Site icon ETHIOREVIEW

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የከፍታ ጉዞ

በአሜሪካዊያኖቹ የኦልቪራይት ወንድማማቾች ፈጠራ ለአለም የተበሰረው የአቭዬሽን እንዱስትሪ በአስገራሚ ፍጥነትና የሳይንሱ ምጥቀት ታግዞ ዛሬ ከድምፅ ፍጥነት በላቁ ፈጣን የውጊያ ተዋጊ ጄቶችን ጨምሮ ወደ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የድሮን ቴክኖሎጂ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማደግ ችሏል።

ከግማሽ ትሪይለን ዶላር በላይ በዓመት የሚንቀሳቀስበት ይህ የእንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገራት የጡንቻቸው መለኪያ ሚዛን ከመሆንም አልፎ በአለም የኃይል አሰላለፍም ተፅእኖው እየጎላ መጥቷል።

በዚህም ተጨባጭ የአለም ነባራዊ ሁኔታውም የሚያሳየው ነገር ቢኖር ያለዘመናዊ አቭዬሽን ተቋም ግንባታ በአሁን ጊዜ ዘላቂ ሰላምም ሆነ አስተማማኝ ልማት ማረጋገጥ ከቶም የማይታሰብ ወደ ቴክኖሎጂው ሽግግሩም በፍጥነት ካልተገባ የሚያስከትለው ጉዳትና መዘዙም የዛኑ ያህል የከፋ ነው።

እንደ ኢትዮጵያዊያን ዘመን አቆጣጠር በ1920ዎቹ መጀመሪያ አከባቢ ሀገራችንም በይፋ ወደ አቭዬሽን ኢንዱስትሪ መግባቷን ያረገጠችበት ቴክኖሎጂውንም ከታጠቁ ጥቂት የአለም ሀገራት መካከል አንዷ ለመሆን በቅታለች።

አየር ኃይላችንም በወቅቱ ከአፍሪካ ብቸኛው ተቋም ነበር

የሀገራችንን የአየር ክልልና ስፔስ እንዲሁም የግዛት አንድነታችን በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ ዋነኛ ተልዕኮው የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተቋቋመበት ዕለት ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜው ትውስታችን በሆነው የሀገር ህልውና ዘመቻችንም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ታለቅ መስዋዕትነት የከፈለ የሀገሪቱ አንጋፋው የአቭዬሽን ተቋም ነው።

ተቋሙ ምንም እንኳን ከአመሰራረቱ የረዥም ዓመት ታሪክ ያለው ቢሆንም በየወቅቱ የመንግስታቶች መቀያየርና ከፖለቲካ ተፅእኖም ነፃ ሆኖ ካለመዝለቁ ጋር ተያይዞ በአንድም ይሁን በሌላም ምክንያት የእድሜውን ያህል ደረጃውን ጠብቆ አድጓል ማለት አይቻልም።

ንጉሱ በስልጣን ዘመናቸው በአለም የአቭዬሽን ኢንዲስትሪ መስክ ልዩ ስምና ዝና ካላት ከታላቋ አሜሪካ ጋር ጥብቅ ወዳጅነትና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ስለነበራቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአንፃራዊነት ሞዴል የሆነና መልካም የሚባል መዋቅራዊ አደረጃጀት የነበረው ተቋም ነበር።

ከንጉሱ የስልጣን መውረድ በኃላ ቀጥሎ የመጣው ወታደራዊ መንግስት ግን ከሚከተለው የሶሻሊዝም ርዕዮት አለም የተነሳ ወደ ምስራቁ ጎራ መቀላቀሉ ከጅምሩ ጠንካራ ለነበረው የተቋሙ ተልዕኮ ላይም የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ መፍጠሩ አልቀረም።

እናም በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ከሶቭዬቶች ጉያ ስር የተወሸቀው አየር ኃይላችን ኢምፔሪያሊዝም ይውደም ከሚል መፈክሩ ጋር ታጅቦ የሀገር አንድነቱን ለማስጠበቅ ቢፍጨረጨርም ነገሮች ከአቅሙ በላይ ሆኖ ሊሳካለት አልቻለም።

ከድህረ ደርግ በመለስ ያለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ግን በተለይም እስከ ሀገራዊ ለውጡ ድረስ ያለውን መዋቅራዊ ሁኔታን ስናየው ከአቭዬሽን ስልጣኔ ጋር የተኳረፈ ይመስል ተልዕኮን በመፈፀም ብቃትና በሌሎችም የአቭዬሽን ቴክኖሎጂ መስፈርቶች ኃላ ቀርና ለዚች ታላቅ ሀገር የማይመጥን ነበር።

ይህም የሆነበት ዋነኛው ምክንያት የወቅቱ መንግስት ለዚህ ታሪካዊ ተቋም ተገቢውን ክትትል ያለማድረጉ እንዲሁም እንደ ተቋም ከሌሎች ወታደራዊ ተቋማት የተለየ ክብካቤና አማራጭ ፕላኖች አያስፈልጉትም ከሚል ግልፅ እሳቤዎች ይመነጫል።

ሀገራዊ ለውጡና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዳግም ትንሳኤ!

ይህ ለውጥ ይዞ ከመጣው ትሩፋቶች መካከል በዋነኝነት የሀገርቱን የፀጥታና ደህንነት ተቋማትን አቋማቸውን በመፈተሽ ጊዜውንና ዘመኑን በሚመጥን መልኩ እንደ አዲስ ማዋቀር ላይ ትኩረት ማድረጉ ነው።

በመሆኑም ይህንን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመውሰድ ሪፎርሙን ወደተግባር ከለወጡት ወታደራዊና የፀጥታ ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ነው።

ዘጋቢ ፍቅሬ በቀለ አገር መከላከያ

Exit mobile version