የአማራ ክልል መንግስት አኹን የሚገኝበትን ፖለቲካዊ ችግሮች ፈር ለማስያዝና እና ፖለቲካዊ ፈተናዎችን ተጣብተው የተፈጠሩ ዙሪያ መለስ አደጋዎችን ለመቀልበስ ሁሉንም አይነት ዋጋ እየከፈለ ይገኛል፡፡

ሕዝባችን ከ3 አሥርተ ዓመታት በላይ የታገለባቸው የማንነት ጥያቄዎች፤ የአስተዳደራዊ ወሰን ጉዳዮች፤ የሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ ማሻሻያዎች፤ ስሁት የሆኑ ፖለቲካዊ ትርክት እርማቶች፤ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ጥያቄዎች፤ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አከባበር ላይ የሚታዩ ዝንፈቶችን ለመግራት ያላሰለሰ ፖለቲካዊ ትግል እያደረገ መሆኑ የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡

ምንም እንኳን የአማራ ሕዝብ ያነሳቸው ጥያቄዎች ፍትሃዊነታቸውና ተገቢነታቸው የማያወላዳ ቢሆንም መሰረታዊ ጥያቄዎቻችን በጸረ-ኢትዮጵያ እና ጸረ-አማራ አቋም ኅልውናቸውን በመሰረቱ ቡድኖች በተሳሳተ የታሪክ አረዳድ ላይ በተመሰረተ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች ተጣመው የተቀነበቡ መሆናቸው የትግላችንን ዳርቻ እልህ አስጨራሽና የተራዘመ ግዜ የሚወስድ አድርጎታል፡፡

በተለይም በሕዝባችን ማንነት ላይ ያነጣጠሩ መርዘኛ የፖለቲካ የጥላቻ ውትወታዎችን እንደ ትግል ስልት የሚጠቀሙና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያቀነጭር የሕግ ድንጋጌዎች፤የፖለቲካዊ ስርዓትና አስተዳደራዊ አደረጃጀት ከአንድ ትውልድ እድሜ በላይ ሲተገበር የቆየ መሆኑ አሁናዊው የአማራ ሕዝብ ፖለቲካዊ ችግር ሥር የሰደደ እና በውስብስብ መንስዔዎችና በሴራ ወለድ አቁሳይ ውጤቶች የተጠላለፈ እንዲሆን አድርጎብናል፡፡

የሕዝባችን ፍትሃዊ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኙና ተፈላጊውን ለውጥ ለማረጋገጥ እንደ አንድ ሕዝብ ለጋራ ዓላማ ውስጣዊ አንድነትን ከማጽናት ባሻገር የጋራ የሆነን ችግር በጋራ የመፍትሄ ስልት የመፍታት ፖለቲካዊ ብቃት ባለቤት ሆኖ ከመገኘት ባሻገር፤ የኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍን ያስቀደመ ከመላው ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር የላቀ መተማመንን እና የትብብር መስተጋብርን ፈጥሮ መገኘትን የሚጠይቅ በመሆኑ ከራሳችን ጥረት በተጫማሪ የወገኖቻችንን ድጋፍና ይሁንታ ይጠይቃል፡፡

See also  ለ25,791 እድለኞች የጋራ መኖርያ ቤት ዕጣ ወጣ

በመሆኑም ፍትሃዊ ጥያቄዎቻችን በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ አግባብ ብቻ እንዲፈቱ አስፈላጊውን የፖለቲካዊ የሀይል ሚዛን የሚያሰባስብና በኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊ አንድነት ማዕቀፍ የተዋጀ የፖለቲካ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊም ፤ አስገዳጅም በመሆኑ ፓርቲያችን ብልጽግናን መስርተናል፡፡ ባሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥም ከፓርቲያችን ብልጽግና ፕሮግራሞችና መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ የማንነትና የአስተዳደራዊ ወሰኖች ጉዳይ ምላሽ የሚያገኙበት መደላደሎች ተፈጥረዋል፡፡

