Site icon ETHIOREVIEW

“ፅንፈኛ” ከሚባለው ሃይል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መከላከያ እያደነ መሆኑንን አስታወቀ – “በደብረ ኤልያስ ወረዳ ሰላም ሰፍኗል”

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ በፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ በተወሰደ እርምጃ የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል እየተሠራ መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።

መንግሥት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሰላም ተመልሶ የግብርና ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን የአካባቢው አርሶ አደሮች መግለጻቸው ይታወሳል።

በመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ 403ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አዘዘው መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት በደብረ ኤሊያስ ወረዳ በስላሴ ገዳም አካባቢ የታጠቀ ፅንፈኛ ኃይል መሽጎ ነበር።

በገዳሙ የመሸገው ኃይል ችግር ለመፍጠር በማለም ተጨማሪ ኃይል በማሠልጠን እና በማደራጀት ሲሠራ መቆየቱን በተገኘው መረጃ ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።

የአካባቢውን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት አንቅስቃሴዎችን ከማስተጓጎሉም በላይ የፀረ-ሰላም ኃይሉን አስተሳሰብ የማይቀበል ግለሰቦችን ሲገድሉ እንደነበረም አስታውሰዋል።

መከላከያ ሠራዊት ሕግ ለማስከበር ወደ አካባቢው ሲገባም ቀድሞ ባዘጋጀው ምሽግ ውስጥ በመደበቅ እና ተኩስ በመክፈት ሥርዓት አልበኝነቱን አሳይቷል ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ፀረ-ሰላም ኃይሉ የተመታ ሲሆን ተንጠባጥቦ በመሸሽ ላይ ያለውን የመከታተል ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከአካባቢው መስተዳድር እና ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበርም የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግም ከፅንፈኛ ኃይሉ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሰላም እና ደኅንነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ላቃቸው አብጠው የተገኘውን ሰላም ለማጽናት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በአካባቢው የፀረ-ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ መስተዋል ከጀመረ የቆየ ቢሆንም ችግሩ እየተባባሰ እና ሥርዓት አልበኝነቱ እየተስፋፋ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በአመለካከት የማይደግፏቸውን ንፁሃን ዜጎች፣ አመራሮች እና የሃይማኖት አባቶችን ሲገድሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ገዳሙ ትክክለኛ የሃይማኖት ስፍራ እንዲሆን ከጠቅላይ ቤተክህነት እና ከዞኑ ሀገረ ስብከት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያው ምስሎችን በመቆራረጥ እና በማገናኘት ገዳሙ እንደወደመ ተደርጎ የሚነዛው ወሬ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን ሁሉም ሕዝብ ሊያውቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አሁን የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድርግም ሕዝቡ ሃይማኖትን ሽፋን በማድርግ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ማጋለጥና መታገል አለበት ሲሉም አሳስበዋል።

Exit mobile version