Site icon ETHIOREVIEW

የኢሰመኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ “ምክረ አሳብ” ለፓርላማ አባላት ከውሳኔ በፊት ታደላቸው

ከእንግሊዝ ተመልሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ዶክተር ዳንኤል በቀለ በአማራ ክልልና ሳይገደብ እንደ አስፈላጊነቱ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተፈጻሚ እንዲሆን የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ” ምክረ አሳብ” በሚል የተዘጋጀ ባለ 26 ገጽ ሰነድ ፓርላማው ለውሳኔ ከመቅመጡ በፊት ለአባላቱ እንዲደርስ አድርገዋል። በሰነዱ የአምራ ክልልን ለከፋ ቀውስ፣ ዝርፊያ፣ ግድያና ንብረት ማውደም እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መስተጓጎል በአስቸኳይ እንዲቆም “ድርድር” ከሚል ውጪ ሌላ ዝርዝር መፍትሄ አልተካተተም።

ከሰው ልጆች መብት አንጻር አዋጁን ቃል በቃል በመተቸት ምክረ አሳብ ያቀረበው ኢሰማኮ፣ የአስቸኳይ አዋጁ ተነስቶ ክልሉ ዳግም ወደ ነበረበት ቀውስ ሊገባ ቢችል ማን ሃላፊነት እንደሚወስድ አላመላከተም። በንጽሃን ላይ የደረሰው ግድያና እጅግ እንዳሳሰበው፣ በጅምላ የሚደረግ እስርና ማንነት ላይ ያተኮረ እርምጃ ሊቆም እንደሚገባ ጠቅሶ ተደጋጋሚ መግለጫ የበተነው ኢሰማኮ ምክረ አሳቡን በማጤን የፓርላማ አባላቱ ውሳኔያቸውን እንዲያስተካክሉ በይፋ ጠይቋል።

ሳምሪ በሚባሉ የትህነግ ሰልጣኞች የተገደሉ የአማራ ክልል የወልቃይት ነዋሪዎችን አስመልክቶ የተንሸዋረረ አቋም ሲያራምድ የነበረው ኢሰመኮ፣ በተለይም ዋና ኮሚሽነሩ በትግራይ ወረራ ወቅት ያሳዩት የነበረው ፍጹም ገለልተኛ ያልሆነ አካሄድ በአንብዛኛው ተቃውሞ ሲያስነሳባቸው እንደነበር የማይካድራን ጭፍጨፋ አስመልክተው ያቀረቡትን ሪፖርትና ቃለ ምልልስ በመጥቀስ በማስታወስ ብዙዎች ይጠራጠሯቸዋል።

“መከላከያ ከአማራ ክልል ይውጣ” ከሚለው አሳብ ባልተለየ መልኩ ዶክተር ዳንኤል አስቸኳይ አዋጁ ከታወጀ ጀምሮ ያሳዩት ተከታታይ ተቃውሞ የተገናኘባቸው አካላትም አሉ።

በርካታ ንጹሃን መገደላቸውና መታሰራቸው በበቂ ማስረጃ ማረጋገጡን የሚያመለክተው የኢትዮጵያ ሰብአዊ ኮሚሽ መንገድ ሲዘጉ የነበሩ ክፍሎች ሳይቀር መሞታቸውን አመልክቷል። ኮሚሽኑ በቀጣይ ሙሉ ሪፖርቱን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። ከስር በገጹ ላይ ያስቀመጠው ዜናው ነው። ባለ ሃያ ስድስት ገጽ ሪፖርቱን እዚህ ላይ ተጭነው ያንብቡ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 ላይ ያዘጋጀውን ባለ 26 ገጽ የሰብአዊ መብቶች ትንታኔ እና ዝርዝር ምክረ ሐሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን አስታወቀ፡፡ በመጪው ሰኞ ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዋጁ ላይ ለመምከርና ለመወሰን አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሚሽኑን ምክረ ሐሳቦች በጥንቃቄ አጢኖ ተግባራዊ እንዲያደርጋቸው ኮሚሽኑ ጠይቋል፡፡

ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ በላከው የትንታኔ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ በተለይም በአዋጁ የተመለከቱ ክልከላዎችና ግዴታዎች፣ ለመንግሥት የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን፣ የአዋጁ ከባቢያዊና የጊዜ ተፈጻሚነት ወሰን፣ የሕዝብ ተወካዮች እና ዳኞችን ያለምክር ቤቱ ውሳኔ አለመያዝና መከሰስ ልዩ መብት (Immunity) ጨምሮ ሌሎችም ሊገደቡ ስለማይችሉ መብቶች ጥበቃ፤ በአጠቃላይ የአዋጁ እያንዳንዱ አንቀጾች ከጥብቅ አስፈላጊነት (necessity)፣ ተመጣጣኝነት (proportionality) እና ሕጋዊነት (legality) አንጻር አንዲመረመሩ ይጠይቃል፡፡