በፈተና ውስጥም ሆነን ቢሆን የዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደትና ሥርዓት ግንባታ፤የአካታች መንግስት ምስረታ፤ የቱሪዝም ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን ማስፋት፣ የማዕድን ልማትን ማሳደግ፣ ከተሞችን ለነዋሪዎች የሚመጥኑ ለማድረግና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን የመፍታት አይነተኛ ድሎችን፣ የግብርና እና የኢንቨስትመንት ልማትና የማረጋገጥና ግጭቶችን በድርድር የመቋጨት ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን ለማሳመዝገብ ችለናል፡፡ ይሁን እንጂ የተገኙ ድሎችን የሚያመክኑና በሕዝባችን ጥያቄዎች ላይ ደንቃራ የሚሆኑ ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች ተፈጥረዋል፡፡ በተለይም አፍራሽ ኃይሎች ክልሉን ለማተራመስ ስሜት ኮርኳሪ የሆኑ ቁርሾዎችን በማፋፋም የተጠቂነት ስነ ልቦናዊ ውቅርና የተጠቂነት ስነ ልቦና የሚወልደው ጽንፈኝነትን ለማስፋፋትና የስርዓት አልበኝነት ድርጊቶች እየተባባሱ በመሄዳቸው በክልላችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ውስጣዊ ምልከታና ለወቅቱ ተግዳሮት የሚመጥን መፍትሔ መተለም ግድ ብሏል፡፡

በመኾኑም በክልላችን አሁናዊ የፖለቲካ ኑባሬ ላይ ተመስርተን፤ የምንገኝበትን ፈታኝ ሁኔታ እንደ ዘላቂ የመፍትሄ አማራጮች ማምረቻ እድል ለመጠቀም የሚያስችል ኮንፍረንስ በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች መካከል ተከናውኗል፡፡

ከግንቦት 10 እስከ 12- 2015 ዓ/ም ድረስ በክልላችን የወቅቱ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ባከናወንነው ውስጣዊ ውይይት እንደ አንድ ሕዝብ ያጋጠሙንን ሁለንተናዊ ፈተናዎች እና በፈተናዎች ውስጥም ሆነን ያስመዘገብናቸውን ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ውጤቶችን መርምረናል ፡፡

እንደ አንድ የካበተ ሥርዓተ መንግስት ምስረታ ልምድ ያለው ማኅበረሰብ አካል እንደመሆናችን መጠን፤ የዛሬያችን መሰረት የሆነውን ትላንታችንን በምልሰት መቃኘት፤ ለነጋችን ፍካት ጉልበት የሚሆንበትን እድል እንደ ወረት ለመውሰድና፤ ሕጸጾችን እያረሙ የጋራ ቅቡልነት የተቸረው ሥርዓተ መንግስት ለመገንባት በሚያስችል ሕብረ ብሔራዊ ሂደት ላይ ትኩረት የመስጠት አማራጭን አስቀድመናል፡፡

ከረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ሥርዓተ መንግስት ግንባታ ምእራፍ ውስጥ ዜጎች በየትውልዳቸው ለሰብዓዊ፤ ዴሞክራሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው መከበር ሲሉ ካከናወኗቸው ትግሎችና ካስመዘገቧቸው ውጤቶች አንጻር በመነሳት ከአሁናዊው ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ጋር ያለውን ታሪክ ተኮር መሰናስን ፈትሸናል፡፡

አሁን ለምንገኝበት ወቅታዊ የለውጥ መንስዔዎች፤ ተግዳሮቶች እና ተስፋ ሰጪ ስኬቶች ለማስመዝገብ ካስቻሉን የፓርቲያችን ብልጽግና ፕሮግራምና መርሆዎች ላይ በተገነባ የአመራር ቁመና ያጋጠሙንን ፈተናዎች ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን የምናሻግርበትን አቅጣጫዎች ለይተናል፡፡

