Site icon ETHIOREVIEW

ኢትዮጵያ አበራች!!” የደርግ” ብለው አፈረሱት፤ በአገሩ መከላከያ ጉዳይ ከዚህ በሁዋላ የሚታለል ኢትዮጵያዊ አይኖርም!!

የኢትዮጵያ ደሟ፣ የኢትዮጵያዊያን የመጨረሻ ክብራቸው፣ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በልባቸው የሚያነግሱት፣ ታሪክ ለአፍታም የማይዘነጋው፣ ትውልድ ሁሉ አግዝፎ የሚያከብረው፣ ደሙን የሚያካፍለው፣ ምድሪቱ ውለታዋን ቆጥራ እስከማትጨርስ ድረስ በክብር የምትሞሽረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዳግም ከመፍረስ ተርፎ 116ኛውን የምስረታ ዓመቱን ለማክበር መብቃቱ ከኩራትም በላይ ብዙ ሚስጢሮች አሉት። ለዚህ ታሪካዊ ቀን ላበቁ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ምስጋና ሲያንስ ነው።

ትህነግና ሻዕቢያ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ህዝብ ማህጸን ውጤት የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት “የደርግና የመንግስቱ አገልጋይ” በማለት እንዳፈረሱት ይታወቃል። እነሱ እንደ ምክንያት ይሁኑ እንጂ ኢትዮጵያን ማኮሰስ፣ ማሳነስና ደካማ ማድረግ አጀንዳቸው የሆኑ የውጭ ሃይሎች ባጠመዱት ወጥመድ፣ ከውስጥ ባሉ ባንዶችና ከሃዲዎች ትብብር የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንዲበተን፣ አገር በታደገ እንደ ነውረኛ ተቆጥሮ በአደባባይ ለማኝ እንዲሆን መደረጉ የዚህ ትውልድ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ኢትዮጵያ የመከላከያ ሃይሏ መሪ አልባ እንዲሆን ሆን ተብሎ እንዲከሽፍ በተዘጋጀ መፈንቅለ መንግስት ጀነራሎቿን ያስፈጁ፣ አስከሬናቸው አደባባይ እንዲጎተት ያደረጉ ባንዳዎችና የባንዳ ልጆች ዳግም እቅዳቸው መክኖ እንደገና ከመፍረስና መበትን የዳነው የኢትዮጵያ መከላከያ ለዚህ ታሪካዊ ቀን ምብቃቱ አገራቸውን ለሚወዱ ሁሉ ኩራት ነው። ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚጋብዝ ነው። አገር መበተንና ማጽናት ምን ማለት እንደሆነና በእነ ማን እንብደሚሰራ የሚለይበትም ነው።

የሶማሌው ቅጥረኛ ዚያድባሬ በምስራቅ ከ600 ፣ በምዕራብ ከ300 በላይ ኪሎሜትር ዘልቆ በወረረ ማግስት አገራዊ ጥሪ ተቀብሎ ወራሪውን ሃይል በአጭር ጊዜ አፈር ያስጋጠውን ነበልባል፣ ፓራ ኮማንዶ፣ ሚሊሻና መላው የመከላከያ ሰራዊትና አየር ሃይልን በደባ አፍርሰው የካቲት 7 ቀን 1987 የመከላከያ ሰራዊት ዓመታዊ በዓል እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል።

ቀደምት አባቶቻችን የተዋደቁለትን ባንዲራና የሰራዊት አደረጃጀት ከእነ ታሪኩ ቀብሮ በነጻ አውጪ ሰራዊት ታሪክ የተካው ትህነግ ኢህአዴግ ይህን ያደረገበት ምክንያት በወቅቱ የገባቸው ቢቃወሙም ሰሚ አላገኙም ነበር። የኢትዮጵያን ገድልና አብረቅራቂ የጀግንነት ታሪክ እንዳልነበረ አድርጎ ከየካቲት 7 ቀን 1987 ጀመሮ የመከላከያ ሃይል ታሪክ በኢትዮጵያ እንደተጀመረ አድርጎ ያወጀው ትህንግ፣ እንዳሰበው ሳይሆን 119 ዓመት ወደሁዋላ በመሄድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ታሪክ አምሮና ደምቆ ለትውልድ እንዲቀርብ መደረጉ አሁንም ኩራት ነው። ይህን ለማየት የበቁ አንጋፋ የጦር መኮንኖችና የተገፉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትም እንኳን ደስ ያላችሁ።

በቅርቡ ” በቅጽበታዊ ጥቃት” ብሎ መከላከያን በማረዱና በመክዳቱ ሲመጻደቅም የነበረው ትህነግ፣ ደሙን ጠርጎ፣ እልህና ቁጭት ሰንቆ፣ በገዘፈ የሞራል ልዕልና እንደ እቶን ነዶ፣ ህዝብን አስተባበሮና አካባቢያዊ አደረጃጀቶችን አጣምሮ ለድል የበቃው የኢትዮጵያ መከላከያ ” ጠፋ፣ ከሰማ፣ ሞተ…” በሚል ሲያሟርቱበት ለነበሩት ሁሉ መርዶ የሆነ ክብረ በዓል ማሳየቱ ” ተመስገን” የሚያሰኝ ታላቅ ሃሴት ነው።

