Site icon ETHIOREVIEW

ከሕግ ውጭ ፓስፖርት በመስጠት የሌብነት ወንጀል የተጠረጠሩ 28 ግለሰቦች ፍ/ቤት ቀረቡ

ጉቦ በመቀበል ከሕግ ውጪ ለውጭ ሀገር ዜጎች ፓስፖርት በመስጠት ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ 28 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል÷ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምሩ ገምበታ እና ምክትል ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ቦጋለን ጨምሮ በአገልግሎቱ በተለያዩ ዘርፎች ሲሠሩ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ይገኙበታል።

ከ28 ተጠርጣሪዎች መካከል አራቱ ሴቶች ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹን በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ መደበኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ያቀረባቸው የፌደራል ፖሊስ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዘርፍ መርማሪ ፖሊስ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ ከግለሰብና ከደላላ ጋር በጥቅም በመመሳጠር ከ10 ሺህ እስከ 300 ሺህ ብር የሚደርስ ጉቦ በመቀበል ሕግ አሠራር ውጪ÷ ለውጭ ሀገር ዜጎች ያልተገባ ፓስፖርት በመስጠት የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል፡፡

እንዲሁም በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ብርበራ ከተቋሙ ውጪ ሊገኝ የማይገባ ሠነድ መገኘቱን ለችሎቱ ጠቅሶ የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሠነድ ማስረጃ አደራጅቶ ለመቅረብ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው÷ በደንበኞቻቸው ላይ ፖሊስ ያቀረበው የጥርጣሬ መነሻ ላይ ማን ከማን ጋር ገንዘብ ተቀበለ?፣ ለማንስ ፓስፖርት ሰጠ? የሚል የተናጠል የወንጀል ተሳትፎ ተለይቶ ባልቀረበበት ሁኔታ በጅምላ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቁ አግባብ አደለም የሚሉ መከራከሪያ ነጥቦችን አንስተዋል።

የፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያው ግልጽነት የሚጓድለው ነው ሲሉም ተቃውመው ተከራክረዋል።

በደንበኞቻቸው መኖሪያ ቤት ብርበራ ሲደረግ የፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ ሳይቀረብ ብርበራ መደረጉን ጠቅሰው ከሕግ ውጪ ብርበራ ሊከናወን አይገባም የሚሉ መከራከሪያዎችንም አንስተዋል፡፡

በመኖሪያ ቤት በብርበራ ከተቋም ውጪ ተገኘ ተብሎ በመርማሪ የተገለጸውን ሠነድ በሚመለከትም ሠነድ ያልተገኘባቸው ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ጠበቆቹ ተከራክረዋል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የረጅም ጊዜ ክትትል ተደርጎ በደኅንነት ተቋም ተይዘዋል ተብሎ በፖሊስ መገለጹ በራሱ ቀድሞ የምርመራ ሥራ መሠራቱን የሚጠቁም በመሆኑ ተጠርጣሪዎቹ ተጨማሪ በእስር ሊቆዩ የሚችሉበት ምክንያት ሊኖር አይችልም በማለት የተከራከሩት ጠበቆቹ÷ የተጠርጣሪዎቻቸው የዋስትና መብት እንዲጠበቅ ችሎቱን ጠይቀዋል።

በተጨማሪም አንድ ተጠርጣሪ የቀድሞ አመራር በቁጥጥር ስር ሲውሉ የሰብዓዊ መብታቸውን ተጥሷል የሚል አቤቱታ በጠበቆቹ በኩል ቀርቧል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ÷ የተናጠል ተሳትፏቸው ያልተገለጸው የተጠርጣሪዎቹ ግብረ- አበሮች በመኖራቸው እና የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ የኦዲት ሪፖርት ገና ስላልመጣ ነው ብሏል፡፡

እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ ሌሎች ግብረ- አበሮች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን የጠቀሰው ፖሊስ÷ በክልል ከተሞች፣ በተቋሙ ቅርጫፎች ጭምር የተፈጸመ ወንጀል መኖሩን ገልጿል፡፡

የድምጽ ቅጂ ምርመራ ከሚመለከተው ተቋም የማምጣት፣ የገንዘብ ዝውውርን የሚመለከት የባንክ ማረጋገጫ ማስረጃ የማምጣትና የተጠርጣሪዎችን እንዲሁም የምስክሮችን ቃል የመቀበል ሥራ እንዳልተከናወነ በማብራራት ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

ካለፍርድ ቤት ፈቃድ ብርበራ ተደርጓል ለሚለው የጠበቆች መከራከሪያም÷ ፖሊስ የብርበራ ፈቃድ ቀድሞ ሊያቀርብ ወይም ብርበራ ከተደረገ በኋላ ፈቃድ ከፍርድ ቤት ሊያቀርብ ይችላል የሚል አሻሚ መልስ ሰጥቷል።

አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ሲውል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል ተብሎ የቀረበውን አቤቱታ በተመለከተም ተጠርጣሪን የሚይዝ ሌላ ቡድን መኖሩን እና ጉዳዩን እንደሚያጣራ ገልጿል።

ከተጠርጣሪዎች መካከል 27ኛ ተጠርጣሪ የኢሚግሬሽን ሠራተኛ ባልሆነበት ሁኔታ ሠራተኛ ተብሎ መቅረቡ ተገቢነት የለውም ተብሎ ለተነሳው መከራከሪያ ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ ለረጅም ጊዜ ክትትል ሲያደርግ የነበረው የደኅንነት ተቋም ግለሰቡን ሠራተኛ ነው ብሎ ማቅረቡን ጠቅሶ መልስ ሰጥቷል ፖሊስ።

ባጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ በተቋሙ ውስጥ ካላቸው የሥራ ዕውቀት እና ኃላፊነት አንጻር ማስረጃ ሊያሸሹና ምስክር ሊያባብሉ ይችላሉ በማለት የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

መዝገቡን የሚመለከቱት ዳኛ የፖሊስ የጥርጣሬ መነሻ ምክንያት ላይ የግልጽነት ክፍተት መኖሩን ጠቁመው ለተጠርጣሪዎች ጠበቆች በድጋሚ ሐሳብ እንዲሰጡ ዕድል ሰጥተዋል።

ጠበቆችም የፖሊስ ምላሽ በማስረጃ የተደገፈ አለመሆኑን እና ተጠርጣሪዎችን በእስር ለማቆየት የሚያስችል ምክንያት አልቀረበም በማለት ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎትም÷ ፖሊስ የመነሻ የምርመራ መዝገቡን ለችሎቱ እንዲያቀርብ በማድረግ አጠቃላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለነገ ከሰዓት በኃላ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ – FBC


Exit mobile version