በሁሉም የአማራ ክልል አካባቢዎች ለተፈጻሚነታቸውም የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ በኮንፍረንስ ቆይታችን የደረስንበትን ማደማደሚያ የሚያረግግጡ ባለ 9 ነጥብ የአቋም መግለጫ እንደሚከተለው ተዘጋጅቷል ፡፡

1ኛ- በየትኛውም ወቅት ማንኛውም ሀገር ወይም አካባቢ እድሎችና ፈተናዎች ያጋጥሙታል፡፡ በክልላችንም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ጉዞ ውስጥ በርካታ እድሎችና ፈተናዎች አጋጥመውናል፡፡ በተለይም የአማራ ሕዝብ በብሔር ላይ የተመሰረተ የፌደራል አወቃቀር በሕዝቦች መካከል አንድነት ሳይሆን እርስ በርስ የመጠራጠር እና የመከፋፈል አዝማሚያ እንዲፈጠር ሆን ተብሎ ስሁት የሆነ የፖለቲካ ትርክት በመፈጠሩ የአማራ ሕዝብ ማሕበራዊ እረፍት እንዲያጣ ብሎም የግጭትና የመፈናቀል ሰለባ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ሆኖም የሕዝቡን ትግልና የለውጥ ፍላጎት ዳር ለማድረስ በተደረገው እልህ አስጨራሽ ጥረት ዛሬ ላይ የዴሞክራሲ ምህዳርን ለማስፋት የፖለቲካ ሪፎርም ተሰርቷል፤ አግላይና ጠቅላይነት የሚንጸባረቅበትን የፖለቲካ ድርጅት በመለወጥ ዜጎች በንቃት የሚሳተፉበትና ከጠርዘኝነት ወደ መሀል የሚያመጣ ኅብረ ብሔራዊ ውህድ ፓርቲ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ ይህም የብሔር አስተሳሰብ ገዢ በነበረበት አካባቢና አውድ በአንድ ግዜ የብሔርተኝነት አስተሳሰብን ከሀገራዊ አስተሳሰብ ጋር አጣጥሞ ለማቻቻል ግዜ ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ ፈር እና ሚዛኑን ጠብቀን የሁሉቱንም አስተሳሰብ የሚያስታርቀውን የብልጽግናን የመሃል መንገድ መርጠናል፤ ለተፈጻሚነቱም ጉዟችንን ጀምረናል፡፡ በመሆኑም ይህንኑ ሂደት ዳር ለማድረስና ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን ለማጽናት ቃል እንገባለን !!!

See also  አጫጭር ወቅታዊ መረጃዎች

2ኛ፡- በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ፤ቁሳዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳቶች ደርሰዋል ፡፡ ምንም እንኳ የተከናወኑት የመልሶ ማልማትና ግንባታ ተግባራትን ከደረሰብን ጉዳቶች አንጻር ገና ጅምርና ዝቅተኛ ቢሆንም አቅም በፈቀደ መጠን በጦርነቱ የተጎዳው ማኅበረሰብና አካባቢን ከጦርነቱ ዳፋ ፈጥኖ እንዲያገግም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ የሰሜኑ ጦርነት እንደ አንድ ሕዝብ ተደቅኖብን የነበረው የኅልውና አደጋን ለመቀልበስ እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለመታደግ የገባንበት ቢሆንም ከፍተኛ መጠን ያለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ላይ የጣለን በመሆኑ በክልላችን ልማት፤ በሕዝባችን የልማት ተጠቃሚነት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ ስለሆነም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸውን ጉዳቶች ፈጥኖ ለማከም ሁለንተናዊ አቅሞቻችንን በማቀናጀት ሕዝባችን ከጉዳቱ ፈጥኖ እንዲያገግምና ተወዳዳሪ ክልል ለመገንባት ያለእረፍት የምንሠራ መኾኑን እናረጋግጣለን ፡፡

