በዩኬ የውሸት አባት ለመግዛት ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፍሉት ስደተኛ ነፍሰጡሮች በዩኬ

በርካታ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ጥገኝነት ጠያቂ ነፍሰ ጡሮች ለሚለወደው ልጅ የውሸት አባት በመግዛት ቪዛ ለማግኘት እንደሚሞክሩ በቢቢሲ ኒውስናይት የተሠራ የምርመራ ዘገባ አጋለጠ።

ድርጊቱ በምን ያህል ጥገኛ ጠያቂዎች የተፈጸመ እንደሆነ ለጊዜው መረጃ ባይኖርም፣ በርካታ ሴቶች በዚህ ዘዴ በዩኬ የመቆያ ቪዛ እንዳገኙ አመላካች ነው ተብሏል።

ነፍሰ ጡር እናቶች ለዚህ የውሸት አባት በአማካይ እስከ 10 ሺህ የዩናይትድ ኪንግደም ፓውንድ እንደሚከፍሉ ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል።

የውሸት አባቶች ገበያ

በዩኬ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዓመት የመኖርያ ፍቃድ እና ጥገኝነት ይጠይቃሉ። ከእነዚህ መካከል ገና የጥገኝነት ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ በእንጥልጥል ያሉ ብዙ ናቸው።

አንዳንዶቹ ደግሞ ነፍሰጡሮች ናቸው። ወይም ለዚሁ ዕድል ሲሉ ያረግዛሉ።

ምክንያቱም ነፍሰጡር መሆናቸው አዲስ የቪዛ በር ይከፍትላቸዋል።

አንዲት ስደተኛ ሴት ነፍሰ ጡር ከሆነች እና ያረገዘችው ከአገሪቱ ዜጋ ከሆነ በዩኬ የመቆያ ቪዛዋን ታረጋግጣለች።

በዩኬ ሕግ መሠረት በአገሪቱ ውስጥ የተወለደ ልጅ ከአባቱ ወይም ከእናቱ አንዳቸው ዜጋ ከሆኑ ልጁ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ዜግነትን ያገኛል።

እናትም የቤተሰብ ቪዛ በመጠየቅ በዩኬ የሚኖራትን ቆይታ ማራዘም ትችላለች።

በሂደትም ቋሚ መኖርያ እና ዜግነት ጥያቄ ለማቅረብ ትችላለች።

ለዚህም ነው የውሸት አባቶች ገበያ የደራው፣ ይላል የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ።

ይህ የውሸት አባቶች ገበያ በእርግጥ ያለ ነገር ነው ወይ? በሚል ቢቢሲ ጋዜጠኛውን አንዲት በሕገ ወጥ መንገድ በዩኬ የምትገኝ ነፍሰጡር ሴት መስላ እንድትተውን አሰማርቷል።

ይህቺ ጋዜጠኛ የዩናይትድ ኪንግደም ዜጋ የሆነ ወንድ ‘የውሸት አባት’ እንዲሆናት ደላላ ፈላጊ ሆና እንደትቅርብ ተደረገ።

እነዚህ የውሸት አባቶች በፌስቡክ በሚገኙ ደላሎች በኩል የሚገኙ ናቸው።

ከእነዚህ ደላሎች መካከል አንዱ ራሱን ‘ታይ’ ብሎ ይጠራል።

የቢቢሲ የምርመራ ቡድን አባል ታዲያ ሕገ ወጥ የዩኬ ነዋሪ ሆና፣ ነፍሰ ጡር እንደሆነች እና የውሸት ባል እንደምትፈልግ ለታይ ነገረችው።

