Site icon ETHIOREVIEW

ሸይኽ አብዱ ያሲን በተተኮሰባቸው ጥይት ተመተው ተገደሉ፤ ዓላማው የሙስሊሙን ህብረተሰብ ወደ ዓመጽ ለማስገባት እንደሆነ እየተሰማ ነው

በቀብር ስነ ስነ ስርዓታቸው ላይ የግድያው ምክንያት ሳይጣራ ያልተረጋገጡና የምርመራ ሂደቱን የሚያበላሹ መረጃዎችን ከማሰራጨት መቆጠብ እንደሚገባ በሚመልከታቸው አካላት መልዕት

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አስኮ አዲስ ሰፈር የበድር መስጂድ ኢማምና ኸጢብ እንዲሁም በመስጂዱ የተለያዩ ኪታቦችን በማቅራት የሚታወቁት አቅሪ ሸይኽ አብዱ ያሲን ትላንት ምሽት ላይ ከዒሻ ሰላት በኃላ ባልታወቁ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይት የራስ ቅላቸውን ተመተው ህይወታቸው አልፏል። ገዳዮቹ ባይታወቁም ግድያው የረጋውን የሙስሊም ህብረተሰብ ወደ ዓመጽ ለመክተት ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ብለው የሚያምኑ መኖራቸው ተሰምቷል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፤ መንግስትና ባለድርሻ አካላት አስቸኳይ የማጣራት ተግባር በማድረግ የኢማሙን ገዳይ ለሕግ እንዲያቀርቡ እንዲሁም ህብረተሰቡ የጸጥታ አካላት ለሚያደርጉት ምርመራ አጋዥ ሊሆን የሚችል መረጃ በማቀበል የኢማሙ ገዳዮች እንዲታወቁ ለህግ እንዲቀርቡ የበከሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፏል። መጅሊስ በህልፈተ ህይወታቸው ማዘኑንም ከጥልቅ ሃዘን ጋር አስታውቋል።

ምክር ቤቱ አሳዛኝ እና አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ህይወታቸውን ላጡት ኢማም ሼይኽ አብዱ ያሲን አላህ እንዲምራቸው፣ ማረፊያቸውንም በጀነተል ፊርዶስ እንዲያደርግላቸው፣  የሸሂድነትን ማዕረግም እንዲያጎናፅፋቸው እንዲሁም ለቤተሰባቸውና ለመላው ሙስሊም ማህበረስሰብ መፅናናትን እንዲሰጥ አላህን ተማፅኗል።

ቲክቨሃ እንዳለው ትናንት ምሽት ከዒሻ ሶላት በሁዋላ የተገደሉት የበድር መስጂድ ኢማም እና ኸጢብ ሸይኽ አብዱ ያሲንን የግድያ ሁኔታ በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በምርመራ ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገልጿል።

ወንጀል የፈፀመውን አካል በማፈላለግ ረገድ ፖሊስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ማህበረሰቡ በንቃት ጉዳዩን እንዲከታተልና ጥቆማዎችን በማድረስ አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንዲያደርግ ጥሪ ተላልፏል። ም/ቤቱ ወንጀለኛውን ለማጋለጥና ለህግ ለማቅረብ ከሚመለከተው አካል ጋር በጋራ እንደሚሰራ አሳውቋል።

በተመሳሳይ ዜና ሟቹ ሸይኽ አብዱ ያሲንን ስርዓተ ቀብር በርካታ ምዕመናን በተገኙበት እንድተፈጸመ ተገልጿል በስርዓተ ቀብር ወቅት በተላለፈ መልዕክት ትክክለኛው የግድያው ምክንያት ሳይጣራ ያልተረጋገጡና የምርመራ ሂደቱን የሚያበላሹ መረጃዎችን ከማሰራጨት መቆጠብ እንደሚገባ ተመልክቷል።

በተጨማሪ ፤ ሼይኽ አብዱ ያሲን የቲም ልጆች አሳዳጊ የነበሩና ከመሞታቸው በፊት እዳ እንዳለባቸው  የተገለፀ ሲሆን ህዝበ ሙስሊሙ ዕዳቸውን በመክፈል እና ከየቲም ልጆቻቸው ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀርቧል።

Exit mobile version