Site icon ETHIOREVIEW

“በተቀደሱት ቅርሶች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም” የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር

ከሰሞኑ በታሪካዊቷ ከተማ በተከሰተ ግጭት ምክንያት የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ደኅንነት መነጋገሪያ ኾኖ ሰንብቷል፡፡ ለዓመታት ከእነ ግርማቸው እና ውበታቸው የዘለቁት፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ የሃይማኖት፣ የባሕል እና የጥበብ ማሳያ የኾኑት ቅርሶች ጥቃት እንደደረሰባቸው የሚገልጹ መረጃዎችም በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ሲገለጡ ቆይተዋል፡፡

“የተቀደሱት ቅርሶች በከባድ መሣሪያ ተመትተዋል፤ ቅርሶቹ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል” የሚሉ መረጃዎች በስፋት ሲሰራጩ ሰንብተዋል፡፡ በእርግጥ ቅርሶቹ በቀጥታ መመታት አለመመታታቸው ሳይኾን በቅርብ ርቀት የከባድ መሣሪያ ተኩስ ካለ ለቅርሶቹ አደጋ ነው፡፡ በተኩስ ልውውጦች የሚፈጠረው ንዝረት ለዓመታት የቆዩትን ቅርሶች ይጎዳቸዋልና፡፡

አሚኮ በላሊበላ የደረሰውን ግጭት እና የተቀደሱት ቅርሶችን ደኅንነት በተመለከተ ከከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ወንድምነው ወዳጅ ከሰሞኑ በላሊበላ ከተማ አሥተዳደር እና በላስታ ወረዳ ግጭቶች መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡ በተፈጠረው ግጭት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ወድመቶችን አስተናግዳለች፤ በማኅበረሰቡ ላይ የሥነ ልቡና ጫና አሳድሯል ነው ያሉት፡፡ በከተማዋ የነበሩ ሰላማዊ እቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውንም ገልጸዋል፡፡

በተፈጠረው ግጭት ማኅበረሰቡ ለማይገባ ሥነ ልቡናዊ ጉዳት እና ተደጋጋሚ መስተጓጎል መዳረጉንም አመላክተዋል፡፡ የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት እና ማኅበረሰቡ ወደ መደበኛው ማኅበራዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

በነበረው ግጭት መነሻነት በቅርሶቹ ላይ የሚናፈሱ መረጃዎች መኖራቸው ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከሁሉም የሚቀድመው የፈጣሪ ቅርስ ሰው ነው፣ የሰው ሕይወት እያለፈ ነው፣ ለላሊበላ ከተማ ማኅበረሰብ ጦርነት ይገባዋል ብለን አናምንም ብለዋል፡፡ ከተማዋ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች የሚኖሩባት ናት፤ የከተማዋ እጣ ፈንታ ቱሪዝም ነው፣ ለቱሪዝም ደግሞ ሰላም ያሥፈልጋል ብለዋል፡፡

ከተማዋ ባለፉት አራት ዓመታት የቱሪዝም ፍሰቷ በእጅጉ እየወረደ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ የቱሪዝም እቅስቃሴዋ ሙሉ በሙሉ መቆሙንም አመላክተዋል፡፡ በቅርሱ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ሁሉ ሰላምን ማስቀደም ይገባዋልም ብለዋል፡፡ በቅርሱ ላይ አላስፈላጊ መረጃዎችን የሚያወጡ አካላት ሰላምን ቢሰብኩ፣ ካላስፈላጊ መረጃዎች ቢቆጠቡ እና ሐሰተኛ መረጃዎችን ከማሰራጨት ቢርቁ የተሻለ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ጦርነት መከሰቱ ልክ ነው፣ በጦርነቱም ከሰው ሕይወት መጥፋት እስከ ንብረት ውድመት ጉዳት ደርሷል፤ ነገር ግን ቅርሱ ተመትቷል እየተባለ የሚወራው ውሸት ነው፤ እውነታው ይሄ ነው፤ የትኛውም አካል ቅርሱን መጥቶ ማየት ይችላልም ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፡፡