በተጨማሪም ጦርነት ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣ ባለመሆኑ በሰላም ለመቋጨት የተሄደበትን ሂደት በመደገፍ እና በማንኛውም የሀገራችን አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን በሰላማዊ አማራጮች የመፍታት ሂደትን ቀዳሚ አማራጭ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት እየገልጽን ሌሎች ሠላም ወዳድ ኃይሎች ሁሉ ማንኛውንም አይነት ልዩነት በሠላማዊ እና በሠላማዊ መንገድ ብቻ የመፍታት አማራጭን እንዲከተሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

3ኛ- ባካሄድነው ውስጣዊ ኮንፍረንስ የተፈተሹ ስኬቶችና ፈተናዎቻችንን እና የመውጫ ስልቶችን በሚገባ ተገንዝበናል ፡፡ በመሆኑም መላው የክልላችን አመራሮች በለውጡ የተገኙ ሀገራዊና ክልላዊ ሁለንተናዊ ስኬቶችን የበለጠ በማስፋትና በማጽናት፤ በለውጡ ሂደት ውስጥ የተስተዋሉ ፈተናዎችን ደግሞ በሕዝብ ወገንተኝነት ስሜት፤ በሐቅ ላይ በተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ትግል እና በቁርጠኛ የአመራር ሥርዓትን በመከተል ፈተናዎችን እንደ እድል በመውሰድ ሕዝባችን አበክሮ የሚፈልጋቸውን እውነተኛ ሠላም፤ የዴሞክራሲ እና የመልማት ፍላጎቶች እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ዳር እንዲደርስ መላው የክልሉ አመራሮች ሌት ተቀን ለመሥራት እና ሁሉንም አይነት ዋጋ ለመክፈል ቁርጠኞች መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡

4ኛ- የአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ ቅቡልነት ያለው የስርዓተ መንግስት ግንባታ እንዲሳካ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በጋራ በመሆን ከፍተኛ አበርክቶ ያለውና በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን ለማጽናት ሁሉንም አይነት ዋጋ የከፈለ ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝባችን ያነሳቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች የሚፈቱት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ፤ በወንድማማችነትና እህትማማችነት መስተጋብር፤በኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊ አንድነት፤በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ትግል ብቻ መሆኑን አበክሮ ይገነዘባል፡፡

ሥለሆነም የወሰን እና የማንነት፤ የዜጎች መብት፤ የኢኮኖሚ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፤ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያዎች፤የስሁት ፖለቲካዊ ትርክቶች እርማት እና የመሳሰሉትን ውለው ያደሩ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችም ሆነ አሁናዊ የአማራ ሕዝብ ፍላጎቶች ማለትም የሠላም እና የመልማት፤ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር አብሮ የመኖር፤ ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ እንዲከበር እኛ የአማራ ክልል አመራሮች ያሉብንን ችግሮች አርመን፤ ምሁራንን፤ ሲቪክ አደረጃጀቶችን የሃይማኖት ተቃማት መሪዎችንና መላው ሕዝብችንን አስተሳስረን፤ በጋራ እየመከርን የጋራ መፍትሄዎችን እያስቀደምን፤ ለዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎቻችን ቅደም ተከተል አስቀምጠን ችግሮችን ለመፍታት የኮንፍረንሱ ተሳታፎዎች ዘንድ ሙሉ ስምምነት ላይ ተደርሳል፡፡ በዚህ አግባብ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶቹን ለማሳካት እንደ አመራር አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል ቃል እንገባለን ፡፡

5ኛ- በክልላችን እየተባባሰ የሚስተዋለውን ሌብነት፤ጎጠኝነት፤ የአመጽና የአድማ እንቅስቃሴዎች ፤ ብልሹ አሠራር፤ ስርዓት አልበኝነት፤ ጽንፈኝነትና አክራሪነት የክልላችንን ፖለቲካዊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶቻችንን በእጅጉ እየጎዳውና ሁሉን አቀፍ ኪሳራ እያስከተለ መሆኑ ተገምግሟል፡፡ ስለሆነም ማንኛውም አይነት የስርዓት አልበኝነት አስተሳሰብ እና ድርጊቶችን ጉዳት ለሕዝባችን በማስረዳት ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ ቃል እንገባለን !!!

