ETHIOREVIEW

የኢትዮጵያ መከላከያ የላቀ ደረጃ መድረሱን ያሳየ ግዙፍ ሰራዊት ተመረቀ ” ተወደደም ተጠላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገር ናት”

“እንባዬ ፈሰሰ” ይላሉ የስቶኮልም ነዋሪው የቀድሞ ሰራዊት አባል። ፓራኮማንዶ ሆነው ምስራቅ የዘመቱት አዛውንት ” የባህር ህይላችንን ነጩን ልብስ ስመለከተ በደስታ ሰክሬ ነበር፣ ዛሬ ቀይ ለባሾቹን ስመለከት እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ” ሲሉ ደስታቸውን አጋሩ። ይህ የሆነው “ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያውን ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል አስመረቀች” የሚለውን ዜና በተመለከቱበት ቅጽበት ለወዳጃቸው ነው። “ይህ ሃይል ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት ያደርጋል” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ያደመጡ አስታውቀዋል።

የኮማንዶ እና አየር ወለድ ዕዝ ማሠልጠኛ ማዕከል  ያሠለጠናቸውን የመሠረታዊ ኮማንዶ አባላት የምርቃት መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ፣ ሰራዊቱን “ቀይ መለዮ ማለት ጠላቱን የሚያርበደብድ ወገኑን የሚያኮራ ነው” ሲሉ ገልጸውታል። ኢትዮጵያ አሁን ላይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንደምትዋጋ አስታውቀው ይህ ሃይል ውጊያ ጨረሽ እንደሆነም አመክተዋል። የሰላም ሃይል መሆኑንንም ገልጸዋል።

አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በሁዋላ በሻእቢያና ወያኔ ትብብር የፈረሱትን የኢትዮጵያ አየር ሃይል፣ ባህር ሃይል፣ ካዴት ማሰልጠኛ ተቋም፣ የፓራ ኮማንዶና የልዩ ኢንተለጀንስ ማስለልጠኛ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ኢትዮጵያ አይታው የማታውቀውን የመከላከያ ሃይል እንዲገነባ አድርገዋል። እጅግ ዘመናዊ በተባለ ደረጃ እየተዋቀረ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ አዳዲስ ምሁር መኮንኖችን እያፈራ ሲሆን፣ በውጭ አገርና በአገር ውስጥ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ትምህርት የቀሰሙ ተተኪ ጀነራሎችንም እያዘጋጀች መሆኑ እየተገለጸ ነው። እነዚህ ከብሄርና ከዘር እሳቤ ርቀው እየተዘጋጁ ያሉ ምሁር የጦር መኮንኖች ከነባሮቹ ልምድ በመቅሰም ላይ እንደሆኑም ታውቋል።

ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው ሰራዊት ስፋትና ዘመናዊ መሆን ቀደም ሲል የኢትዮጵያን መከላከያ “የደርግ ” ብለው ፈርጀው ላፈረሱ ሴረኞች ስጋት እየሆነባቸውና በውስጥ ጉዳይ ገብተው እየፈተፈቱ ባለበት ወቅት ይህ ግዙፍ ሃይል መመረቁ ሌላ ስጋት እንደሚሆንባቸው ተገልጿል። አብይ አህመድ ለነዚህ ወገኖችም ሆነ ለሌሎች ” ቁርጣችሁን እወቁ” ዓይነት መልዕክት አስተላልፈዋል። ኢትዮጵያ ታላቅ አገር በመሆኗ በሚመጥናት ደረጃ መከላከያዋን እየገነባች እንደሆነ አመልክተዋል። ” አገራችን ተወደደም ተጠላም በአፍሪካ ተጽእኖ ፈጣሪ፣ ታላቅ አገር ናት” በማለት ይህን ደረጃዋን አምነው መቀበልና በደረጃቸው ማሰብ ለሚገባቸው ምክር ቢጤ ሰጥተዋል። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዜናውን በአድናቆት እንዳዩትም ለመረዳት ተችሏል።

ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ሃይል ለሰላም አለኝታ እንደሆነ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ በየብስ፣ በባህር፣ በአየርና በሳይበር ለሚሰነዘር ማናቸውም ጥቃት አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት የሚችል ሁሉ አቀፍ ሰራዊት መግንባቱን፣ ወደፊትም የማዘመኑ ስራ በዚሁ እንደሚቀጥል አመልክተዋ። ይህን የሰሙ ምሁራን ” ኢትዮጵያ በዚህ አቅሟ የወደብ ባለቤት የምትሆንበት ቀን ለሌሎች ስጋት ቢሆንም ሩቅ አይደለም” ሲሉ ምልክት ማየታቸውን አስታውቀዋል። አብይ አሕመድ ” እኛ የምናደርገው የሚገባቸው ጠላቶቻችን ናችው” ሲሉ የገለጹትን በማስታወስ ኢትዮጵያ እንዳትረጋ የሚደረግበትና በብሄር ተቧድና እንድትጫረስ የሚረጨው ቅስቀሳ የዚሁ አካል እንደሆነም አመክተዋል።

“እኛ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች እየሠራን ያለነው ሥራ ፕሮፌሽናል ሠራዊት መገንባት ነወ፤ አሁን ላይ ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተወጣጣ ህብረ ብሄራዊ ሠራዊት እየገነባን ነው፤ ብቃት ያለው ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችል ሠራዊት እያበቃን እንገኛለን፤ የዛሬ ተመራቂ ኮማንዶዎች እና አየር ወለዶች የዘመናዊነታችን ማሣያዎች ናቸው፤    ኮማንዶዎች እና አየር ወለዶች የምድር ድሮዎኖች ብቻ ሳይሆኑ በእሳት ተፈትነው ያለፉ የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው፤ ቀይ መለዮ ማለት ጠላቱን የሚያርበደብድ ወገኑን የሚያኮራ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አመልክተዋል።

“ከፊት ለፊታችን የኢትዮጵያችን ሰንደቅ-ዓላማ፣ ከኃላችን መላው ሀገር ወዳድ ዜጋ” የሚል መርህ ያለው የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሰራዊት በራሱ ወገኖች፣ ፈርሶ በየጎዳናው እንዲለምን ተደርጓል። በክህደት በተኛበት ታርዷል። በዚህ ሁሉ ውስጥ አልፎ ራሱን ያጸናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ባንድራ ላብሶ ቃል ኪዳኑንን እንደማይበላ ምሎ ምረቃውን አተናቋል።

እኛ ተራ ጀብደኞች አይደለንም።ስሜት በድንገቴ ዛቻ አቅል አሳጥቶ የሚነዳን ልጓም አልባነት ፈጽሞ አይዳዳንም። እኛ በሸንጋይ ሙገሳና ውዳሴ ስለተንቆለጳጰስን ደማችን የሚሞቅ፣በነገር ሽንቆጣ ስንብጠለጠል የምንቀዘቅዝ ደመ-ነፍሳዊነትም አይነካካንም። ምክንያቱም እኛዊ ማንነታችን ነፋስ በበረታ ቁጥር የሚወዛወዝ መርገጫ አልባ ሳይሆን መርህን ተመርኩዞ፣በነጠረ ግብ የቆነጀ፣የመዳረሻን ፍኖት ጠንቅቆ በተረዳ አስተዋይነት የተዋበ ስለሆነ። እኛነታችን ሲገለጥ በሞያዊ ዕውቀት የቀለመ፣ በታላቅ የሃላፊነት መንፈስ ያማረ፣በኢትዮጵያዊ ሞራልና ስነ-ምግባር ያጌጠ ማራኪ ህብረ ቀለም ጎልቶ ያንጸባርቃል” ሲሉ ከምረቃው በሁዋላ የሰራዊቱ አባላት ተቀኝተውለታል።