የተበተነውና የፈረሰው ወታደራዊ ፖሊስ፣ ፓራ ኮማንዶ፣ አየር ወለድ፣ ልዩ ጋርድ … በዘመናዊ ትጥቅና አቋም ታጅቦ ኢትዮጵያዊያን ፊት እንደ አንበሳ እያገሳ ሲተም ማየት አገራቸውን ለሚወዱ የሚፈጥረው ስሜት ልዩ ነው። ቃላት አይገልጸውም። በተቃራኒ ባንዳዎች፣ የባንዳዎች አገልጋዮችና በቀቀኖቻቸው ይህን ሲያዩ የሚሰማቸው ስሜት መራራ እንደሆነ ሳይታለም የሚፈታ ነው።

በኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ፣ ይህ ሃይል ለኢትዮጵያ ጠላቶች ክንደ ብርቱ ሆኖ ኢትዮጵያ ወደ ልማቷ እንድታመራ ሁሉም ዜጋ ድጋፉን ሊያበረታ ይገባል። ልዩነት ያላቸው አካላት ባለመረዳት አሳባቸውን ጠልፈው የአገራችንን መከላከያ ዳግም ለማፍረስ ወጥነው ለሚሰሩ ሲሳይ ከመሆን እንዲታቀቡ ያስፈልጋል።

ይህን አይነት ሃይል በአጭር ጊዜ የገነባ መንግስትም ሆዱን አስፍቶ ለሰላም ያለውን ቁርጠኛነት በማጠንከር ኢትዮጵያ የሰላማና የመረጋጋት ምሳሌ እንድትሆን እንዲሰራ ግዴታ አለበት። የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊያንን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ፣ ጥቅሟን በማስቀደም ውይይት ማድረግና ሰላምን ማስፈን ልክ እንደ መከላከያ ግንባታው ልዩ ትኩረት የሚያሻው ነው።

ባለስልጣናት እዚያና እዚህ በመርገጥ፣ ግጭትን የሌብነታችሁ መመከቻ በማድረግ የምታደርጉት ሩጫ እያበቃለት መሆኑንን፣ እዛና እዚህ በመርገጥ ህዝብን ማጋደል የሚቀጥል እንዳልሆነ ተረድታችሁ፣ በዚህ አካሄድ አትራፊ መሆን እንደማይቻል ከልብ አምናችሁ ወደ ልባችሁ ተመለሱ። ከደም ነጋዴዎች ጋር ሆናችሁ ፖለቲካዊ ውስልትና ውስጥ የገባችሁ ከህዝብ አታመልጡምና አቁሙ።

የዛሬው ወታደራዊ ትርኢት ያልታየውን ጨምሮ “መከላከያ የገሌ ነው፣ የገሌ ብሄር ነው” በሚል የሚዛበቱ ዓላማቸው ምን እንደሆነ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። በግልጽ ይህን አስፈሪ ሃይል ማፍረስ ነው። “የደርግ” ብለው አፈርሱን። ዳግም የሚሸወድ ትውልድ የለም። በዚህ ክፉ አሳብ ተከፍሏችሁም ሆነ ሳንቲም እየለቀሙ የሚተፉ ሁሉ ተስፋ ቆርጠው ቢተውት ይሻላል። አገርንና መንግስትን፣ ተቋምንና ፖለቲካን በመለየት መስራት ከሚዲያ ይጠበቃል። በስመ ዩቲዩበርነት ለሳንቲም ብሎ አገር ላይ በነጋ በጠባ ሟርት፣ እልቂት፣ ሃዘን፣ ጥፋትና ሞራል የሚነካ ወሬ መርጨት በየትኛውም መመዘኛ አያስኬድም። ተቀጣሪነትም ቢሆን አይኖርም። ከስራ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ያለው ነው!!

“ኢትዮጵያ ፈተናን ወደ ድል የሚቀይር የአሸናፊ ሠራዊት ባለቤት ናት”

መላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን አደረሳችሁ!

