የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዓመቱ 200 አውሮፕላን አብራሪዎችን እንደሚያስለጥን አስታወቀ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ 200 አውሮፕላን አብራሪዎችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ለማስገባት መዘጋጀቱን ገልጿል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት በአየር ትራንስፖርቱ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ሰፊ የመሰረተ ልማት እና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

ብዙ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች በኮቪድ ምክንያት ሰራተኞቻቸውን በመቀነሳቸውና ገበያው ላይ አዳዲስ የሰው ኃይል ባለማግኘታቸው እየተፈተኑ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ነባሮቹን ባለመቀነስና አዳዲስ ባለሙያዎችን በማፍራት በስኬቱ ቀጥሏል ነው ያሉት።

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2035 የረጅም ጊዜ ዕቅዱ የያዘውን ራዕይ ለማሳካት በኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ 1 ሺህ 100 ተማሪዎች በተለያዩ ሙያዎች እየሰለጠኑ መሆኑን ገልጸዋል። ይህንን ዕቅዱን በማስፋትም በቀጣይ ዓመት 1 ሺህ 600 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን መዘጋጀቱን ነው የጠቀሱት።

አየር መንገዱ ዘንድሮ ከ170 በላይ አውሮፕላን አብራሪዎችን አስመርቆ ወደ ስራ ማስገባቱን ጠቅሰው፤ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ነው ብለዋል።

ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ 200 አውሮፕላን አብራሪዎችን ለማፍራት ዕቅድ መያዙንም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ያስታወቁት።

ለዚህም ጥር ወር ላይ የተመረቀው የሀዋሳ የአውሮፕላን አብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተቋማዊ ስኬቱ ጠንካራ የስራ ባህል ግንባታን ከሰራተኞች ጥቅም ጋር አስተሳስሮ እየተጓዘ መሆኑን ነው የተናገሩት። በዚህም የ17 ሺህ ቋሚ ሰራተኞቹን የማስጠበቅ ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በዚህም ሰራተኞች በራሳቸው ወጪ መኖረያ ቤት እንዲሰሩ ሲያስተባብር መቆየቱን ለአብነት ጠቅሰው፤ በመጀመሪያው ዙር ለ5 ሺህ ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት የሚሆኑ ባለ 20 ወለል ህንጻዎች ግንባታ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በቅርቡ ይጀመራል።

……..

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት የ20 በመቶ ገቢ ጭማሪ ማግኘቱን ሰሞኑንን ማስታወቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት የ20 በመቶ ገቢ ጭማሪ ማግኘቱን ማስታወቁን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ናቸው ተቋሙን ጠቅሰው የዘገቡት። አየር መንገዱ ዘንድሮ ያገኘው ገቢ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ሲኾን፣ ባለፈው ዓመት ገቢው ግን 5 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ተገልጧል። የአየር መንገዱ ሥራ አስፈጻሚ ኩባንያው ካቀደው ትርፍ የበለጠ ሊያገኝ እንደሚችል ጠቁመዋል ተብሏል። አየር መንገዱ፣ በተያዘው በጀት ዓመት 13 ነጥብ 7 ሚሊዮን መንገደኞችንና 723 ሺህ ቶን ካርጎ ማጓጓዙን እንደገለጠ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። አየር መንገዱ ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት ወደነበረበት አቅሙ መመለሱን ስራ አስፈፃሚው ከቀናት በፊት መግለጣቸው ይታወሳል።

See also  የጭካኔ ጥግ - በጣርማ በር መዘዞ

Leave a Reply