በአካባቢው የተከሰተው የሰላም እጦት ቅርሱን ይጎደዋል ብሎ የሚያምን እና ለቅርሱ የሚቆረቆር ሰላምን ማስቀደም እና ጦርነትን ማስቆም አማራጩ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በውጭም ኾነ በሀገር ወስጥ የሚገኙ የሚዲያ አካላት ቅዱሱን ቦታ ለመጠበቅ ስለ ሰላም መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ አካባቢው ሰላም ሲኾን ቅርሱ ይጠበቃል፤ በምጣኔ ሃብት የተጎዳው ማኅበረሰብም ይነቃቃል ነው ያሉት፡፡

ከሕግ ማስከበር ከተደረገው ጦርነት ማግሥት መነቃቃት ላይ የነበረው የላሊበላ ቱሪዝም አሁን ላይ ባለው የሰላም እጦት ምክንያት አቁሟል፡፡ ነዋሪዎቹም ለችግር ተዳርገዋል፡፡ በከተማዋ ከደረሰው የንብረት ውድመት የላቀው ውድመት እና ኪሣራ የሥነ ልቡናው ኪሣራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ በከተማዋ ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ስለ ሰላም መስበክ አለበት ነው ያሉት፡፡

ሰላምን እንደ ቀላል ነገር መመልከት እና ዋጋውን ማሳነስ እንደማይገባም ገልጸዋል፡፡ በሀሳብ እና በውይይት ችግሮች ቢፈቱ ትርፋማ እንኾናለን ብለዋል፡፡ ሕግ አክባሪነት እና ሥርዓት የሁሉም ጉዳይ ሊኾን እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ከግጭት ይልቅ እያንዳንዱ ሰው ለሰላም የሚጠበቅበንት ሚና መወጣት አለበትም ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ መንግሥት እና ሌሎች አካላት ለሰላም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡

ሚደያዎች ሐሰተኛ መረጃዎችን በማራገብ ችግሩን ከማባባስ ተቆጥበው እውነተኛ መረጃዎች ላይ ተንተርሰው እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በቃላት ሀገርን ከማጥፋት በቃላት ሀገርን መገንባት እንደሚሻልም ተናግረዋል፡፡

የአምላክ ሥራ የኾነው እና ቀዳሚ ቅርስ የሰው ልጅ እንዳይሞት መቆርቆር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ሞት የሚቆምበት ጊዜ እንዲመጣ መላው የአማራ ክልል ሕዝብ አንድነት እንዲቆም እና ስለሰላም እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ / (አሚኮ)

“ላሊበላ ጉዳት ደረሰበት በሚል የሚናፈሰው ወሬ መሠረት ቢስ ነው” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ

ባሕር ዳር፡ ኅዳር 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ቀደምት ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ነው። የክልላችን ሃብት፣ የሀገራችን ኩራትና ኢትዮጵያዊያን የቀደምት ስልጣኔ ባለቤቶች መሆናችን ማሳያ መኾኑን ቢሮው ገልጿል።

በዚህ የዓለማችን ቀደምት ቅርስ ስም ሐሰተኛ ፕሮጋንዳ እየነዙ፤ ሕዝብን እያደናገሩ አሸናፊ ለመሆን መሞከር ሞራላዊና ኅሊናዊ ኪሳራን እንጅ ድልን አያጎናጽፍም ብሏል ቢሮው በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ባጋራው መረጃ።

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በሚገኘው የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተደርጎ ከትናንት ጀምሮ የሚናፈሰው ወሬ መሠረት ቢስ ነው።

በላሊበላ ስም መቀደስ እንጅ የጥፋት ድግስ መደገስ አስፈላጊና ተገቢ አይደለም። የላልይበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ቦታውም ቅዱስ ነው ህንጻውም ሰላም ነው ብሏል ቢሮው።


Exit mobile version