ሞት አቀንቃኝ የግጭት ነጋዴዎች

የአማራ ክልል ሕዝብ ሕግ አክባሪ ሰላም ወዳድ ታላቅ ሕዝብ ነው። ሕዝቡ የሚፈልገው በሰላም ወጥቶ መግባት መልማት እንጅ የግል ጥቅሙ የተነካበት፣ ግጭትን የሕልውና ምንጩ ባደረገ የፍለጠው ቁረጠው መፎክር አስጨፋሪዎች ከሕግ ያመለጠ ወንጀለኛ ሁሉ ሕዝበኛ አመራርንና የሌሊት ወፎችን ተጠቅሞ ሰላሙ ከቀን ወደቀን ይደፈርስ በኢኮኖሚው ይዳቀቅ ዘንድ እንደማይፈልግና እንደማይፈቅድ ለማንም የተሰወረ አይደለም።

በአዲስ አበባ ከተማ ለራሳቸው ቡድናዊ ጥቅም ለውጡን ተከትሎ ለውጡን ለማደናቀፍ በአማራው በኩል ሲንቀሳቀሱ ከከረሙት የደም ነጋዴዎች መካከል በርካታዎቹ ከአዲስ አበባ ወጥተው አማራ ክልልን ምሽጋቸው እያደረጉ በአማራ ስም የአማራን ሕዝብ ለተጨማሪ መከራ ለመዳረግ በሕዝቡ ጥያቄ ከወንጀላቸው ለመንፃት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው።

እነዚህ የግል ጥቅማቸውን በአማራ ስም ለማስጠበቅ የሚፈልጉ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም ሞት አቀንቃኝ የግጭት ነጋዴዎች ብአዴንን እንደገና በመውለድ ቁጥር ሁለት ኢህአዴግን ለመፍጠር የነበራቸው እቅድ ከአንዴም ሁለት ሶስቴ የከሸፈባቸው ቢሆንም አሁንም በያዙት አቋም ፀንተው በመቆም(ለነገሩ ሌላው መስመር ግጭት ስለማይፈጥርላቸው ነው) ሕልማችን እውን ይሆናል ሲሉ በተለያዬ መንገድ መለፈፉን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል።

ብአዴናዊያኑን ለየት የሚያደርጋቸው እና ብዙሃኑን ሰው እንዲደናገርላቸው ያስቻለላቸው ብአዴንን በግብር ሆነውና ለብሰውት ሳለ በአፋቸው ብልፅግናን ብአዴን እያሉ መውቀስ መቻላቸው ነው።

ብአዴናዊያን በግብራቸው ስለሚከተሏቸው የብአዴን ተቃዋሚ የነበሩትንና ብልፅግናን በበጎ፣ ለውጡንም በባለቤትነት ሊመለከቱ የሚችሉትን፣ የብአዴን ተቃዋሚ መስለው ብልፅግናን ብአዴን በማስመሰል እየሰደቡና እየተራገሙ ወደፊት መጥተው ሚዲያውን በጩኸት በመቅጣጠር ፍላጎታቸውን ለማሳካት ባለ በሌለ አቅማቸው ተንቀሳቅሰዋል። በእነዚህ የተጭበረበረ ሐሰተኛ ጩኸት ብዙ ሰው ተሰናክሎ የነበረ ቢሆንም ብአዴንን ለመፍጠር ብልፅግናንን ብአዴን የሚሉ ብአዴናዊያን መሆናቸውን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየነቁ የመጡ እውነተኛ የአማሪ ሕዝብ ተቆርቋሪ ትክክለኛ የብአዴን ተቃዋሚዎች በመኖራቸው ይበል የሚያሰኝ ተስፋ ነው። እነሱን ያብዛልንም እንላለን!!

በነገራችን ላይ የሚፅፉትንም ሆነ የሚናገሩት ጉዳይ በደንብ የገባቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩ፣ እውነተኛ የአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪና የብአዴን ተቃዋሚ አማራዎች ብአዴን ሊከስም ሲልና ከስሞ ብልፅግና ሲፈጠር ልክ እንደ ሕወሓት ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ ሊገለገሉ አይገባም ነበር። ሲጀመር የተፈጠረው ብልፅግና የራሳቸው የትግል የመስዋዕትነት ውጤት ሆኖ ሳለ በደስታ ሊጨፍሩ እንጅ በሐዘን ሊቀመጡ ድንኳን ሊጥሉ አይገባምና።

See also  መፍትሔው የአባቶቻችን መንገድ መከተል ነው!(ረዘም ያለ የድርጊት ማመላከቻ)