በዛሬው ዕለት 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በሀገርአቀፍ ደረጃ እየተከበረ ነው፡፡ ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ/ም በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ስፍራ አለው፡፡ ዕለቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተቋማዊ መልክ ተላብሶ በሚኒስቴር ደረጃ የተመሰረተበት ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያ 116 ዓመታትን ያስቆጠረ፤ በትውልድ ቅብብሎሽ ፀንቶ የቆየና ሀገርን ያፀና የመከላከያ ተቋም ባለቤት መሆኗ ዛሬ ላይ ለጠንካራ ተቋማት ግንባታ ትልማችን እንደ ወረት የሚወሰድ በጎ የታሪካችን አካል በመሆኑ እለቱ በሀገርአቀፍ ደረጃ ይዘከራል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከተመሠረተበት ከዛሬ 116 ዓመት በፊት ጀምሮ የአያት ቅድመ አያቶችን ወኔ፣ የሀገር ፍቅርና ጀግንነት ተላብሶ በፅናት ቀጥሏል፡፡ በደም መስዋዕትነት በተጻፈው አኩሪ ታሪኩ ሀገርን እየታደገ ዛሬ ላይ የደረሰው መከላከያ ሠራዊታችን፤ ምንግዜም ቢኾን ቃልኪዳኑ እናት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ መከላከያ ሠራዊታችን አንድ ክፍለ ዘመን በተሻገረ ታሪኩ ሀገር አፅንቷል፣ ሉዓላዊነታችንን አስከብሯል፣ የግዛት አንድነታችንን አስጠብቋል፣ በደምና አጥንቱ ኢትዮጵያን ከትውልድ ወደ ትውልድ አሸጋግሯል፡፡

መከላከያ ሠራዊታችን በዘመናት መካከል ኢትዮጵያ ላይ የሚደቀኑ ፈተናዎችን በፅናትና በጀግንነት እየተሻገረ የሚያሸንፍ ድል አብሳሪ ሠራዊት ሆኖ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች ዘመናዊ የውትድርና ስልጠና ሳያገኙና ዘመናዊ መሳሪያ ሳይታጠቁ በወቅቱ እጅግ የተደራጀውን የወራሪ ኃይል በአድዋ ድል አድርገው ለቀጣይ ትውልድ ነፃ ሀገርን አስረክበዋል፡፡ በፋሽስት ጣልያን ወረራ ወቅት ራሳቸውን ‟ጥቁር አንበሳ” በሚል ስያሜ አደራጅተው ለአምስት ዓመታት በዱር በገደሉ ሲዋደቁ የነበሩት የኢትዮጵያ አርበኞች ሀገራቸውን ለድል አብቅቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ መከላከያ ሠራዊታችን በካራማራ ተራራ ወራሪውን ኃይል በመምታት ዳር ድንበራችንን አስከብሯል፡፡ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የኢትዮጵያ ህልውና ላይ አደጋ የደቀኑ ኃይሎችን በሙሉ በተለያዩ ጊዜያት በጥንካሬ በመዋጋት ክቡር መስዋዕትነት የከፈለውም ይኸው ለዘመናት ሲገነባ የመጣው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው፡፡

ከሀገር ውስጥ አልፎ ዝናው በዓለም የናኘው መከላከያ ሠራዊታችን፤ በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያና በሌሎችም ሀገራት የሰላም ማስከበር ግዳጆቹን በብቃት በመወጣት የጀግነታችን ምልክትና የኩራታችን ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በመሆኑም ከጥንት እስከ ዛሬ የሉዓላዊነታችን ዋስትና፣ የኩራታችን ምንጭ፣ የፈተና ጊዜ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት ቀንን በሃገርአቀፍ ደረጃ ማክበር ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችንን ማክበር ነው፡፡

ዛሬም እንደ ትላንቱ በየቦታው ከሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ጋር በመፋለም ሀገሩን እያፀና፤ የሕዝብንም ሰላም እያስጠበቀ የሉዓላዊነት ዋስትና፣ የክፉ ቀን ምሽጋችን ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ቅዠታቸውን እውን ለማድረግ ከዛሬ አሻግረው ነገን የማያስቡ ፅንፈኞች የጀግናውን መከላከያ ሠራዊታችን ስም በሀሰት ለማጠልሸት ዘወትር ያለ እረፍት ቢተጉም ሰራዊታችን ለእናት ሀገሩ የገባውን ቃልኪዳን በልቡ አኑሮ በዚህች ሰዓትና ደቂቃ ሳይቀር በየጦር ሜዳው ለሃገሩ ተጋድሎ እያደረገ ነው፡፡ መከላከያ ሠራዊታችን ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በመጠበቅ፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመፋለም፣ ዳር ድንበርን በማስከበር በሰማይም ኾነ በምድር ኢትዮጵያችንን ቀን ለሊት ፈተናዋን እያሻገረ፤ ሞቷንም እየሞተላት ነው፡፡

በመሆኑም ኹሉም ኢትዮጵያዊ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሚከፍሉትን ታላቅ መስዋዕትነት በመገንዘብ የተለመደውን ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ በየተሰማራንበት የሥራ ገበታ እንደ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሁሉ በወኔ፣ በትጋትና በፅኑ የሀገር ፍቅር ስሜት ልንሠራ ይገባል፡፡

በተፈተነ ጊዜ ኹሉ የሚፀና የድል ሠራዊት!

ክብር ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት!

-ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት


Exit mobile version