Site icon ETHIOREVIEW

ባለቅኔና ሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ

ከ92 ዓመታት በፊት ጥቅምት 5 ቀን 1924 ዓ.ም የሀገራችን ብርቅዬ ሁለገብ የጥበብ ሰው ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ የተወለደበት ቀን ነው።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበረው ሠዓሊና ባለቅኔ ገብረክርስቶስ ደስታ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስነጥበብ ህዋ ላይ በተለይም አብስትራክት የተሰኘውን እና ዘመናዊ የስዕል አሰራር ስልት በስፋት ከማስተዋወቅ በላይ የራሱ የሆነ የአሳሳል ጥበብ በመጠቀም በሚስላቸው ስዕሎቹ የሀገራችንን ማህበረሰብ ህይዎት በአመዛኙ በመግለጽ የጥበብና የዜግነት ግዴታውን በመስዋእትነት ጭምር የተወጣ የሀገራችን ታላቅ የጥበብ ሰው ነበር።

ሰዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ስዕል በሚያስተምርበት ወቅት ተማሪዎቹ የኢየሱስ ክርስቶስን ስዕል ስለዉ እንዲያመጡ በቤት ስራ መልክ አዘዛቸው። ሁሉም በመሠለዉ መልክ ኢየሱስን ስሎ ሲያመጣ አንድ ተማሪ ግን የክርስቶስን ስዕል በጥቁር ወይም አፍሪካዊ መልክ ስሎ ያስረክባል። ገብረ ክርስቶስ በስእሉ ተገርሞ ለምን ክርስቶስን ጥቁር አድርጎ እንደሳለው ሲጠይቀው ተማሪው «ክርስቶስ ፈረንጅ ሊሆን አይችልም ምክንያቱም ፈረንጆች በጣም ጨካኞች ናቸው። ኢየሱስ ነጭ ሳይሆን ጥቁር ነው» ብሎ ይመልሳል። ይሄን ጊዜ ነው ሰአሊው ገብርዬ ወደቤቱ ሲበር ሄዶ ኢየሱስ ክርስቶስን ቀለም እንዳይኖረው ፣ ዘር እንዳይኖረው ፣ ነገድ እንዳይኖረው አርጎ ከፀጉሩ እስከእግር ጥፍሩ ድረስ በደም ለውሶ ሳለው። በስእሉም ፍቅር ዘር የለውም። ፍቅር ቀለም የለውም። ፍቅር የነገድና የቀለም አጥርን ይሻገራል። ክርስቶስ ሲያድነን ዘር ቀለም ፆታ አልመረጠም። በማለት ለትውልድ አስቀምጦ ሄዷል።

እንደ ዘመናዊ ስዕሎቹ ሁሉ በኢትዮጵያ የስነ ግጥም ባህልም ውስጥ ገብረ ክርስቶስ እንደ አዲስ ዘመናዊ ግጥም ከፍ ያደረገም ነበር። አዳዲስ የግጥም ዘዴ በመከተል በኢትዮጵያ የስነ ግጥም ባህል ውስጥ አዲስ ንቅናቄ የፈጠሩ ግጥሞቹና ቅኔዎቹ የአማረኛ ቋንቋን ጣዕምና ለዛ ግልጽና ቀላል በሆነ ፤ ነገር ግን ቅኔያዊ ውበትን በተጎናጸፈው የገለጻ ሀይል እስከ ባህላዊ ትውፊታችንን ተሻግረው የኢትዮጵያዊያንን ነፍስ የገለፁ ናቸው።

የሀገራችንን መልካምድራዊ ገጽታ ከመቅረታቸውም በላይ ለአገሩ ባህለኛነቱን እና ወገን ወዳድነቱን በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ስብዕናውን አሟልተው የገለጹለት ናቸው።

ከነበሩን ብርቅዬ የጥበብ ሰዎች አንዱ ሁለገቡ የጥበብ ሰው በዘመነ ደርግ በህይወቱ ላይ ባንዣበበ አደጋ በመስከረም ወር 1971 ሀገሩን በስደት ጥሎ እንደወጣ ቀረ ከተሰደደ ከዓመታት እንግልት በኋላ መጋቢት 21 ቀን 1973 ዓ.ም በተወለደ በ 49 ዓመቱ አሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ህይዎቱ አለፈች ፡ በወቅቱ አስክሬኑ ጭምር ሀገር የከዳ ተብሎ ለአገሩ መሬት ሳይታደል ግብአተ መሬቱም እዚያው ተፈጸመ።

ይሄን የህይዎቱን ትራጂዲያዊ ፍፃሜ አስመልክቶ ዛሬ በህይዎት የለሉትና ተቆርቋሪ የስነጥበብ የታሪክ ምሁር ስዩም ወልዴ የሰአሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥሞች 1981 በሚለው ዝክረ ጽሑፋቸው እንዲህ ደምድመውታል። “የገብረክርስቶስ ሞት ተራ የአካል ሞት ነው። ይሁን እንጂ ሞቱን ትራጂዳዊ የሚያደረገው አንድ ቁም ነገር በግጥሞቹ ውስጥ እናገኛለን። በተለያዩ ግጥሞቹ ውስጥ ተመልስ እስኪረግጣት የሚናፍቃት እኔም ከእናንተ የምትበልጥ ሀገር አለችኝ የሚላት ፤ሰው ከሀገሩ ውጭ ሰው አይደለም ብሎ ሲተማመንባት የነበረች ሀገሩ ፣ የህይወቱን የመጨረሻ ህልፈት ሳታስተናግድለት መቅረቷ ነው”።

እንኳን ሞቶ አስከሬኑን ይቅርና ቅፅበታዊ ትንፋሹን እንኳን በባዕድ ሀገር መተንፈስ የማይፈልገው ገብረክርስቶስ በ1973 በኦክላሆማ እስቴት ማረፉ ለሀገር ወዳዱ ድንቅ ባለውለታችን የህይወት መጨረሻ የሚያስታውስ አሳዛኝ ክስተት ነው።

ክብር ለሚገባቸው ክብር ሰጥተን ልንዘክራቸው በዘመን ኮርቻ ወደኃላ እንሳፈራለን | መናኻሪያ ኤፍኤም 99.1

ዓብዱራሕማን ጋሻው


Exit mobile version