የቢቢሲዋ ‘ነፍሰጡር እና ለልጇ የውሸት አባት ፈላጊ’ ከደላላ ታይ ጋር የተገናኙት በአንድ ካፌ ውስጥ ነበር።

See also  ያልተገረዛችሁ ተገረዙ!! አሉ ጌታቸው ረዳ

ደላላ ታይ ለዚች ሴት በጭራሽ ስጋት እንዳይገባት፣ ሂደቱ አልጋ በአልጋ እንደሆነ ቃል ገባላት።

ለልጇ የዩኬ ዜግነት ያለው የውሸት አባት እንዳገኘላት እና 8 ሺህ ፓውንድ እንደምትከፍል አግባባት።

“ምንም አጠራጣሪ ነገሮች እንዳይኖሩ በጥንቃቄ ነው ጉዳዩን የምንፈጽመው” ብሏታል።

ለዚች የቢቢሲ የምርመራ ቡድን አባል እና ራሷን ነፍሰጡር አድርጋ ለቀረበች ሴት ደላላ ታይ የተባለው ደላላ ‘አንድሩ’ የሚባል የዩኬ ፓስፖርት ያለው ሰው አገናኛት።

አንድሩ ይህንኑ ለማረጋገጥም የዩኬ ፓስፖርቱን አሳይቷታል።

የቪዛ መኮንኖች ቢጠራጠሩ እንኳ እነሱን ለማሳመን ፎቶ መነሳት ጠቃሚ ነው በሚልም ነፍሰጡር ነኝ ለልጄ የውሸት አባት እፈልጋለሁ ላለችው የቢቢሲ የምርመራ ቡድን አባል ፎቶዎችን አብሯት ተነስቷል።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ ለደላላው ምንም ዓይነት ክፍያ አልፈጸመችም።

ታይ በዚህ የውሸት አባት የማገናኘቱ ሂደት ላይ በድብቅ ካሜራ እየተቀረጸ የነበረ ሲሆን፣ የዩናይትድ ኪንግደም ፓስፖርት የነበረው አንድሩም በተመሳሳይ በዚህ ድርጊት ውስጥ ሲሳተፍ በካሜራ ተቀርጿል።

ቢቢሲ በኋላ ላይ ለምን በዚህ ወንጀል እንደሚሳተፉ ጠይቋቸዋል። ታይ ድርጊቱን መፈጸሙን የካደ ሲሆን አንድሩ ግን ለቢቢሲ ምንም ምላሽ አልሰጠም።

ሌላ በዚሁ የውሸት አባት ገበያ ውስጥ ልምድ እንዳላት የምትናገር እና ራሷን ‘ቲ ኪም’ ብላ የምትጠራ ሴት በሺህ የሚቆጠሩ ነፍሰ ጡር እናቶችን በዚህ ዘዴ በማገናኘት ቪዛ እንዳስገኘችላቸው ተናግራለች።

ይቺ ደላላ እንዳመነችው ከሆነ የዩኬ ዜግነት ላለው የውሸት አባት 10 ሺህ ፓውንድ እንደምትከፍል እና ለራሷ ግን እስከ 300 ፓውንድ ኮሚሽን እንደምትጠይቅ ተናግራለች።

ቲ ኪም ብላ ራሷን የምትጠራው የዉሸት አባቶች ዳላላ
የምስሉ መግለጫ,ቲ ኪም ብላ ራሷን የምትጠራው የዉሸት አባቶች ዳላላ

“ይህ ጥርሴን የነቀልኩበት ሥራዬ ነው፤ ምንም አሳሳቢ አይደለም። ለዩኬ ፓስፖርት አበቃሻለሁ” ብላታለች የቢቢሲን የምርመራ ዘጋቢ።

አና ጎንዛሌዝ በዩናይትድ ኪንግደም የኢሚግሬሽን ጉዳዮች ጠበቃ ናቸው።

“ይህ ጥንቅቅ ተደርጎ የሚፈጸም፤ ፖሊስም ሊደርስበት የማይችል የቪዛ ማግኛ ዘዴ ነው” ይላሉ።

“በሌላ መልኩ ሲታይ ደግሞ ሴቶች ቪዛ ለማግኘት የሚሄዱበትን ርቀት ማሳያም ነው” ባይ ናቸው።

በሕገ ወጥ መንገድ ዩኬ የገባች ሴት ከአገሪቱ ዜጋ ከሆነ ባል ልጅ ብታረግዝ ልጁ ወዲያው ዜጋ እንዲሆን ሕግ ያስገድዳል።

See also  አረንጓዴው ጎርፍ ሲታወስ፤ "የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስደሰት እስከመጨረሻው ተስፋ አልቆረጥኩም" ጉዳፍ ፀጋይ

