Site icon ETHIOREVIEW

ብሄራዊ ባንክ የገንዘብ ቁጥጥሩን አጠንክሮ እንደሚገፋበት አስታወቀ፤ ህገወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጀ

በአገሪቱ የሚታየውን የዋጋ አለመረጋጋት ለመግራት የግንዘብ ስርጭት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የተጀመረው ስራ ውጤት እያሳየ መሆኑ ተመለከተ፤ ተጠናክሮ ክምሩ እንደሚሰራበትና ግሽበትን በዓመቱ መጨረሻ 20 ከመቶ ለማድረስ መታቀዱ ተሰማ። ህገወጥ የወርቅ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና የማበረታቻ መደረጉ ለውጥ ቢያሳይም በቂ እንዳልሆነ ተመለከተ።

ይህ የተገለጸው የባንኩ ገዥ ማሞ ምኅረቱ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው።

በሪፖርታቸውም በ2015 የበጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 2 በመቶ ማደጉን አስታውሰው፤ ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ በ6 ነጥብ 5 በማደግ ጠንካራና አበረታች ውጤት እንደተመዘገበ ተናግረዋል።

ባለፉት ሥድስት ወራት ውስጥ የዋጋ ንረቱ በተከታታይ ቅናሽ አስመዝግቧል ያሉት አቶ ማሞ÷ ምንም እንኳን የዋጋ ንረቱ አሁንም ከፍተኛ ቢሆንም ሂደቱ ግን እየቀነሰ መሆኑን አሃዞች ያሳያሉ ነው ያሉት፡፡

ለአብነትም ያለፉትን አራት ወራት መረጃዎች በመስከረም ወር በገመገምንበት ወቅት የኑሮ ውድነቱ በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም ከነበረበት 35 በመቶ ገደማ ወደ 27 ነጥብ 7 በመቶ መቀነሱን ዐይተናል ብለዋል፡፡

ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ንረት አሁንም ከ30 በመቶ አለመውረዱን ገልጸው÷ በአንጻሩ የምግብ ነክ ዋጋ ንረት በሩብ ዓመቱ መጨረሻ 26 ነጥብ 1 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ የዋጋ ንረት የቆየ መሠረታዊ ችግር መሆኑን የገለጹት የባንኩ ገዥ÷ አሁን ያለበት አሃዝ ዝቅተኛ ነው ባይባልም ሂደቱ ግን ቅናሽ እያሳየ መሆኑን ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡

ከመድኃኒትና ሕክምና አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ያለውን የዋጋ ንረት ለማስተካከል ከጤና ሚኒስቴር ጋር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የዋጋ ንረቱ መንስኤዎች የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች (በተለይም በሩሲያና ዩክሬን መካከል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የሸቀጥ ዋጋ መጨመር)፣ በትራንስፖርት አውታሮች፣ የሎጂስቲክስ ሥርዓትና የችርቻሮ/የጅምላ ንግድ ተወዳዳሪነት ድክመት እንዲሁም የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን፣ የምርትና ምርታማነት በበቂ ሁኔታ አለማደግ እንደሆኑ አብራርተዋል።

በተጨማሪም የፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲ ልል መሆን እና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው አለመረጋጋት ለዋጋ ንረቱ ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለማስተካከል በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አመላክተው፤ እንደ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች መደረጉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ባንኮች የሚሰጡት ብድር ዕድገት ከ14 በመቶ እንዳይበልጥ ገደብ አስቀምጠናል ነው ያሉት፡፡

እንዲሁም የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ የሚወስደውን ብድር በ75 በመቶ ቀንሰናል ብለዋል፡፡

ባንኩ የተለያዩ የገንዘብ ፖሊሲዎች ላይ ጠንካራ ውሳኔዎችን በማሳለፉም አሁን ላይ የተረጋጋ የዋጋ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ ምርት እንዲጨምር በህገወጦች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2016(ኢዜአ):- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ ምርት እንዲጨምር በህገወጦች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

ለህጋዊ አምራቾች ማበረታቻ በመስጠት ለባንኩ የሚቀርበው የወርቅ ምርት እንዲጨምር እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ተጠሪ ተቋማት በ2016 በጀት የባንክ የሩብ ዓመት አፈጻጸም ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ውይይት አድርገዋል።

የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ወርቅ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ወርቅ ወደ ውጪ በመላክ እስከ 600 ሚሊዮን ዶላር ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፤ በህገወጥ ንግድና በተለያዩ ችግሮች ገቢው እያሽቆለቆለ መጥቷል ብለዋል።

በተለይም ወርቅ አምራች በሆኑ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እንዲፈጠርና ሃብቱ በህገወጥ መንገድ እንዲወጣ በማድረግ አንዳንድ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጭምር እጃቸው እንዳለበት ነው ያነሱት።

በመሆኑም ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የወርቅ ምርት እንዲጨምር የክልል መንግስታት ጠንካራ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አክለውም ባንኩ ከጸጥታና ደህንነት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ህገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይትን ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

ማዕድናት በአግባቡ ተመርተው ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ የባለድርሻዎች የትብብር መድረክ መቋቋሙን ያነሱት የብሔራዊ ባንክ ገዥ፤ ለወርቅ አምራቾች እስከ 70 በመቶ ማበረታቻ በመስጠት የተሻለ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ በበኩላቸው፤ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ ምርት በበቂ ሁኔታ ለማዕከላዊ ገበያ እንዲቀርብ ተጨማሪ መመሪያና ፖሊሲ ማውጣት አለበት ብለዋል።

ህገ-ወጥ የወርቅ ግብይትን ለመከላከልም ሌሎች ባለድርሻዎች ባንኩን ማገዝ እንዳለባቸው በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ መከላከል ላይ በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል።

source ENA, FBC, walata

Exit mobile version