Site icon ETHIOREVIEW

ቻይናዊው የፀሃይ ሪል ስቴት ዋና ስራ አስኪያጅ ከ9 ግብረ አበሮቻቸው ጋር የውጭ አገር ብሮች በማተምና በጥቁር ገበያ ወንጀል ታስረው ፍ/ቤት ቀረቡ

በርካታ መጠን ያላቸው የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን በማተምና ጥቁር ገበያን በማስፋፋት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ። ተጠርጣሪዎቹ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

የፀሃይ ሪል ስቴት ዋና ስራ አስኪያጅ ኪያ ዦንግን ጨምሮ ዘጠኝ የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ሶስት ኢትዮጵውያን ተጠርጣሪዎች ናቸው ፍርድ ቤት የቀረቡት።

መርማሪ ፖሊስ ግለሰቦቹ በርካታ መጠን ያላቸው የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን በማተምና ጥቁር ገበያን በማስፋፋት ወንጀል መጠርጠራቸውን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች የሚታተሙባቸው ማተሚያ ማሽኖችና ለግብዓት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች እንዲሁም በርካታ ዩሮ፣ የአሜሪካ ዶላርና የሌሎች ሀገራት ገንዘቦች መያዙን ፖሊስ ጠቅሷል።

ተጠርጣሪዎቹ ላይ የተጀመሩ ሰፊ የምርመራ ስራዎችን አከናውኖ እና የተናጠል ተሳትፏቸውን ለይቶ ለመቅረብም የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል። ከአራተኛ ተጠርጣሪ ውጪ ያሉ ግለሰቦች ከወንጀል ድርጊቱ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የግለሰቦቹ የወንጀል ተሳትፎ ባልተገለጸበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

የፀሃይ ሪል ስቴት ዋና ስራ አስኪያጅ ኪያ ዦንግን የተባሉት ግለሰብ በበኩላቸው÷ የተገኘው የውጭ ሀገራት ገንዘብ ማተሚያ በእርሳቸው ቤትና ቢሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወንጀል ድርጊቱ የሚገናኘው ከእርሳቸው ጋር ብቻ መሆኑን ገልጸው÷ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ለችሎቹ አብራርተዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ÷ ተሳትፏቸው አልተገለጸም ተብሎ የተነሳውን መከራከሪያ በሚመለከት በቀጣይ ተሳትፏቸውን ለይቶ በስፋት ምርመራውን አከናውኖ እንደሚቀርብ ገልጾ መልስ ሰጥቷል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የማጣሪያ ምርመራ መደረግ እንዳለበት በማመን የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው ውድቅ አድርጎታል።

ፖሊስ በቀጣይ ቀጠሮ የተጠርጣሪዎችን የወንጀል ተሳትፎ ለይቶ እንዲያቀርብ ከነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የሚታሰብ የ12 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰብ ጋር እንዲገናኙ እና ሕክምና ማግኘት የሚፈልጉም ሕክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ FBC


Exit mobile version