Site icon ETHIOREVIEW

ጄነራል አበባው ትክክለኛው ፋኖ በህጋዊ መስመር ተጨማሪ ሃይል እንደሆነ አመልከቱ፤ ያፈነገጠውም መስመር ይዟል አሉ

ፋኖን አስመልክቶ የጦር ሀይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሠ በአብዛኛው ዓላማውን ተረድቶ ወደ ህጋዊ አግባብ መግባቱንና ይህም ሃይል ተጨማሪ ሃይል እንደሆነ ገለጹ። በማይሆን ስብከት አሻፈረኝ ያለውም ሃይል አስፈላጊው ስራ ተሰርቶ መስመር እንዲይዝ መደረጉን አስታወቁ። ቀደም ሲል ትክክለኛው ፋኖ የሚዲያ ጋጋታና አጉል ዝና የማይወድ ዓላማውንና መሰረቱን የሚያውቅ ሲሆን በስሙ ዝርፊያ፣ አፈናና ግድያ የሚፈጽሙትን ሃይሎች ህዝብ አስታግሱልን ማለቱ ይታወሳል።

ጀነራሉ ይህን የተናገሩት በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ በየሦስት ወሩ በሚታተመው መከታ መፅሄት ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ ምልልስ ነው። ይህንኑ ሰፊ ቃለ ምልልስ ቆንጥሮ ለንባብ ያበቃው የሰራዊቱ የማህበራዊ ገጽ ያተመውን ያንብቡ።

በቦርድና በጡረታ የሚሰናበተውም ህጉ በሚፈቅደው መንገድ የሚስተናገዱበት ሁኔታ ተቀምጧል። መንግስትና መከላከያ ለሐገር አስተዋፅኦ ያደረጉና በፀጥታ ማስከበር ስራ ላይ ተሠማርተው የቆዩ አንድም ግለሰብ ቢሆን ከሥራ ውጪ መበተን የለባቸውም የሚል አቅጣጫ ይዘው ነው የሠሩት።

የዕድሜ መግፋት ያለባቸው በሽተኛ የሆኑና በጥይት ከፍ ያለ ጉዳት ደርሶባቸው መሥራት የሚይችሉ ካሉ ህጉ በሚፈቅደው መልኩ አስፈላጊው ነገር እንዲፈፀምላቸው መልሶ መቋቋም የሚያስፈልጋቸውም በተሐድሶ ኮሚሽን ከሚቋቋሙት ጋር እንዲቋቋሙ በሚል እያንዳንዱ በዝርዝር ታይቶ ነው ወደ ሥራ የተገባው።

ይሕንን መሰረት በማድረግ ሁሉም ወደየቦታው እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ይሁንና ሒደቱ እንዲስተጓጎል ፅንፈኛው ሃይል ያካሄደው አፍራሽ ቅስቀሳ ብዙ ነበር። “የሌላው ክልል ትጥቅ ሳይፈታ አንተን ብቻ ነው የሚያስፈቱት” የሚል የፅንፈኛ ፕሮፓጋንዳ በስፋት ነበር። ፅንፈኞችና ስልጣንን ሕገ መንግስቱ ከሚፈቅደው ውጪ መያዝ የሚፈልጉ ወገኖች ይሄንን ሃይል እንደ ሃይል እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። ምክንያቱም በነውጥ ስልጣን መያዝ ስለሚፈልጉና በብሔር ስም የተቋቋሙ የታጠቁ አደረጃጀቶችን በብሔር አጀንዳ እየቀሰቀሱ በነውጥ ስልጣን መያዢያ ሊያደርጓቸው ስለሚያስቡ ነው።

ተጨባጩ ዕውነታ ግን ሁሉም ክልሎች በዚህ ፕሮግራም ውስጥ የታቀፉ መሆናቸውና ያልታቀፈ ክልል አለመኖሩ ነው። ይሄ መሆኑ እየታወቀ ለተወሰነ ክልል ብቻ የመጣ ተደርጎ በየሚዲያው ፕሮፓጋንዳው ቀድሞ ስለተሰራጨናና ብዥታ ስለፈጠረ በአማራ አከባቢ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ችግር ተፈጥሯል። ያንን ሠራዊቱ በለመደው አሰራር ሕዝባዊ ወገኝተኝነቱን መሰረት አድርጎ በውይይት ለማስተካከል ተሞክሮ ስኬታማ ሆኗል አሁን ሁሉም ወደ ተቀመጠላቸው አደረጃጀታቸው እንዲገቡ ተደርገዋል።

በዚህ ላይ ምንም የቀረ ክልል የለም ምንም በልዩ ሃይል የሚታዘዝ አደረጃጀትና የኮማንድ ስርዓት ያለው አሁን የለም። እንደ ሃይል ወይ መከላከያ ሆኗል ወደ መደበኛ ፖሊስ ሆኗል ወይም ደግሞ ፌዴራል ፖሊስ ሆኗል። ይሄ በተሳካ መንገድ ነው የተፈፀመው፡፡