6ኛ- የጽንፈኝነት አስተሳሰብም ሆነ ድርጊት ለማንኛውም፤ ሀገር፤ ሕዝብ፤ግለሰብ፤ ባህላዊም ሆነ ሃይማኖታዊ እሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል አውዳሚ አደጋ ነው፡፡ ይህንን አውዳሚ አስተሳሰብ በወቅቱ የማከም እና የመግራት ተጨባጭ ስራዎች ካልተፈጸሙ የሀገራችንም ሆነ የክልላችንን ፖለቲካዊ፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በማመሰቃቀል እንደ ሀገር ዘላቂ ጉዳት ማስከተሉ አያከራክርም፡፡ በክልላችን አንዳንድ አካባቢዎችም በተጨባጭ እየሆነ ያለው ይኸው አሳዛኝ ሁነት ነው፡፡

See also  ከትግራይ የመጡ የሽብር ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ሥለሆነም የጽንፈኝነት አስተሳሰብና ድርጊቶች በሀገር ሉዓላዊነት እና በሕዝብ ሁለንተናዊ ኅልውና ላይ የደቀነውን ግልጽ አደጋ ለመቀልበስ በየደረጃው የሚገኘው የፓርቲያችን አመራር የጽንፈኝነት አስተሳሰብና ድርጊቶችን አደጋን በማጤን ፤ ራሱንም ከዚህ አደገኛ አስተሳሰብ ሰለባነት ታድጎ፤ የጽንፈኝነት አስተሳሰብና ድርጊትን የማክሰም ተግባር ከአንገብጋቢነቱ ባሻገር አጣዳፊነቱ ጭምር ተገንዝቧል፡፡

ስለሆነም የዚህ ኮንፍረንስ ተሳታፊ እና በሁሉም ደረጃ የሚገኝ አመራር መላ ሕዝባችንን በማስተባበር ክልላችንን ከጽንፈኛ አስተሳሰብም ሆነ ድርጊቶች አደጋ የጸዳ ክልል ለመፍጠር ቃል እንገባለን፡፡

7ኛ- በውስጥና በውጭ የሚገኙ አፍራሽ ኃይሎች ሉላዊው የሚዲያ ቴክኖሎጂ እድገትና የተደራሽነት እድልን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የአማራ ክልልን ለማተራመስ እና በወቅታዊ ጉዳዮች እየተናጠ ዘላቂ ጥቅሞቹን የሚያሳጡ፤ ሕዝብና አመራሩን የሚያቃቅሩ፤ በአመራሩ መካከል አለመተማመንን የሚፈጥሩ፤ ከእውነት የራቁና በክልሉ መሪዎች ላይ ጥላቻን የሚቀሰቅሱ አጀንዳዎችን በማራገብ ክልሉን መሪ አልባ ለማድረግ እረኛውን በመግደል በጎችን የመቀራመት ተኩላዊ ቀመር የተሰላ የአውሬ ተግባራትን እንደ ትግል ስልት ያለማቋረጥ እየተገበሩ መሆናቸውን እና ለዚህ አይነቱ የአፍራሾች የጥፋት ተግባር መስፋፋት በየደረጃው የሚገኘው አመራር ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለሕዝባችን ከመስጠት አኳያ የተስተዋለብንን ዳተኝነት መሆኑን ገምግመናል፡፡

በመሆኑም በየትኛውም የመንግስት መዋቅር ደረጃ ላይ የሚገኘው አመራራችን አመቺውን የመረጃ ማሰራጫ ዘዴዎችን በመጠቀም ተገቢውን ሁሉ መረጃ ለሕዝባችን በመስጠት ሕዝባችን ከአፍራሽ ኃይሎች መርዘኛ መረጃዎች ሰለባነት የመከላከል ስራዎችን በትጋት ከመከወን ጎን ለጎን፤ ሐሰተኛ መረጃዎችን ፤ የጥላቻ መልእክቶችን እና ሁከትና ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን በሚያሰራጩ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ላይ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራን ያለ አንዳች ማወላወል ለማስፈጸም የመሪነት ሚናችንን የምንወጣ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

