Site icon ETHIOREVIEW

“ሀገር ወዳድነት፣ ማንበብ፣ ማሰብና ማንሰላሰል እንዲሁም ምክንያታዊነት የዚያ ዘመን በጎ ጎኖች ነበሩ”

ጳግሜን 5 የትውልድ ቀን ” ኢትዮጵያ የትውልዶች ድምር” በሚል መሪ ሃሳብ በፌዴራል ደረጃ እየተከበረ ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ፍትሕ ሚኒስቴር በጋራ ባዘጋጁት የትውልድ ቀን በዓል ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ አርበኞች፣ አረጋዊያን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ለበዓሉ ታዳሚዎች መልእክት ያስተላለፉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የአሁኑ ትውልድ ካለፈው የሚማር እና ለሚመጣው የሚያስተምር መደላድል ነው ብለዋል፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ቆመን ያለፈውን እና የሚመጣውን ስናስብ ለነገ ተስፋ የምናይበት ነው ብለዋል፡፡

ሽግግሩ የአንድ ዓመት ብቻ ሳይኾን በርካታ ዘመናትን አስታውሰን፤ እልፍ ዘመናትን የምንቀበልበት ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ የእርሳቸው ትውልድ በርካታ ጥሩ ነገሮች እንዳሉት አንስተው አሁናዊው ትውልድ ሊማርበት የሚገባ በርካታ ጉድለቶች ነበሩበት ብለዋል፡፡ ሀገር ወዳድነት፣ ማንበብ፣ ማሰብና ማንሰላሰል እንዲሁም ምክንያታዊነት የዚያ ዘመን በጎ ጎኖች ነበሩ ብለዋል፡፡

“የእኛ ትውልድ የትግሉ ማዕከል ሀገሩ ነበረች” ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ነገር ግን ዓለምን የምንመለከትበት መነጽር ጠባብ በመኾኑ በርካታ ዋጋ ከፍለናል ብለዋል፡፡ አንድ ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም እንደ መታገያ መስመር መውሰድ እና እርሱን ብቻ መፍትሔ አድርጎ መመልከት ድክመት ነበር፤ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ አለማስገባትም ዋጋ አስከፍሏል ብለዋል፡፡

ትናንት ከሀገር ፍቅር እና ደመ ሞቃትነት የተነሳ አንድ ትውልድ በሚባል መልኩ ዋጋ ከፍሏል ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከዚያ መማር የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ነው ብለዋል፡፡ ሀገርን መጠበቅ፣ ሥልጣኔን ማስቀጠል እና ውስብስብ የኾነውን ዓለም ተረድተው መውጫ ብልሃት የሚያመነጩ ልጆችን ኢትዮጵያ ትፈልጋለች ነው ያሉት፡፡

ሚኒስትሩ በንግግራቸው ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ትውልዱ የተወዛገበ የሞራል መሰረት ላይ መቆሙን ጠቁመው፤ “እኛ ከእኛ የተሻለ ትውልድ መፍጠር ካልቻልን ሀገር እየገደልን ነው” ብለዋል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ እየፈጸማቸው ያሉ የሥርዓተ-ትምህርት ማሻሻያ እና የትምህርት ፍኖተ ካርታ ትግበራ ዓላማው ተማሪዎችን መጣል ሳይኾን ራሱን ችሎ የሚቆም ትውልድ ማፍራት እንደኾነ አንስተዋል፡፡

በጎ፣ ግብረ-ገብ፣ አንሰላሳይ፣ አሳቢ፣ ምክንያታዊ እና ትጉህ ተማሪ ለማፍራት ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንዲቆሙም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው አሚኮ


Exit mobile version