ETHIOREVIEW

ሰው በማገት 10 ሚሊየን ብር የጠየቁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ጋር ባደረጉት ክትትል ወጣቱን አግተው 10 ሚሊዮን ብር የጠየቁ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የእገታ ወንጀል የተፈፀመበት ወጣት ልዑል መብራቱ ፀጋዬ ይባላል፡፡ ወጣቱ በማህበራዊ መገናኛ አውታር አማካኝነት ባንቴ ይድረስን የተባለውን ግለሰብ ይተዋወቃል።

የወንድሜ ጓደኛ ቤት ላሳይህ በማለት ወጣቱን ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ/ም ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ቁሊቲ መንደር 4 አካባቢ ይዞት ከሄደ በኋላ ከግብረ አበሩ ልዑል ጫላ ጋር ያግቱታል፡፡ ዘግናኝ ፊልሞችንና ፎቶግራፎችን ለወላጆቹ በመላክ 10 ሚሊዩን ብር ካልተከፈላቸው ወጣቱን እንደሚገድሉት የማስፈራሪያ መልእክት ይልካሉ፡፡

የእገታ ወንጀል እንደተፈፀመ ሪፖርት የደረሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ጋር ባደረጉት ጠንካራ ክትትል ወንጀሉን በተፈፀመ በአራተኛው ቀን ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ወጣቱን ከእገታው ነፃ ማውጣት ተችሏል፡፡

ሁለቱ ግለሰቦች ወንጀሉን ለመፈፀም በ5ሺ ብር ቤት መከራየታቸውንና የታጋቹ ወጣት ወላጅ አባት ውጭ ሀገር ይኖራሉ በሚል መረጃ ወንጀሉን መፈፀማቸው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ዘሪሁን ተፈራ አስታውቀዋል፡፡

ያልተገባ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት መሰል የእገታ ወንጀሎችን እንደሚፈፅሙ ኃላፊው ተናግረው መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከልና አጥፊዎችን ህግ ፊት ለማቅረብ የህብረተሰቡ ሚና ወሳኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠትና ወንጀለኞችን በማጋለጥ በኩል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በልዩ ልዩ ምክንያት የምንቀርባቸው ግለሰቦች ማንነታቸውን ጊዜ ወስደን ማረጋገጥ አለብን ያለው ፖሊስ በተለይ ሙሉ ቤት የሚያከራዩ ግለሰቦች የተከራዮችን ማንነትና ለምን እንደተከራዩ ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ይህን ሳያደርጉ በሚፈጠር ችግር የህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አዲስ አበባ ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

ታህሳስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Exit mobile version