Site icon ETHIOREVIEW

በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ ግዙፏ “ዓባይ ፪” መርከብ አቀባበል ተደረገላት

በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ ግዙፍ ናት የተባለችው “ዓባይ ፪” መርከብ በዛሬው ዕለት በጅቡቲ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት አቀባበል ተደርጎላታል።

በስነ ስርዓቱ ላይ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የጅቡቲ ሪፐብሊክ የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ሀሰን ኢብራሂም፣ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት የሺፒንግ ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ ካፒቴን ወንድወሰን ካሳ እና የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

“ዓባይ ፪” መርከብ በቻይናው ያንግዡ ዳያንግ ሺፕ ቢዩልዲንግ የተገነባች ሲሆን፤ 200 ሜትር ርዝመት እና 63,229 ቶን የመጫን አቅም እንዳላት ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ታሪክ በግዙፍነቷ አቻ የለሽ የሆነቸው ይህች መርከብ የባሕር ትራንስፖርት ስራን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደምታሸጋግርም ተጠቅሷል።

“ዓባይ ፪” መርከብ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ድርጅትን ለኪሳራ ዳርገው በነበሩት 42,000 ቶን የመጫን አቅም ባላቸው ሁለት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የተቀየረች መሆኗን የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።

ኢዜአ ባይዘግበውም መንግስት በድብቅ የኢትዮጵያን መረከቦች እየሸጠና የባህር ትራንዚት ዘርፉን በመግደል አገሪቱን እያራቆተ እንደሚገኝ በስፋትና በዘመቻ ሲዘገብ መሰበቱ ይታወሳል። መርከቦቹ አክሳሪ የሆኑ እንደነበሩ ባህር ትራንዚት ከቀናት በፊት በሶስት ባለሙያዎቹ ሰፊ ማብራሪያና ሙያዊ ትንተና ቢሰጥም ” የኢትዮጵያ መርከቦች ተሸጡ” ሲሉ የነበሩ አካላት ማስተባበያም ሆነ ማስተካከያ አላደረጉም።

Exit mobile version