አዋሳ በወ/ት ጽጌ ጠለፋ የተሳተፉ ስድስት ተጠርጣሪዎች ተያዙ

ሰሞኑን በአዋሳ ከተማ ወ/ሪት ጸጋ በላቸው የተባለች ወጣት በአንድ ግለሰብ የመጠለፏ ጉዳይ የማህበራዊ ድህረ ገጾች አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል።የከተማዋ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ በዛሬዉ እለት ባወጣዉ መግለጫ ፥ ከጠለፋ ወንጀሉ ጋር የተጠረጠሩ 6 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አስታዉቋል፡፡

የወንጀሉ ድሪጊት የተፈፀመው በሐዋሳ ከተማ በመናኸሪያ ክ/ከተማ መሆኑን የከተማው ፖሊስ ገልጿል፡፡በዚህም ወ/ሪት ፅጌ በላቸው የተባለች ግለሰብ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ቤተሰቦቿ ተጠልፋ የት እንደደረሰች አናውቅም በማለት ለመነኸሪያ ክ/ከተማ ፖሊስ ባቀረቡት ማመልከቻ መሰረት ምርመራ መጀመሩ ተገልጿል።

ይህን ተከትሎ መምሪያው ተፈፀመ በተባለዉ ወንጀል መሰረት ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ብርቱ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡በዚህም ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ጭምር አስፈላጊውን ጥረት እያደረግኩ ነው ብሏል፡፡ከወ/ሪት ፅጌ በላቸው የጠለፋ ወንጀል ጋር የተጠረጠሩ ሥድስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ተጠርጣሪው ሣጅን የኋላ መብራቴ እና የተጠለፈችውን ወ/ሪት ፅጌ በላቸው ይዞ ከተሰወረበት ቦታ አድኖ ለመያዝ ጥረትና ክትትል እየተደረገ ነውም ብሏል ፖሊስ።ህብረተሰቡ የሚችለውን ሁሉ በ09 64 50 46 77 እና 09 69 41 52 72 ስልክ ቁጥሮች ጥቆማ እንዲሰጥ የከተማዋ ፖሊስ ጠይቋል ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ፖሊስን ዋቢ አድርጎ ሽፏል፡፡

የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕ ፀጋዬ ቱኬ የወ/ሪት ፀጋ በላቸው ጠለፋ ወንጀሉን አስመልክተው፣ ከወ/ት ፀጋ በላቸው የጠለፋ ወንጀል ጋር በተያያዘ በተለያዩ የማኀበራዊ ሚድያዎች የተዘገበው አስነዋሪ ድርጊት ከተማ አስተዳደሩ ጥቆማ ከቀረበበት እለት ጀምሮ ጉዳዩን በልዩ ትኩረት እየተከታተለዉ እንደሚገኝ አስታወቁ ገልጸዋል፡፡ በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠረው ግለሰብ የልዩ ኃይል አባል የነበረና በመንግስትና ህዝብ የተሰጠውን ታላቅ ኃላፊነት በማይመጥን መልኩ የተጠረጠረበትን ወንጀል መፈጸሙን ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።

በወንጀሉ ላይ ፖሊስ መረጃ ከደረሰዉ ግዜ ጀምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከከተማችን ፖሊስ፣ ከሲዳማ ፖሊስና ከክልላችን ሰላምና ጸጥታ ጋር በመቀናጀት ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት አላቸዉ ተብለዉ የተጠረጠሩ 6 ሰዎችን ይዞ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ፖሊስ እንዳረጋገጠው ሁሉ እሳቸውም ማረጋገጫ አቅርበዋል፡፡

See also  የውጭ ብድር ያነቃት ኢትዮጵያ!! "እዳዋን እንዴት ትክፈል?"

ተጠርጣዉ ግለሰብ ከከተማ ወጥቶ የተሰወረ በመሆኑ ከክልላችን የሰላምና ጸጥታ ቢሮና ከክልላችን ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በልዩ ትኩረት እየሰራን ያለን በመሆኑ ዉጤቱን ለህዝባችን በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ አያይዘውም የተፈጸመዉ የወንጀል ድርጊት ከከተማ አስተዳደሩም ሆነ ከሲዳማ ህዝብ ጋር ምንም የማይገናኝና ፈጻሚ ግለሰብ ብቻ የሚጠየቅበት በመሆኑ መላው ህዝባችን ከዚህ ቀደም በተለመደው ወንጀልን በመከላከልና የከተማችንን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቁ ከጸጥታ አካሉ ጎን በመሆን የከተማችንን መልካም ስምና ገጽታ የሚያጎድፉ ድርጊቶችን የመጠበቅ ስራውን አጠናክሮ እንዲሰራ አሳስባለሁ ብለዋል። ወንጀል ፈጻሚ ማንም ይሁን ማን በህግ ተጠያቂ እንዲሆን አበክረን እንሰራለን ማለታቸው የደረሰን ዜና ይጠቁማል።


Leave a Reply