Site icon ETHIOREVIEW

ምርመራ ከተደረገባቸው 22 ሺህ የትምህርት ማስረጃዎች አስር በመቶ መስፈርት የማያሟሉ ሆኑ፤ ምርመራው ይቀጥላል

በተያዘው ዓመት ፍተሻ ከተደረገባቸው 22ሺ የትምህርት ማስረጃዎች አስር በመቶ የሚደርሱት ሀሰተኛና መስፈርቱን የማያሟሉ መሆናቸውን የኢፌዴሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ የተቋማት ቁጥጥርና የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቸሩጌታ ገነነ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ በትምህርት ዘርፍ ከሚታዩ ችግሮች አንዱ ነው።ችግሩን ለመቀነስ ባለሥልጣኑ ባደረገው ፍተሻ ከ22ሺ የትምህርት ማስረጃዎች መካከል አስር በመቶ የሚደርሱት ሀሰተኛ አልያም መስፈርቱን የማያሟሉ ናቸው፡፡

ከዚህ በፊት የይረጋገጥልኝ ጥያቄ በስፋት የሚመጣው ከግለሰቦች ነበር ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት በመጣ አቅጣጫ መሠረት የሁሉም ተቋማት ሠራተኞችን የትምህርት ማስረጃ ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመት 40 የሚደርሱ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች የትምህርት ማስረጃዎችን የማረጋገጥ ሥራ መሠራቱን አስታውሰው፤ ምን ውጤት ተገኘ የሚለው በቀጣይነት ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ቸሩጌታ ገለጻ፤ የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛ አይደለም የሚባለው ሀሰተኛ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ተቋማት ፍቃድ ሳይኖራቸው ሲያስተምሩ፣ መስፈርቱን ያላሟላ ተማሪ ተቀብለው ሲያስተምሩና በሌሎችም ሕግን ባላከበረ መልኩ የተገኘ የትምህርት ማስረጃ ጭምር ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ባለሥልጣኑ የማረጋገጥ ሥራ ካከናወነባቸው 22ሺ የሚደርሱ የትምህርት ማስረጃዎች አስር በመቶ የሚሆኑት ትክክለኛ መስፈርቱን ያላሟሉ ሆነው መገኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ተማሪዎች ወደ ትምህርት ተቋማት ከመግባታቸው በፊት የተቋማትን ፍቃድና እነሱም አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ስለመመዝገባቸው ማረጋገጥ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ባለሥልጣኑ የትምህርት ሥርዓቱ የሚመራባቸው መስፈርቶች (ስታንዳርዶች) እና ደንቦች ጊዜውን የሚመጥኑና ለትምህርት ጥራት መጨመር አጋዥ በሚሆን መልኩ የማስተካከልና የማሻሻል ሥራዎች እየሠራ ነው ብለዋል።ውጤት የሚመጣው ግን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሲሠሩ ስለሆነ ማኅበረሰቡና መገናኛ ብዙኃን ከሕግ አግባብ ውጪ ተማሪዎችን ተቀብለው የሚያስተምሩ ተቋማትን በማጋለጥ በኩል የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ሀገር ተረካቢ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነት የተጣለባቸው ተቋማት ሕግን አክብረው በመንቀሳቀስ ሀገራዊ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ተማሪዎች መስፈርቱን ሳያሟሉና ፍቃድ በሌላቸው ተቋማት ሲማሩ መጨረሻ ላይ ለችግር ስለሚዳረጉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኢፌዴሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የከፍተኛ ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ፈቃድ አሰጣጥ፣ የከፍተኛ ትምህርት እውቅና አሰጣጥ፣ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ እና የአቻ ግመታና የተቋማት የክትትልና የቁጥጥር መመሪያዎችን ለማሻሻል እየሠራ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version