ትናንት ከለውጡ በፊት ዘውጌ ብሔርተኝነትን እንቃወማለን ከመርህ አንፃር የብአዴን ተቃዋሚዎች ነን ሲሉ የነበሩ አማራዎች ከብልፅግና ይልቅ ብአዴን ይሻለናል(የፍላጎታቸው የግብራቸው መግለጫ ድርጅታቸው የሆኑት መብታቸው ሆኖ )ካሉ እነሱ ከመጀመሪያውም አንድም የብአዴን ተቃዋሚ ሳይሆኑ ባለ ሌላ ተልዕኮዎች አስፈፃሚ የነበሩ አለበለዚያ ደግሞ የሚቃወሙትንና የሚደግፉትን፣ ለምንና ለማን እንደሚታገሉ በቅጡ የማያውቁ፣መነሻና መዳረሻቸውን ያላወቁ የሐሳብ ጥራት የሌላቸው የማንም አልፎ ሂያጅ መጠቀሚያ ደመነብሳዊያን ስለመሆናቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
የአማራ ሕዝብ ደግሞ በእነዚህ የአጥፍቶ ጠፊ ሚና በማንም ሊሰጣቸውና በቀላሉ ሊተገብሩ በሚችሉ አካላት ላይ እጣፈንታው ሊወሰን ሰላሙን እያጣ ከልማት ርቆ ሊቀጥል አይገባም። ስለሆነም በተቃውሞው ጎራ የተሰለፈው የአብዛኛው መሪና ጭንቅላቱ ብልፅግናን ብአዴን የሚል ብአዴናዊያን ስለሆነና ነገሮች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ የአማራ ሕዝብ መቼም ቢሆን ሰላሙ የሚረጋገጥ እና ትኩረቱን ወደልማት የሚያዞር ባለመሆኑ እነዚህን አካላት አደብ ማስገዛት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል።

ትናንት ለ27 ዓመት ያላሰቡለትንና ያላደረጉለትን ለውጡ እንዳይፀና እና የአማራ ሕዝብ በለውጡ ተቋዳሽ እንዳይሆን ያሴሩበትን እነዚህን አካላት የአማራ ሕዝብ ዛሬ እነሱ ከስልጣናቸው ሲነሱ ጥቅማቸው ሲነካ እና በወንጀል የሚጠየቁ ሲመስላቸው ደርሰው የሕዝብ ተቆርቋሪ ስለመሰሉ፣ሻንጣ ተሸካሚ የግል አክቲቪስቶቻቸው ዩትዩበሮችና ቲክቶከሮች ሐጢያታቸውን ለመሸፋፈን አብዝተው ስለጮኹ እውነቱን አይቀየርምና ሕዝቡ ተሸውዶ ደጀናቸው ሊሆን አይገባም።አይችልምም።

ሕዝብ ሁሉንም ነገር ያውቃል። ሁሉንም ነገር መዝግቧል ይመዘግባልም። የሚጠቅመውንና የሚጎዳውንም ከራሱ በላይ የሚያውቅ የለም። ወንጀለኛና አመፀኛ ግለሰቦችን ሕዝባዊ አስመስሎ በመቀባባት ምሽጋቸው ሕዝብ እንዲሆን ጥረት ቢደረግም አይሳካም።በሕዝብ መስዋዕትነት የሚነፃ የግለሰብ ወንጀል አይኖርም። የአማራ ሕዝብ ፍርድና ፍትህ አዋቂ ስለሆነ ወንጀለኞችንና አመፀኞችን ለራሱ ሰላምና ልማት ሲል አሳልፎ ለሕግ ስለመስጠቱ ለመናገር ነብይ መሆንን አይጠይቅም።

የአማራ ክልል ሕዝብ ከእንግዲህ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚሉ ትናንት በበዘበዙት እና አንገት ባስደፉት ዛሬም ለተጨማሪ መከራ በሚያዘጋጁት የአብዮታዊ ደሚሞክራሲ ወይም ሞት አቀንቃኝ ብልፅግናን አምርረው በሚቃወሙ ብአዴናዊያን መሪነት በማፍያዎች በመንደር አውደልዳዮች በሰፈር ሙሴዎች ሰላሙን አጥቶ ከልማት ርቆ መኖርን ፈፅሞ አይፈልግም። ሰላሙ ተረጋግጦለት የቱሪዝሙ መስክ ተነቃቅቶለት ወደልማት መግባት ነው የሚፈልገው። ሰላሙንና ልማቱን ኦሊጋርኪዎች ይወስኑለት ዘንድ አሳልፎ አይሰጥም።

See also  ደጀን አለህ - ትልቁ ጥፋት

በአማራ ክልል ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ሲሰሩ እንደቆዩትና አሁንም አጠናክረው እንደሚሰሩት ያለ ጠላት ደግሞ ለአማራ ሕዝብ አለመኖሩን ማወቅ ያስፈልጋል!!

ሰላም ለሐገራችን!

footnote፥ ፅሑፉ በዋናነት በብልፅግና ውስጥ እና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ላሉ ብልፅግናን ብአዴን ለሚሉ ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም ሞት አቀንቃኝ ብአዴናዊያን እና ለእነሱ ሻንጣ ተሸካሚ የግል አክቲቪስቶቻቸው፣ ለማፍያ ደላላዎቻቸው እና የእነሱን እኩይ አላማ ለማስፈፀም በየሰፈሩ ለተፈለፈሉ የምድጃ ዳር ወሬ አመላላሽ የሰፈር ሙሴዎቻቸው ነው። ከእነዚህ ውጭ ለእኔም ነው የሚል ሰው ካለም የመውሰድ መብቱ የተጠበቀ ነው!!

ነሻ አስተያየት በቶማስ ጃጃው

Leave a Reply