- የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት በቅርቡ አዲስ አበባ ይመጣሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፓሪሱ አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ ላይ ለአፍሪካውያን የሚደረገው የልማት ፋይናንስ ድጋፍ እንዲጨምር በአፅንኦት መጠየቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከልዑካን ቡድናቸው ጋር ለሁለት ቀናት በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም፤ ኢትዮጵያ በጉባኤው ስለነበራት ተሳትፎና ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካይነት በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ላይ አቋሟን ያንጸባረቀችበት እንዲሁም የአፍሪካውያንና የታዳጊ ሀገራትን ድምፅ ያሰማችበት ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር አፍሪካ ተደራራቢና ውስብስብ የሆኑ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት፣ የዕዳ ጫና እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ላመጣቸው ቀውሶች ተጋላጭ መሆኗን ማንሳታቸውንም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሀገራት ፍትሐዊ እና ዘላቂ ዕድገት እንዲኖራቸው የፋይናንስ አቅርቦቱ መሻሻል እና መጠናከር እንዳለበት የኢትዮጵያን ግልፅ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ነው ያብራሩት።
በተለይም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን የበለጠ ተራማጅ ማድረግ እንደሚገባ መጠቆማቸውንና ከዚህ ቀደም ቃል የተገቡ ስምምነቶችን መተግበር እንዳለባቸው መናገራቸውንም እንዲሁ።
በተለይ ለአፍሪካ አገራት ሊሰጡ የታሰቡ የልማት ፋይናንስ ድጋፎች በተጨባጭ ፈሰስ እንዲደረጉና አቅርቦቱም እንዲጨምር በአፅንኦት ጠይቀዋል ነው ያሉት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መሆኗን ለጉባኤው ማቅረባቸውን ያነሱት ቢልለኔ፤ ወደ አረንጓዴ ልማት ሽግግር ለሚያደርጉ አገራት የበለጠ የገንዘብ ድጋፍ መደረግ እንዳለበት መጠቆማቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጻቸው ኢትዮጵያ በስንዴ ልማትና በአረንጓዴ አሻራ አመርቂ ውጤቶችን ማምጣቷንም ለጉባኤው አብራርተዋል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በግብርናውና በሌሎችም መስኮች የጀመረቻቸው የልማት ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ በራስ አቅም ከሚደረገው ጥረት ባሻገር ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፋቸውን በማጠናከር የታሰበው ዕድገት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሳካ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ስለመወያየታቸውም ቢልለኔ ገልጸዋል።
በዚህም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ፣ ከአዲሱ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ከፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ከአፍሪካውያን መሪዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምምነቶች ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በውጤታማነት እያደገ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በፓሪሱ አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ ለታዳጊ ሀገራት የሚሰጠው የልማት ፋይናንስ እንዲጨምር ስምምነት ላይ ተደርሷል- የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ
ፓሪሱ አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባዔ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለታዳጊ ሀገራት የሚሰጠው የልማት ፋይናንስ እንዲጨምር ስምምነት ላይ መደረሱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከሀገራት መሪዎችና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግላትና አዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ የልማት ፋይናንስ ድጋፍ እንድታገኝ ስምምነት ላይ መደረሱንም ገልፀዋል።
አዲስ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት የመሪዎች ጉባዔ ባለፉት ሁለት ቀናት በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ተካሂዷል።
ጉባዔውን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፤ አፍሪካውያንን ጨምሮ ለታዳጊ ሀገራት የሚደረገው የልማት ፋይናንስ አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር በጉባዔው ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ለዚህም የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ)ን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ድህነትን ለመቀነስ የሚደረጉ የልማት ፕሮግራሞች ከፍተኛ የፋይናንስ ፈሰስ እንዲያደርጉና ይህንን ያማከለ ሪፎርም እንዲያካሂዱ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።
በጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥን በሚመለከት ከዚህ ቀደም የተደረሱ ስምምነቶች ወደ ተጨባጭ የተግባር ምዕራፍ እንዲገቡም ውሳኔ መተላለፉን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ብዙ ታዳጊ ሀገራት በኮቪድ ወረርሽኝ፣ በዩክሬንና ሩስያ ጦርነት እና በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መዋዠቅ ምክንያት ጫና ላይ በመውደቃቸው፤ የዕዳ ቅነሳ እና ሽግሽግ እንዲደረግላቸው መግባባት መፈጠሩን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያም በዚህ የዕዳ ጫና ቅነሳና ሽግሽግ ውሳኔ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እንደምትሆን ነው የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመድረኩ ስለ ሀገራዊ ሪፎርሙ ስኬትና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን አቅርበው አድናቆት ተችሯቸዋል ነው ያሉት።
በቀጣይ መርሃ-ግብሩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፍ ከተደረገለት ኢትዮጵያ በቀጣናውና በአፍሪካ ለማስፋት የጀመረችውን ጥረት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አንስተዋል ብለዋል።
በግብርናው መስክ ከውጭ የሚገባ ስንዴን ከማስቀረት ባሻገር ለጎረቤት ሀገራትና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኤክስፖርት ማድረግ መጀመሩም በመድረኩ አድናቆት ተችሮታል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባዔው በተጓዳኝ ከተለያዩ ከሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር በመወያየት በልማት ፋይናንስ ድጋፍና ሌሎችም የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በተደረገው ውይይት፤ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግ፣ የሚሰጣት የፋይናንስ ድጋፍ እንዲጨምር በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እገዛ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአዲሱ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት አጃይ ባንጋስና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጄቫ ጋር ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
አዲሱ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት በቅርቡ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ መግለጻቸውንና የኢትዮጵያ ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና ሰፋፊ የልማት ፕሮግራሞች እንዲሳኩ የዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግባባት ላይ መደረሱን ነው ያብራሩት።
በተያያዘም አይ ኤም ኤፍ ኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ያላትና ውጤታማ ልማት እያከናወነች መሆኗን እንደሚገነዘብ እንዲሁም የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግላትና የማክሮ ኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲሰጣት ፍላጎት እንዳለው ክሪስታሊና ጆርጄቫ አረጋግጠዋል ብለዋል።
በዚህ ደረጃ ከተቋሙ ጋር የሚደረጉ የማክሮ ፕሮግራም ውይይቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የፕሮግራም መጠኑና ይዘቱ በስምምነት እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም የአየር ንብረት፣ በግብርና ምርት፣ በቀጣናዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ያላት የመሪነት ሚና በጉባዔው ከፍተኛ ሥፍራ እንደተሰጠው የገንዘብ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ሰላሟንና ውስጣዊ አንድነቷን በማጠናከር ፊቷን ወደ ልማት በማዞር ሁለተኛ ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዘጋጀቷ አድናቆት እንደተቸረው ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ በጉባዔው በባለብዙ ወገን፣ በሁለትዮሽ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምምነቶች ላይ መደረሱን ተናግረዋል። የዓለም ባንክ ሊቀመንበር በቅሩ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ አመልክተዋል።
ዜናው የኢዜአ ነው