በምረቃው ወቅት አባትና ልጅ በብላቴ መገኘታቸውን “ግጥምጥም” ሲል ኢፒድ የሚከተለውን ዘግቧል።

ሻለቃ ካሳ አበራ ይባላሉ። በደቡብ ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባል ሆነው አገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በ1990 ዓ.ም የሀገር መከላከያን የተቀላቀሉት ሻለቃ ካሳ፤ በሰራዊቱ ውስጥ ሆነው አገራቸውን ለ26 ዓመታት አገልግለዋል።

የኢፕድ ዘጋቢዎች ትናንት ያገኟቸው የኮማንዶና የአየር ወለድ ዕዝ በብላቴ ኮማንዶና አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል ያሰለጠናቸውን 41ኛ ዙር ዞብል ኮርስ  መሰረታዊ  ኮማንዶዎችን፥ አየር ወለድና ልዩ ሀይል ፀረ ሽብር አባላት ምረቃ ላይ የልጃቸውን ምረቃ ሲታደሙ ነበር።

“ከአመታት በፊት የሁለት ዓመት ህጻን ልጅ ነበረኝ። ከልጄ ጋር እየኖርን ሳለን ለግዳጅ ተነስ ተባልኩ። ልጄ ከአገሬ አልበለጠብኝምና እናቴን እንድታሳድግልኝ ሰጥቼያት ለግዳጅ ወጣሁ”  የሚሉት ሻለቃ ካሳ፥ ልጃቸው የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆኑን የሰሙትም ለግዳጅ ሶማሊያ በደለዊ እያሉ መሆኑን ይናገራሉ።

“ልጄ የእኔን የአባቱን አርአያ ተከትሎ ወታደር መሆኑ አስደስቶኛል” ሲሉም ነው ትናንት በብላቴ ለተገኙት የኢፕድ ዘጋቢዎች የተናገሩት።

ሁሌም እናቴ ለልጄ የምትመክረው  ምክር ነበራት። እሱም ምን አልባት  ጓደኞችህ በየቦታው ደክመው የሚቀሩ ከሆነ  ጽናትን፥ ጥንካሬንና አገር ወዳድነትህን ከአባትህ ውረስ የሚለው ነው። ይህ ምክር ብርታት ሆኖት ዛሬ ልጄ ወታደር ሆኗል” ይላሉ ሻለቃ ካሳ።

“አሁን ደግሞ የምድር ድሮኖች በሚል የሚታወቀው የኮማንዶ አባል ሆኖ ብዙ ፈተናዎች አልፎ በመመረቁ የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም” ብለውናል።

ልጅ የአባቱን ሙያ ሲወርስ ደስ ይላል የሚሉት ሻለቃ ካሳ፤ “ውትድርና የቤተሰባችን ውርስ ሆኗል ።ታላቅ ወንድሜ የቀድሞ ሠራዊት አባል ነበር። እኔም ወታደር ነኝ፣ ልጄም ወታደር ሆኗል።ይህ ውርስ የመጣውም ለአገራችን ባለን ፍቅር የሚመነጭ ነው” ሲሉም ስሜታቸውን ገልጸውልናል።

ውትድርና አድካሚ ነው፤ ለአገር መስዋዕትነት ያስከፍላል።እሱና ጓዶቹ  ይህን ተገንዘበው ለአገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፤ ሻለቃ ካሳ።

“የአባቴንና የአጎቴን የወታደርነት ሙያ በመቀላቀሌ ደስተኛ ነኝ” የሚለው መሰረታዊ ወታደር እዮብ ካሳ ነው።

ውትድርና ትልቅ ሙያ ነው። አገር መጠበቂያ፣ የህዝብ ሰላምና ደህንነት መጠበቂያም መተዳደሪያም የሆነ ታላቅ ሙያ ነው ሲልም ነው ሃሰቡን ያጋራን።

“የኮማንዶን ውስብስብ ስልጠና አልፌና ወጣ ውረዱን ተሻግሬ ቀይ መለዮ በወታደሩ አባቴ ፌት በመልበሴ እጅግ ደስ ብሎኛል” የሚለው መሰረታዊ ወታደር እዮብ፣ አገሬና ህዝቤ የሚሰጡኝን ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብሏል።


  

Exit mobile version