8ኛ- የኑሮ ውድነት፤ ሥራ አጥነት፤ መልካም አስተዳደር ጉድለት፤ ሌብነት እና የብልሹ አሰራር ተግባርና አሰተሳሰብ በሕዝባችን እና በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገታችን ላይ እያሳደረ የሚገኘውን ጫና ከፍተኛ መሆኑን በኮንፍረንሳችን ገምግመናል፡፡ ስለሆነም ሕዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ እነዚህን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለማስወገድና የሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማክሰም ቃል እንገባለን ፡፡

9ኛ- የአማራ ሕዝብ ያደሩ ጥያቄዎችንም ሆነ አኹናዊ ዴሞክራሲያዊ መሻቶቹን ለማስተግበር ብቃት ያለው የአመራር ቁመና፤ ወቅቱ የሚጠይቀውን የመሪነት ስብእና የተላበሰ ጥራት ያለው የአመራር እና የአባላት ስብስብ የግድ ይላል፡፡ ከዚህ አንጻር የአመራርና የአባላቶቻችን ጥራት ሲመዘን ኃይላችን በአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ረገድ ዝንፈት የሚታይበት፤ የጎራ መደበላለቅና የሚና ብዥታ የሚስተዋልበት፤ ከሕዝብ አገልጋይነትም አንጻር የመንፈስ ዝለትና የስነ ምግባር ብክለቶች የተጠቃ መሆኑን ያለ አንዳች ሽንገላ ፈትሸናል፡፡ ስለሆነም እንደ አማራ ሕዝብ የምንሻቸውና የታገልንባቸው ፍትሐዊ ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተው ችግሮቻችን ይፈቱ ዘንድ አመራርና አባላችንን በውስጠ ድርጅታዊ አሠራር የማብቃት እና የማንጻት ሥራዎችን መከወን የግድ ይላል፡፡ በመሆኑም ከጽንፈኝነት የጸዳ ሥርዓት አልበኝነትን በግልጽ የሚታገል ፤በሕዝብ አገልጋይነት ስሜት የሚዋጅ የአመራር ግንባታ ተግባራትን ለመፈጸም ቃል እንገባለን !!!

በመጨረሻም፡- መላው የፓርቲያችን አመራሮች፤ አባላትና ደጋፊዎቻችን ላለፉት 3 ቀናት በአማራ ክልል ያጋጠሙ ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚቻልበትን መፍትሄ ለማስቀመጥ ባካሄድነው ኮንፍረነስ የደረስንባቸው ድምዳሜዎች ተግባራዊ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው የእናንተ ሙሉ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡

ስለሆነም በክልላችን ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ ያላሰለሰ ጥረታችሁንና ሁለገብ ሚናችሁን እንድትጫወቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

እንዲሁም፡- መላው የክልላችን ሕዝብ እና ኢትዮጵያውያን፤ ዲያስፖራዎች፤ ምሁራን እና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በለውጡ ሂደት ያገኘናቸውን ሀገራዊ እና ክልላዊ ድሎች ሳናሳንስም ሆነ ሳናዛንፍ በልኩ በመመዘን የተገኙ አንጻራዊ ድሎች እንዲቀጥሉና በአንጻሩ ደግሞ ድክመቶች እንዲታረሙ በማድረግ የገጠሙንን ፈተናዎች ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን ለማሻገር የበኩላችሁን አዎንታዊ ሚና እንድትወጡ ስንል የከበረ ጥሪያችንን እቀርባለን ፡፡

ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን!!!

ግንቦት 12/2015 ዓ/ም

ባሕር ዳር

Leave a Reply