ሶስተኛው ስቴፕ እነዚህ በልዩ ሃይል እና በኢ መደበኛ አደረጃጀትና ቅርፅ ተደራጅተው ሲሠሩ የነበሩት ሐይሎች አሁን ወደ ፌዴራልና ክልል ፖሊስ ወደ መከላከያ ሲመጡ ሀገራዊ ተልዕኮ መቀበል እንዲችሉ ስልጠና መስጠት ነበረብን ፣ ለዚህ የሚያበቃቸውን ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል። እየተደረገም ነው። መከላከያም በመከላከያ ፋላጎት ላይ ተመስርቶ ፌዴራል ፖሊስም ፍላጎቱን መሰረት አድርጎ እንዲሁም ግዳጅና ተልዕኮ ላይ በመመስረት ስልጠናዎች በተለያዩ ዙሮች እንዲሰጡ ሆኗል፡፡

የትግራይ ሐይልን በተመለከተ ከትግራይ ጋር ተያይዞ ያለውም እንደ ማንኛውም ክልል እሱም የሚኖረው መደበኛ ፖሊስ እና ሚሊሻ ብቻ ነው። በተቀመጠለት ስታንዳርድ ብቻ ነው የሚሄደው: ይሄ ትጥቅ የማስረከብ ስርዓቱ የተጀመረ ስለሆነ በቅርቡ ያልቃል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

ፋኖን በተመለከተ በጦርነት የተፈጠረውን የፋኖ ሃይል ወደ ሕገወጥ አሰላለፍ አስገብተው ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ፅንፈኞች ወደ ሕጋዊ አሠራር እንዳይገባ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርገውለት እንደነበር ይታወቃል። መንግስት ግን የፋኖን ሐይልም ለሀገር የሚጠቅም ሃይል ነው በጦርነት ጊዜ የከተት ነው ይሄ ሃይልም ልክ እንደ ልዩ ሃይሉ አማራጭ ይሰጠው ፖሊስ የሚሆን ፖሊስ መከላከያ የሚሆን መከላከያ ይግባ ብለን ክፍት አድርገንለታል።

ይሄንንም እንደ ሃይል እንጠቀም ብለን በወሰነው መሠረት በተሳካ መንገድ ተፈፅሟል፡፡ መንግስት ያስቀመጠውን ወደ ሕጋዊነት የማስገባት ፕሮግራም አልቀበልም ብሎ ወደ የሃይል አማራጭ የተከተለውን ግን በሁለት መንገድ ነው ለመፍታት የሞከርነው፡፡

የመጀመሪያው አማራጭ መንግስት የያዘው ፕሮግራም ምን እንደሆነ ለራሱ ለፋኖው እንዴት እንደሚጠቅመው ለማስረዳትና ለማወያየት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። አስረድተንም አብዛኛው ሊባል የሚችለው ወደ ተፈለገው መስመር ገብቷል። አሻፈረኝ ብሎ የአመፅ መንገድን የመረጠውን ግን ሕጋዊው አሠራር የግድ ተግባራዊ መደረግ ስለነበረበት በመረጠው መንገድ ሔደን መስመር አስይዘነዋል። በድምሩ ሲታይ ግን አቅደን የተነሳነውን አሳክተናል።

ወደ ሕጋዊ አሠራር የመጣው ሐይል እንደ ሃይል በመከላከያም በፌዴራልም በፖሊስም ገብቶ አገራዊ አቅም ጨምሮልናል፡፡ ሠላም እና ፀጥታን በማስከበር ረገድ ገንቢ ሚና ሊጫወት በሚችል መስመር ውስጥ ገብቷል። የተቀመጠው ግብም ተሳክቷል። ይሔ አቅጣጫ በቀጣይም ሀገር የመከላከል አቅማችን እንዲጨምር ያደርጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

የዚሕን ሐገራዊ ወታደራዊ አቅማችንን የማጠናከርና የፀጥታ ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ አደረጃጀቶችን ወደ ሕጋዊነት የማስገባታችንን አሠራር ለማደናቀፍ የሚሠሩ ሐይሎች ከድርጊታቸው ቢታቀቡ መልካም ነው።

በዚሕ ረገድ የተከናወነው ተግባር የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉ ሃይሎች ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ባሉት አማራጮች ብቻ ላይ የሐሳብ ትግል ወደ ማድረግና በውይይት ችግሮችን አንዲፈቱ የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል። በጉልበት የመሄድን ነገር ያስቀራል። የጉልበቱ መንገድ ህጋዊ እንዳልሆነ ህገወጥ እንደሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈቅደው ስልጣንን በህዝቦች ምርጨ ብቻ መያዝ እንዲቻል ያደርጋል።

Exit mobile version