በተጨማሪም አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በነበሩት ተከታታይ ቀኖች በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ተከስቶ የነበረው የሰላምና ደህንነት ልዩ አደጋ በአሁኑ ወቅት ተወግዶና መደበኛ እንቅስቃሴዎች ወደ ነበሩበት ሁኔታ መመለስ መጀመራቸው በመንግሥት በይፋ የተገለጸ በመሆኑ፤ ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን አስፈላጊነት፣ ከባቢያዊና የጊዜ ተፈጻሚነት ወሰንን በተለይ በጥንቃቄ በማጤን ምክር ቤቱ አዋጁን የሚያጸድቀው ቢሆን የጊዜ ተፈጻሚነቱ ከአንድ ወር ወይም የተወሰኑ ሳምንታት የበለጠ እንዳይሆንና ከባቢያዊ ተፈጻሚነቱም ልዩ አደጋው ተከስቷል በተባለበት ቦታ ብቻ የተገደበ እንጂ በጠቅላላ ሀገሪቱ እንዳይደረግ ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁን አስመልክቶ አዋጁ በተነገረበት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም፣ ባወጣው መግለጫ፣ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ሰብአዊ መብቶች ሊከበሩ እንደሚገባ አሳስቦ፤ በተለይም ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. በአማራ ክልል እየተባባሰ ለመጣው የትጥቅ ግጭት እና የጸጥታ ችግር ዘላቂ እና ሰላማዊ መፍትሔ የማፈላለግ ጥረት እንዲቀድም ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው። ኮሚሽኑ ከሚያደርገው መደበኛ የሰብአዊ መብቶች ክትትል በተጨማሪም በተለይ በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን ክትትል እንዲያደርግ በማቋቋሚያ አዋጁ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጠው በመሆኑ የአዋጁን አፈጻጸም በሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በተለይም የጥብቅ አስፈላጊነት፣ በማናቸውም ሁኔታ የማይገደቡ መብቶችን የመጠበቅ፣ የተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነጻ መሆን መርሖችን ባከበረ መልኩ መተግበራቸውን በመከታተል ላይ ነው።

ኢሰመኮ በተለያዩ ወቅቶች በሀገሪቱ በከፊልም ሆነ በሀገር አቀፍ የተጣሉ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች ክትትል እና ምርመራ አድርጎ፣ ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው። በአዋጅ ቁጥር 6/2015 ላይ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችም በዋነኝነት በእነዚህ የክትትል እና የምርመራ ግኝቶቹ ላይ የተመሠረቱ ሲሆን፣ በተለይም ከእዚህ ቀደም በነበሩ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች ወቅት የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መድረሳቸውንና ከእነዚህም ውስጥ አሳሳቢ ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ ኢሰብአዊ አያያዞች፣ በተለይም በጥቆማ ላይ የተመሠረቱ እስሮችን በተመለከተ የጥቆማዎቹ መነሻ የሰዎቹ የብሔር ማንነት አለመሆኑን ለማረጋገጥ እና ምክንያታዊ ጥርጣሬ ስለመኖሩ ለማጣራት በቂ ጥረት ያልተደረገባቸው በርካታ እስሮች እንደነበሩ፣ ሴቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች እና በመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ላይ የደረሱ ጥሰቶችን እንደሚጨምር አመላክቷል።

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችና የሰብአዊ መብቶች መርሖች ላይ በመመሥረት ባቀረበው ትንታኔ ላይ ምክር ቤቱ አዋጁን የሚያጸድቀው ቢሆን ለትርጉም አሻሚ የሆኑና ተለጥጠው በመተግበር ተገቢ ላልሆነ አፈጻጸምና የሰብአዊ መብቶች አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ ድንጋጌዎች ላይ ሊደረጉ የሚገባቸውን ማሻሻያዎች በዝርዝር በማቅረብ ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አወጁ ጋር የሚቃረኑ የፍሬ ነገር እና የሥነ ሥርዓት ሕጎች በጅምላ መታገዳቸው እና የዲፕሎማቲክ ልዩ መብቶችን ብቻ ሲቀር ሌሎች ከልዩ ሥራና ኃላፊነት ነጻነትን ከመጠበቅ አስፈላጊነት የሚመነጩ ልዩ መብቶቸንና ጥበቃዎችን (Functional Immunity) ሊታገዱ መቻላቸው ከሚያስከትላቸው ውጤቶች መካከል አንዱ ለምሳሌ የፓርላማ አባላትና የዳኞችን ያለ ምክር ቤቱ ውሳኔ ያለመያዝና ያለመከሰስ መብቶችን ጭምር አላግባብ ለማገድ በር የሚከፍት በመሆኑ ይህም በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን

ሊታገድ የማይችለውን የዳኝነት ዋስትና እና በነጻነት ላይ የተመሠረተ የፍትሕ አስተዳደርን የሚያግድ፣ እንዲሁም በተለይም በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ሊደረግ የሚገባውን የፓርላማ ክትትል (Parliamentary Oversight) መርሕ ተፈጻሚነት ሊያደናቅፍ የሚችል ነው፡፡ በማናቸውም ጊዜ ብቁ ነጻ እና ገለልተኛ የዳኝነት አካላት እና የፍትሕ ሥርዓት መኖር ለሕጋዊነት እና ለሕግ የበላይነት መርሖች መተግበር የግድ የሚል ነው፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታም የዳኝነት ተቋሙ ተግባርና ኃላፊነት በሙሉ ነጻነት ሊቀጥል የሚገባው ሲሆን በተለይም የመንግሥት ኃላፊዎች እና የሕግ አስፈጻሚ አካላት የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን አጠቃቀም ከአስቸኳይ ጊዜ ሕጉ ጋር የሚስማማ መሆኑንና አለመሆኑን፤ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን አተገባበር አላስፈላጊና ተመጣጣኝ ባልሆነ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት የተረጋገጡ መብቶችን የሚጥሱ መሆናቸውን ወይም አለመሆናቸውን በነጻነት መወሰን መቻል ስላለበት፣ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ ወቅት ክትትል (Parliamentary Oversight) እና የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትል በነጻነት መቀጠል ስላለበት፤ የዳኞችና የምክር ቤት አባሎችን ልዩ መብት ጥበቃ ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አሳስበዋል፡፡


Exit mobile version