እናት ልጇ የዩኬ ዜግነት ካገኘ በኋላ የመኖሪያ ፍቃድ መጠየቅ የምትችል ሲሆን፣ ይህም ዜግነትን ለመጠየቅ በር የሚከፍት ሂደት ነው።

“ይህ ሕግ የወጣው ልጆችን ለመጠበቅ ነው። ወደ ዩኬ በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ እናቶችን ለመጠበቅ አልነበረም ዓላማው” ይላሉ ሚስ ጎንዛሌዝ።

“የሕግ ከፍተት ተደርጎ መታሰብ የለበትም፤ ልጆችን ለመጠበቅ ለልጆች ሲባል የወጣ ሕግ ነው።”

ቢቢሲ በዚህ መንገድ ምን ያህል ሕገ ወጥ ስደተኞች ሐሰተኛ ባል ገዝተዋል የሚለውን መገመት ባይችልም ሂደቱ ግን የሚዘወተር እንደሆነ መረዳት ችሏል።

ባለፈው ዓመት ብቻ 4860 የቤተሰብ ቪዛ የተሰጠ ሲሆን፣ ይህም ልጅ የዩኬ ዜጋ በመሆኑ ሰበብ በዩኬ ለመቆየት የተሰጠ የቪዛ ብዛትን የሚያሳይ አሐዝ ነው።

በዩኬ ሕግ ሆን ብሎ ሐሰተኛ መረጃን ለቪዛ ሲባል መስጠት በእስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው።

የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያቤት ይህን ሐሰተኛ አባት ገበያን ያጋለጠውን የቢቢሲ ዘገባ ተከትሎ እንዳለው፣ እንዲህ ዓይነቱን ማጭበርበር ለመቆጣጠር የልደት ሰርተፍኬት ብቻ ሳይሆን አባት ነኝ የሚለው ሰው ትክክለኛ አባት ስለመሆኑ ማረጋገጫ ተጨማሪ ማስረጃዎችን እንጠይቃለን ብሏል።

የኢሚግሬሽን ጠበቃ የሆኑት ሃርጃፕ ባንጋል ይህ ነገር አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም ሳይሆን ለዓመታት የተሰጠ ነው።

እኚህ ጠበቃ እንደሚሉት በተለይ ይህ የሐሰት አባት ገበያ የሕንድ፣ የፓኪስታን፣ የባንግላዲሽ፣ የናይጄሪያ እና የሲሪላንካ ትውልድ ባላቸው የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች ዘንድ የሚዘወተር ነው።

ቢቢሲ መታዘብ እንደቻለው ደግሞ በበርካታ የቬትናም ተጠቃሚዎች በሚያዘወትሯቸው የፌስቡክ ገጾች በይፋ ጭምር የውሸት ባል እናገናኛለን የሚሉ የደላላ ማስታወቂያዎች እንደ አሸን ፈልተው ተገኝተዋል።

ደላሎቹ ብቻ ሳይሆን የውሸት አባት ፈላጊዎችም ጥያቄያቸውን በግልጽ ያቀርባሉ። ቢቢሲ ከተመለከታቸው ማመልከቻዎች አንዱ እንዲህ ይላል።

“የአራት ወር ነፍሰጡር ነኝ። የዩኬ ፓስፖርት ያለው የውሸት አባት እፈልጋለሁ፤ ዕደሜው ከ25 – 45 ቢሆን ይመረጣል።”

ሌላኛው ማስታወቂያ ደግሞ እንዲህ ይነበባል።

“የዩኬ ፓስፖርት ያለኝ ወንድ ነኝ። ነፍሰጡር የሆነች እና የውሸት አባት ለልጇ የምትፈልግ በውስጥ መስመር ታነጋግረኝ።”

በዩኬ ሕግ ለልጅ የልደት ካርድ ለማስወጣትም ይሁን ለልጅ የዩኬ ፓስፖርት ለማመልከት ዲኤንኤ ምርመራ አይጠየቅም።

See also  [የሽግግር መንግስት] ሊቋቋም ነው !!

ዘገባው የቢቢሲ ነው

Leave a Reply