ከ3.2 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በምድር ላይ ትኖር የነበረችው የሰው ልጆች ቀደምቷ ሉሲ ቀጥ ብላ ትራመድ ነበር ሲሉ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ገለጹ።
ቅሪተ አካሏ እአአ 1974 በኢትዮጵያ የተገኘው ሉሲ በምድር ላይ ሳለች እንቅስቃሴዋ እንዴት እንደነበረ ምርመራዎች ተደርገው ውጤቱ ትናንት በሮያል ሶሳይቲ ኦፕን የሳይንስ ጆርናል ላይ ታትሟል።
ተመራማሪዎች ታዲያ ሉሲ ቀጥ ብላ ከመራመዷ በተጨማሪ በዚህ ዘመን እንዳሉት የጦጣ ዝርያዎች በዛፎች ላይ መኖር ትችል እንደነበረ ቅሪተ አካሉን መርምረን ደርሰንበታል ብለዋል።
ይህም ማለት ሉሲ የነበራት የሰውነት አቋም በአሁኑ ወቅት ካለ ከየትኛው ፍጥረት ጋር ተመሳሳይነት የለውም።
የሰው ልጆች እግሮቻቸው ቀጥ ብለው ስለሚቆሙ ሚዛናቸውን ጠብቀው ይቆማሉ፤ የጦጣ ዝርያዎች ግን ሊቆሙ ቢሞክሩ እግሮቻቸው ሙሉ በሙሉ ተዘርግተው ቀጥ ብለው መቆም አይችሉም።
በዚህም ምክንያት እጅ እና አግሮቻቸውን በጋራ በመጠቀም መንቀሳቀስን ይመርጣሉ ይላሉ ተመራማሪዎች።
ሉሲ ግን ከሰው ልጆችም ሆነ አሁን ላይ ካሉት የጦጣ ዝርያዎች በመለየት በሁለት እግሯ መራመድ ትችላለች። እንዲሁም በዛፎች ላይ መኖር ትችላለች።
አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ የሰው ዝርያ የምትመደበው ሉሲ 40 በመቶ የሚሆነው ቅሪተ አካሏ መገኘቱ ይታወሳል።
- በ2016 ረቂቅ በጀት ላይ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ዕይታከ 8 ሰአት በፊት
- ትግራይ፡ ‘ወይ አይገድል ወይ ነፍስ አይዘራ፣ ጥቂት እርዳታ ስንጠብቅ ሳር አከልን’ከ 8 ሰአት በፊት
- በአማራ ክልል በፀጥታ ኃይሎች እና በነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸከ 7 ሰአት በፊት
በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተመራማሪዎች በቴክኖሎጂ እገዛ የታችኛው የሰውነት ክፍሏን ዲጂታል ሞዴል ሠርተዋል።
ተመራማሪዎቹ ሉሲ የጉልበት መገጣጠሚያዎቿን መዘርጋት ትችላለች ሲሉ ደምድመዋል።
ይህም ሉሲ ቀጥ ብላ መቆም እንደምትችል እና ሳር የሚያድግበት ሜዳማ አካባቢ መኖር ትችል እንደነበር የሚያረጋግጥ ነው።
ሉሲ ቁመቷ አንድ ሜትር ገደማ ሲሆን፤ የአእምሮዋ መጠን ደግሞ አሁን ላይ በምድር ከሚኖረው የሰው ልጅ አእምሮ ሲሶውን ብቻ የሚያክል ሲሆን የፊቷ ቅርጽ ደግሞ ከጦጣ ዝርያ ጋር የሚመሳሰል ነው።
አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ዝርያዎች ላይ ምርመራ ማድረጉ የሰው ልጆች በሁለት እግር ቀጥ ብሎ መራመድ እንዴት እንደጀመሩ ምልክታ ይሰጣል ይላሉ ተማራማሪዎች።

የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የሠሩት የሉሲ የታችኛው ክፍል ሰውነት ዲጂታል ሞዴል፤ ሉሲ አሁን በምድር ላይ ካሉት የሰው ልጆች በበለጠ አብዛኛው የታችኛው የሰውነት ከፍሏ ጡንቻ መሆኑን አሳይቷል።
የሰው ልጆች ታፋ 50 በመቶ ጡንቻ ሲሆን የሉሲ ግን 75 በመቶ የሚሆነው ጡንቻ ነበር። ይህም አስቸጋሪ በሆኑ የመሬት አቀማመጦች ያለ ችግር እንድትንቀሳቀስ ይረዳት ነበር ብለዋል።
በአፋር ክልል ለተገኘችው አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ዝርያ ‘ድንቅነሽ’ የሚል የአማርኛ መጠሪያ የተሰጣት ሲሆን ‘ሉሲ’ የሚለውን የእንግሊዝኛ መጠሪያ ደግሞ ያገኘችው ከቢትልስ የሙዚቃ ቡድን ‘ሉሲ ኢን ዘ ስካይ ዊዝ ዳይመንድስ’ ከሚለው ዘፈን ነው።
የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች የሉሲን ቅሪተ አካል ሲያገኙ ይህን የቢትልስ ሙዚቃ በከፈቱት ቴፕ ሬኮርደር እየተጫወተ ነበር።
ቢቢሲ አማርኛ