ETHIOREVIEW

ፖሊስ አዲስ አበባን ከወንጀለኞች እያጸዳ መሆኑን አስታወቀ 5536 ተጠርጣሪዎች ከማስረጃ ጋር ተያዙ

በአዲስ አበባ ከተማ እየካሄደ ያለው የተቀናጀ ኦፕሬሽን በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ፖሊስ ዝርዝር መረጃና የወንጀል አይነቶችን ዘርዝሮ ይፋ እንዳደረገው አምስት ሺህ አምስት መቶ ሰላሳ ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ህዝብን ሲያማርሩና ጭካኔ የተሞላበት ወጅለ ሲፈጽሙ እንደነበር በዝርዝር ተጠቅሶ የተያዙ ተጠርጣሪዎች የሜትር ታክሲዎችን ይጠቀሙ ነበር። በአሰቃቂ ሁኔታ ሰዎችን እያፈኑ የሚገሉና የተለያዩ ከባድና የረቅቁ ወንጀሎችን ሲያከናውኑ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

ኦፕሬሽኑ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የሚመራ ሲሆን፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ከፍተኛ ውጤት እንዳስመዘገበ ዛሬ በተሰጠ ጋዜታዊ መግለጫ ተመልክቷል። ዘመቻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

በሞባይል ንጥቂያና ስርቆት ኅብረተሰቡን ያማረሩ ተጠርጣሪዎች ከ1 ሺህ 7 መቶ 77 የተለያዩ ሞባይሎች ጋር መያዛቸውን ያመለከተው መግለጫው፣

ፖሊስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከታህሳስ 6 እስከ 11 2016 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በተካሄዱ የኦፕሬሽን ሥራዎች ከአንድ ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎችን ከበርካታ ልዩ ልዩ ኤግዚቢቶች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ታህሳስ 12 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቁን አስታውሷል።

የፖሊስ ተቋማቱ በየጊዜው የደረሱበትን ውጤት እየገመገሙ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ በገቡት ቃል መሠረት ለሁለተኛ ሣምንት ያካሄዱትን የተቀናጀ ኦፕሬሽን ውጤት በመገምገም ታህሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት በርካታ የመገናኛ ብዙሃን በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ መሰረት፦

1. አፈና በማካሄድ በግዲያ ወንጀል የተጠረጠሩ፣

2. በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ የተደገፈ የዘረፋ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ከተጠርጣሩ ግለሰቦች የተያዙ የተለያዩ 26 ሽጉጦች ከመሰል 281 ሽጉጥ ጥይቶች ጋር፣

3. ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ የግድያና የመኪና ዝርፍያ ወንጀል በመፈፀም ተጠርጥረው አዲስ አበባ ከተማ ተሸሽገው የተገኙ ተጠርጣሪዎች ከዘረፉት መኪና ጋር በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ጨምሮ 35 የተለያዩ መኪናዎች፣

4. ወንጀል ለመፈፀም የሚጠቀሙባቸው 373 የተለያዩ ሞተር ሳይክሎች፣

5. 891 የተለያዩ የመኪና ስፖኪዮ እና 1 ሺህ 4 መቶ 66 የተለያዩ የመኪና መለዋወጫዎች፣

6. 73 ኪሎ ግራም አደንዛዥ ዕፅ፣

7. በወንጀል ተባባሪ በመሆን የተጠረጠሩ የሜትር ታክሲዎች፣

8. በሞባይል ንጥቂያና ስርቆት ኅብረተሰቡን ያማረሩ ተጠርጣሪዎች ከ1 ሺህ 7 መቶ 77 የተለያዩ ሞባይሎች ጋር፣

9. 176 የሺሻ ማስጨሻ ቤቶች እና 1 ሺህ 1 መቶ 14 የቤቲንግ ቤቶች ታሽገዋል፣

10. 509 ሺህ 334 የቁማር መቆመሪያ ብር፣

11. 345 የተለያየ የመኪና ታርጋ፣

12. ከበአድ ነገር ጋር የተቀላቀለ 189 ኩንታል የምግብ ዱቄት፣

13. የተለያዩ ኢንች ያላቸው 169 ቴሌቭዥኖች፣

14. ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና 861 ሺህ 240 ብር፣ 35 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እና በርካታ የተለያዩ ሀገራት ገንዘብና ሐሰተኛ ኖቶች፣

15. ከፍተኛ የሞባይል ባንክንግ ማጭበርበር ወንጀል ጋር በተገናኘ አንዳንድ የባንክ ሠራተኞች ጭምር የተሳተፉበት ከባንክ ደንበኞች ገንዘብ በመውሰድ የተጠረጠሩ ሲጠቀሙባቸው ከነበሩ 190 ሲምካርዶች ጋር በተካሄደው ኦፕሬሽን በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ስለሆነም የተደወለባቸውን ስልክ ቁጥሮች ለኅህብረተሰቡ ይፋ ስለሚደረጉ የተጭበረባራችሁ ግለሰቦች በአቅራቢያችሁ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ እየቀረባችሁ ማመልከት የምትችሉ መሆኑን ፖሊስ በመግለጫው ጠቁሟል።

16. ቲቶክን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ መረጃ ያሰራጩ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በአጠቃላይ በተካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን 5 ሺህ 5 መቶ 36 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል ብሏል መግለጫው።

ከፖሊስ ተቋምም በእነዚህ ወንጀሎች ላይ ተሳትፈው የተገኙትን አመራርና አበላት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራባቸው እንደሚገኝ መግለጫው አክሎ ገልጿል።

በተካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን የከተማው ሰላምና ደኅንነት በከፍተኛ ደረጃ እየተረጋገጠ መምጣቱን እና 37 ነጥብ 8 በመቶ ወንጀል መቀነስ መቻሉን ፖሊስ በመግለጫው ጠቅሷል።

በቀጣይም ኅብረተሰቡን ባማረሩ ወንጀሎች ላይ የሚካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ ይቀጥላል ያለው መግለጫው ኅብረተሰቡ እንደተለመደው ሁሉ ለፖሊስ መረጃ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

ምንጭ አዲስ አበባ ፖሊስ

Exit mobile version