Site icon ETHIOREVIEW

ብሔራዊ ባንክ ለአምስት የውጭ ባንኮች ፈቃድ ሊሰጥ ነው፤ የአገር ውስጥ ባንኮች ከፍተኛ ዝግጅት እንዲያደርጉ ተባለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አምስት የውጭ አገር ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው ፈቃድ ለመስጠት ተዘጋጅቷል፡፡ አገር በቀል ባንኮች ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ እና ቀድሞ የነበራቸውን ስትራቴጂ መከለስ እንዳለባቸውም አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የገንዘብ ተቋማት ዘርፍ ምክትል ገዥ አቶ ሠለሞን ደስታ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትን ከማጠናከር ጎን ለጎንም የውጭ ባንኮችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ ነው።

‹‹ሥራውን አሁን እያጠናቀቅን ነው። አዋጁን የመከለስ ሥራውንም እያጠናቀቅን ነው:: ከለጋሾች አንዳንድ ግብዓቶችን እየጠየቅን ነው። በወራት ዕድሜ ለህዝብ እንደራሴዎች ይቀርባል:: ስለዚህ ስራው እየተፋጠነ ነው” ብለዋል አቶ ሠለሞን።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ የውጭ ባንኮች ፈቃድ ለመስጠት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሠለሞን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ገዥው ገለጻ፤ የውጭ ባንኮች የአገር ውስጥ ባንኮችን ከገበያ እንዳያስወጧቸው የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት አቅም ግንባታ ላይ ሊሰሩ ይገባል፤ለዚህም የተቀመጠ አሰራር መኖሩን አመልክተዋል።

ተቋማቱ ከመደበኛ በጀታቸው ሁለት ከመቶ የሚሆነውን ለአቅም ግንባታ እንዲያውሉትና ይህም ለባንኮች ከረጅም ዓመታት በፊት የተላለፈ መሆኑን፣ አሁንም ድረስ በዚሁ አግባብ ክትትል እንደሚደረግ አቶ ሠለሞን አስረድተዋል።

አሁን ቀድሞ እንደተለመደው መሄድ አይቻልም ያሉት አቶ ሠለሞን፣ ሪፎርም ከተደረገ ወዲህ ብዙ አዳዲስ ነገሮች አሉ፤ በጀት ተመድቦም በሰፊው መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

Exit mobile version