የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የመኪና መገጣጠሚያ ማዕከል ሊገነቡ ነው

የሩሲያ የመኪና አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የመኪና መገጣጠሚያ ማዕከል ለመገንባት ማቀዳቸውን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጄኒ ተሬኪን ገለጹ፡፡

አምባሳደሩ ከኢዝቬሺያ ቢዝነስ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ÷በርካታ የሩሲያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይም የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የመኪና መገጣጠሚያ ማዕከል ለመገንባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከሩ ነው ብለዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2022 በሩሲያ እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እያደገ መምጣቱን ነው አምባሳደሩ ያመላከቱት።

ከኢትዮጵያ ወደ ሩሲያ ከሚገቡት ምርቶች ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ቡና ነው ያሉት አምባሳደሩ÷ ሩሲያ በ2022 ወደ ኢትዮጵያ ከላከቻቸው ምርቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ስንዴ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሩሲያ የነዳጅ ምርቶችን እና የወረቀት ምርቶችን ወደ ኢትዮጵያ እንደምትልክ አምባሳደሩ መናገራቸውን አር ቲ ዘግቧል።

ባለፈው ሳምንት የሩሲያ ግዛት የዱማ ሊቀ መንበር ቪያቼስላቭ ቮሎዲን ከኢትዮጵያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ መምከራቸው ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠቃሚ የሩሲያ አጋር እንደሆነች እና ከኢትዮጵያ ጋር ምንጊዜም መሰል ውይይት እንደሚደረግ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
ከ125 ዓመታት በላይ የቆየውን የሩሲያ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት ማስጠበቅ እንደተቻለም ተናግረዋል ሲል ፋና ዘግቧል፡፡

See also  "እኔ ምንም የለኝም ለሰዎች ልሰጥ የምችለው ብቸኛው ነገር ደስታ ነው"

Leave a Reply