ETHIOREVIEW

አረንጓዴው ጎርፍ ሲታወስ፤ “የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስደሰት እስከመጨረሻው ተስፋ አልቆረጥኩም” ጉዳፍ ፀጋይ

“ከጎኔ ሆኖ የሚደግፈኝን የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስደሰት እስከመጨረሻው ተስፋ አልቆረጥኩም” – አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ

በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ በሴቶች 10ሺ ሜትር የፍፃሜ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ የአረንጓዴውን ጎርፍ ታሪክ ደግመዋል። በዚህ ርቀት በሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተመሳሳይ ታሪክ ሲሰሩ የዛሬው ሶስተኛ ነው።

ከዚህ ቀደም እኤአ 2001 ኤድመንተን ቻምፒዮና ላይ ደራርቱ ቱሉ፣ ብርሃኔ አደሬና ጌጤ ዋሚ ከአንድ እስከ ሶስት ያጠናቀቁ አትሌቶች ሲሆኑ 2005 ላይ በሄልሲንኪ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ብርሃኔ አደሬና እጅጋየሁ ዲባባ ይሄንኑ ታሪክ ሰርተዋል።

ባለፈው ቻምፒዮና በ10ሺ ሜትር ለተሰንበት ያገኘችው የወርቅ ሜዳልያ በቻምፒዮናው ታሪክ ለኢትዮጵያ ስምንተኛው የወርቅ ሜዳልያ ነበር። ዛሬ ይሄው ክብረወሰን በጉዳፍ ፀጋይ ቀጥሏል። የወርቅ ሜዳሊያውን ከትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን ለማስጣል እልህ አስጨራሽ የአጨራረስ ትግል ያደረገችው ጉዳፍ በ31:27.18 ቀዳሚ ሆናለች። ያለፈው ቻምፒዮና አሸናፊዋ ለተሰንበት ግደይ በ31:28.16 ሁለተኛ፣ በ31:28.31 ሰዓት እጅጋየሁ ታዬ ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል። ይህም በቡዳፔስቱ ቻምፒዮና የመጀመሪያ ቀን ኢትዮጵያ በአንድ ርቀት ብቻ ሶስት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በማእከላዊቷ አውሮፓ ደምቃ እንድትታይ አድርጓታል።

በዚህ ርቀት ጌጤ ዋሚ በ1999፤ ደራርቱ ቱሉ በ2001፤ ብርሃኔ አደሬ በ2003፤ ጥሩነሽ ዲባባ በ2005 በ2007 እና በ2013 እንዲሁም አልማዝ አያና በ2017 እኤአ ላይ 7ቱን የወርቅ ሜዳልያዎች አግኝተዋል። 7 የብር ሜዳልያዎች ብርሃኔ አደሬ በ2001ና በ2005 ፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ በ2003፤ መሰለች መልካሙ በ2009፤ ገለቴ ቡርቃ በ2015፤ ጥሩነሽ ዲባባ በ2017 እንዲሁም ለተሰንበት ግደይ በ2019 እኤአ ላይ አግኝተዋል። 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን ደግሞ ጌጤ ዋሚ በ2001፤ እጅጋየሁ ዲባባ በ2005፤ ውዴ አያሌው በ2009 እና በላይነሽ ኦልጅራ በ2013 እኤአ ላይ ተጎናፅፈዋል።

አትሌቲክስ ሲዋዥቅ የነበረው ውጤቱ አሁን ላይ ወደ ማይዋዥቅ ጎዳና እያመራ መሆኑ ማሳያ የሆነው የዛሬው ውጤት እነ ሻምበል ምሩጽ፣ መሀመድ ከድርና ዮሃንስ መሃመድ ዘመን ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ጎርፍ የተመሰለችበት ዘመን ያስታወሰ መሆኑ ለኢትዮጵያዊያን ደስታ፣ ለሌላው ዓለም ግራሞት ፈጥሯል።

ቦጋለ አበበ አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 ቀን 2015 ዓ.ም

“ከጎኔ ሆኖ የሚደግፈኝን የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስደሰት እስከመጨረሻው ተስፋ አልቆረጥኩም” – አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ

ኢትዮጵያ በ19ኛው የሴቶች 10 ሺህ የፍጻሜ ውድድር የአለም አትሌትክስ ሻምፒዮና ከ1 እስከ 3ኛ ደረጃን በመያዝ አንፀባራቂ ድል አስመዝግባለች፡፡

በውድድሩ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ወርቅ ያስገኘችው አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድሩ በኋላ ከኢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ ስለነበረው የቡድን ስራ እንዲሁም በተገኘው ድል ስለተሰማት ስሜት ሃሳቧን አጋርታለች።

አትሌት ጉዳፍ በሰጠችው አስተያየት፤ ወርቁ ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ከፍተኛ ጥረት አድርገናል በፈጣሪ እርዳታም ማሰካት ችለናል ብላለች፡፡

በውድድሩ እስከመጨረሻው ድረስ በጭራሽ እጅ አልሰጥም ብዬ ነው የገባሁት ያለችው አትሌቷ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ወርቅ ማምጣት ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ ከዚህ በፊት አይቻለሁ፤ ይህም ድጋፍ ሆኖኛል ስትል ገልፃለች፡፡

አትሌት ጉዳፍ ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቀችው እግሯ እየደማ ሲሆን ይህ አስመልክቶ በሰጠችው አስተያየት” ሩጫ ላይ እንዲህ ያለው ነገር ያጋጥማል። በሩጫው መሃል ላይ ተነክቼ ነው እንደዛ የሆነው። 17 ወይም 18ኛው ዙር ላይ ላልፍ አካባቢ ነው እግሬ የደማው” ብላለች።

“ድሉን ለማሳከት ተነጋግረን ነበር፤ እግዚአብሔርም ሲጨመርበት ነውና ውጤት የሚያምረው የህዝባችን ፀሎት ሰምሯል” ስትልም ደስታዋን አጋርታለች።


Exit mobile version