ትህነግ የቡድን መሳሪያ ባስረከበ ማግስት ጦሩ ለተሃድሶ ካምፕ ገባ

የህወሓት ታጣቂ ሀይሎች የመጀመሪያው ዙር የተሀድሶና መልሶ የማቋቋም መርሀ ግብር ዛሬ ከመቀሌ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ኩሐ በይፋ ተጀምሯል። ይህ የሆነው የቡድን መሳሪያ ለሶስተኛ ጊዜ ርክክብ ከተደረገ በሁዋላ ነው። የትህነግ ታጣቂ ሀይሎች ተወካይ ብርጋዲየር ጀነራል ምግበይ ሀይለ “የሰላምና የልማት ሃይል ሁኑ” ብለዋል።

በርክክቡ ወቅት የትህነግ ወኪል ሆነው የቀረቡት ጀነራል ምግበይ ” የሚቆም ነገር የለም። የትግራይ ህዝብ መሳሪያ አያስፈልገውም” ሲሉ ተደምጠዋል። በየዕለቱ መተማመን መፈጠሩንም አመልክተዋል።

ይህንኑ ተከትሎ የተሃድሶ ሂደት በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑንን አውስተዋል።

“ታጣቂዎች በዚህ ሰላም ተጠቅማችሁ የራሳችሁን ህይወት መቀየርና፥ በክልሉ ብሎም በኢትዮጵያ ልማት መሳተፍ፤ የተፈጠረው ሰላምም ዘላቂ ለማድረግም መስራት ይኖርባችኅል” ሲሉም ለተሃድሶ የገቡትን አበረታተዋል።

መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ወደ መደበኛ ህይወታችሁ እስክትመለሱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ለተሀድሶ የገቡት እስኪቋቋሙ ድረስም ተገቢው ዕገዛ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።

የትህነግ ታጣቂ ሀይሎች ተወካይ ብርጋዲየር ጀነራል ምግበይ ሀይለ በበኩላቸው፤ “እናንተ የተሀድሶ መርሐ ግብርን አጠናቃችሁ ወደ ህብረተሰቡ ስትመለሱ የልማትና የሰላም ሀይል መሆን አለባችሁ” ብለዋል።

በመጀመሪያው ዙር የህወሓት ታጣቂ ሀይሎች ተሀድሶ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ስምምነቱ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ማረጋገጥ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል። የተጀመረው መርሀ ግብር የመጀመሪያ ዙር መሆኑ ተገልጾ በተመረጡ 10 ቦታዎች በተመሳሳይ የተሀድሶ መርሀ ግብሩ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

See also  ሁሉም የእርዳታ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩ የሃገሪቱን ህጎችና መመሪያዎች ማክበር አለባቸው --- ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ

Leave a Reply